አሜሪካ የአል ሻባብን መስራች መግደሏን አስታወቀች

አሜሪካ የታጣቂ እስላማዊ ቡድን አል ሻባብ መስራች አባል የነበረውን ዩሱፍ ጂስ በሶማሊያ በፈጸመችው የአየር ጥቃት መግደሏን አስታወቀች።

አል-ሻባብ ግን እስካሁን ድረስ በጉዳዩ ላይ ያለው ነገር የለም፡፡

የአሜሪካ ኃይል የአፍሪካ ዕዝ አዛዥ የሆኑት ጀነራል ስቴፈን ታውንሴንድ፤ በአል- ሸባብ ውስጥ ከፍተኛ ኃላፊነት የነበረው ዩሱፍን ጨካኝና እና ገዳይ ሲሉ ገልጸውታል፡፡

ግለሰቡ በሶማሊያ እንዲሁም ከሶማሊያ ውጭ ጥቃቶችን ይፈጽሙ ነበር ተብሏል፡፡

ፕሬዝዳነት ዶናልድ ትራምፕ ሥልጣን ላይ ከወጡ በኋላ አሜሪካ በሶማሊያ ላይ የምትፈጽመው ጥቃት በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል።

በመሆኑም አሜሪካ በፈጸመቻቸው የአየር ጥቃቶች በርካታ ወሳኝ የሆኑ የሶማሊያ ታጣቂዎች ተገድለዋል።

ይሁን እንጂ ሁልጊዜም አንድ ጅሃዲስት በተገደለ ቁጥር ሌላኛው ቦታውን ለመተካት ጊዜ አይወስድበትም።

አል ሻባብ በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች ኢላማዎቹን የመምታትና ግዛቶችን የመቆጣጠር አቅሙ እስካሁንም እንዳለ ነው።

ጀኔራል ቶውንሴንድ እንዳሉት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት አሜሪካ ሶማሊያ ውስጥ የምትፈጽመውን ጥቃት ለማቆም ያሰበች ነው።

ነገር ግን የአልቃዳ መሪዎች፣ አል ሸባብ እና እስላማዊ ታጣቂ ቡድን አይ ኤስ የሽብር አጀንዳቸውን ለመፈጸም ወረርሽኙን እንደመልካም አጋጣሚ እንደሚጠቀሙት ስላስታወቁ አሜሪካ ጥቃቷን መቀጠል እንዳለበት ወስናለች።

በሌላ በኩል የመብት ተሟጋቾች አሜሪካ በምትፈጽማቸው ጥቃቶች በርካታ ንጹሃን ሰዎች ለመገደላቸው ማስረጃ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

አሜሪካ በምታደርሰው ጥቃት ንጹሃ ዜጎች መገደላቸውን በተመለከተ አልፎ አልፎም ቢሆን ትቀበላለች።