እነ አቶ በረከት ስምኦን ዛሬ በችሎት ውሏቸው ላይ የጤና ችግር እንዳለባቸው በመግለጽ አጭር ቀጠሮ እንዲሰጣቸው ጠየቁ

አቶ ታደሰ ካሳ እና አቶ በረከት ስምኦን

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በእነ አቶ በረከት ስምኦን የክስ መዝገብ በቀረቡ ማስረጃዎች ላይ የዓቃቤ ህግን አስተያየት ለመስማት ለየካቲት 26/2012 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጠ።

ፍርድ ቤቱ በአንደኛ ተከሳሽ አቶ በረከት ስምኦን እና በሁለተኛ ተከሳሽ አቶ ታደሠ ካሣ በቀረቡ ማስረጃዎች ላይ የዓቃቤ ህግን አስተያየት ለመስማት እና ተከሳሾች ይያያዙልን ያሏቸው የሠነድ ማስረጃዎች እንዲቀርቡ ነበር ለዛሬ ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረው።

ተከሳሾች የኤሌክትሪክ ስማርት ቆጣሪ ማምረትን በተመለከተ ያቀረቡት የምስክር ማብራሪያ ላይ ዓቃቤ ህግ አስተያየት ለመስጠት አለመቻሉን ጠቅሶ ለዚህም ይሆን ዘንድ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቋል።

የተጠየቀው ተለዋጭ ቀጠሮ ደንበኞቻቸው እንደሚያንገላታ የገለጹት የአንደኛ እና ሁለተኛ ተከሳሽ ጠበቃ የኤልክትሪክ ስማርት ቆጣሪው ለማሳየት ብቻ ማቅረባቸውን በመግለጽ ተለዋጭ ቀጠሮው ውድቅ ይደረግ ብለዋል።

የኤሌክትሪክ ስማርት ቆጣሪው ወደ ሌላ ቦታ ሄዶ እንዲፈተሽ ከዓቃቤ ህግ የቀረበው ጥያቄም የንግድ ሚስጥርን የማይጠብቅ ሊሆን ይችላል በሚል ውድቅ እንዲሆን ተከሳሾች ጠይቀዋል።

ተከሳሾች ይቅረቡልን ካሏቸው ሠነዶች መካከል የተወሰኑት የቀረቡ ሲሆን ማብራሪያ የሚጠይቁ እና መረጃዎቹ የሚሰጡት በሌላ አካል በመሆናቸው ከሚመለከተው መሥሪያ ቤት እንዲጠየቅ የሚገልጹ ምላሾች ተሰጥተዋል።

ፍርድ ቤቱ በኤሌክትሪክ ስማርት ቆጣሪው ጉዳይ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለሐሙስ ተለዋጭ ቀጠሮ ቢሰጥም አንደኛ እና ሁለተኛ ተከሳሽ በኤሌክትሪክ ስማርት ቆጣሪው ምከንያት የንግድ ሚስጥር ከሚወጣ እና የአገር ሃብት ከሚጎዳ ማስረጃ መሆኑ ይቅር ብለዋል።

በጉዳዩ ላይ የመከላከያ ምስክር በመሆን የቀረቡት ግለሰብ ምስክርነትም ውድቅ ይሁን ብለዋል።

በዚህም በጽሑፍ ያቀረቡት ማስረጃ እንዲያዝላቸው ጠይቀዋል። ዓቃቤ ህግ በበኩሉ ዛሬ በቀረቡት ሠነዶች ላይ አስተያየት ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጠኝ ብሏል።

ግራ ቀኙን የተመለከተው ፍርድ ቤት ተከሳሾች በጠየቁት መሠረት ኤልክትሪክ ስማርት ቆጣሪውንም ሆነ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የቀረቡትን የመከላከያ ምስክር ቃል ውድቅ አድርጓል።

የተጠየቁ ማስረጃዎች ይቅረቡ ያለው ፍርድ ቤቱ ዓቃቤ ህግም አስተያየቱን በጽሑፍ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ቀጣዩ ቀጠሮም የካቲት 26/2012 እንዲሆን ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ተከሳሾች ጉዳዩ እስካሁን ከወሰደው ጊዜ አንጻር እና በህመም ምክንያት አሁን የተሰጠው ቀጠሮ ረዥም መሆኑን በመጥቀስ አጭር ቀጠሮ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

"ጤንነታችን አሳሳቢ ነው" ያሉት አቶ ታደሠ "በአካል መቅረብ የማንችል ሠዎች በመሆናችን አስከሬናችን ላይ ይፈረዳል" ብለዋል።

ፍርድ ቤቱ ተገቢ ያለሆነ አስተያየት መስጠታቸውን መግለጹን ተከትሎም አቶ ታደሠ ወዲያው ይቅርታ ጠይቀዋል።

ክትትል የሚያስፈልገው ህመም እንዳለባቸው የጠቀሱት አቶ በረከት ስምኦን በበኩላቸው ማረሚያ ቤት ከመግባታቸው በፊት ለቀዶ ህክምና ቀጠሮ ተሰጥቷቸው እንደነበር አስታውሰዋል። በዚህ ምክንያት በተደጋጋሚ ቀጠሯቸውን ማራዘማቸውን በመጥቀስ ቀጠሮ እንዲያጥርላቸው ጠይቀዋል።

በመዝገቡ ሦስተኛ ተከሳሽ የሆኑት አቶ ዳንኤል ግዛውም በጤና እክል ምክንያት አጭር ቀጠሮ ይሰጠን ብለዋል።

ፍርድ ቤቱ ካለበት የሥራ ጫና እና ነባራዊ ሁኔታዎችን ከግምት በማስገባት ቀጠሮ መስጠቱን አስታውቋል።

አቶ በረከት ስምኦን እና አቶ ታደሠ ካሣ የጥረት ኮርፖሬሽንን በቦርድ ሰብሳቢነትና በዋና ሥራ አስፈፃሚነት ሲመሩ ሥራን በማያመች ሁኔታ በመምራት የሙስና ወንጀል ፈፅመዋል በሚል ጥር 2011 ዓ.ም በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ነው።

ተከሳሾች ጉዳዩ እስካሁን ከወሰደው ጊዜ አንጻር እና በህመም ምክንያት አሁን የተሰጠው ቀጠሮ ረዥም መሆኑን በመጥቀስ አጭር ቀጠሮ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።