እስራኤል ዜጋዬን ለኢራን ሲሰልል ደረስኩበት አለች

እስራኤል አንድ ዜጋዋ ዋነኛ ጠላቴ ለምትላት ኢራን ሲሰልል ደርሼበታለው ስትል በቁጥጥር ስር እንዳዋለችው ገልጻለች።

ግለሰቡ ለኢራን ከመሰለሉም በተጨማሪ የሽብር ጥቃት እያቀነባበረ ነበር ተብሏል።

ሺን ቤት የሚባለው የእስራኤል የአገር ውስጥ የደኅንነት መስሪያ ቤት ሹም እንዳሉት ግለሰቡ ከኢራን የደኅንነት መሥሪያ ቤት ጋር ሌሎች አረብ-እስራኤላዊያን አሸባሪዎችን መመልመል በሚቻልበት ሁኔታ እየተወያየ ነበር።

ግለሰቡ የእስራኤልን ደኅንነት አደጋ ላይ በመጣል ክስ ተመሥርቶበታል።

ተጠርጣሪው ማንነቱ በስም አልተጠቀሰም።

ሺን ቤት እንደሚለው ግለሰቡ ባለፈው ወር በቁጥጥር ሥር ሲውል በእጁ የመረጃ ቋት ማጠራቀሚያ ሃርድ ዲስክ እንዲሁም መልዕክትን ከተቀባይ እስከ ላኪ በምሥጢር የሚተበትብ መላን የያዘ ሁነኛ መረጃን ይዞ ነበር።

ግለሰቡ በእስራኤል አደጋ ሊጣልባቸው የሚቻልባቸውን ቁልፍ ቦታዎች ለኢራን በመጠቆም ክፍያ ይቀበል ነበር ተብሏል።

የክስ ዶሴው እንደሚያስረዳው ግሰለቡ በቅርብ ጊዜ ፖፑላር ፍሮንት ፎር ሊብሬሽን ከተባለ የሊባኖስ ቡድን አባል ጋር ሁለት ጊዜ ምሥጢራዊ ግንኙነት አድርጓል ተብሏል።

ሁለቱ የተገናኙት በሁለት የተለያዩ ቦታዎች ነበር።

ከዚህም ሌላ በሃንጋሪ ቡዳፔስት ውስጥ ከኢራን የደኅንነት መሥሪያ ቤት አባላት ጋር ተገናኝቶ ነበር።

እስራኤላዊው ሰው ወደ ውጭ ባደረጋቸው ጉዞዎች መረጃን ስለመተብተብ፣ ስለመቆለፍና ስለመተንተን ስልጠና ተሰጥቶታል።

ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ የቀድሞ የካቢኔ ሚኒስትር ጎነን ሴጎቭ ለኢራን ይሰልሉ ነበር በሚል ዘብጥያ መውረዳቸው ይታወሳል።፡