የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ ቴፒ ካምፓስ በጸጥታ ችግር ምክንያት ተማሪዎችን ወደ ቤታቸው እየሸኘ ነው

የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በአካባቢው በተፈጠረ አለመረጋጋት የተነሳ ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲሄዱ መወሰኑ ተሰማ።
ውሳኔው የተሰማው የዩኒቨርስቲው ሴኔት ካደረገው አስቸኳይ ስብሰባ በኋላ መሆኑ የታወቀ ሲሆን ተማሪዎች ለሦስት ተከታታይ ሳምንታት ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲሄዱ ተወስኗል።
ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ ከአስተዳደራዊ የመዋቅር ጥያቄ ጋር ተያያዘ በሸካ ዞን ሚዛን ቴፒ ከተማ ግጭት ተቀስቅሶ የሠው ህይወት ሲጠፋ ንብረትም መውደሙ ተገልጿል።
በቴፒ ያለው የፀጥታ ችግር ሊረጋጋ ባለመቻሉ የሚዛን ቴፔ ዩኒቨርስቲ ሴኔት በየካቲት 7/ 2012 ዓ.ም ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ተማሪዎች ከትናንት ሰኞ የካቲት 9/2012 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲሄዱ እንደተነገራቸው ቢቢሲ ያነጋገራቸው ተማሪዎች ገልፀዋል።
በዩኒቨርስቲው ተማሪ የሆነችውና ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ ያነጋገራት ተማሪ እንደምትለው ከሆነ "ዩኒቨርስቲው ይህንን ባይወስን እንኳ ተማሪው ሊሄድ ወስኖ ነበር።"
ዩኒቨርስቲው ተማሪዎችን ወደ ቤተሰቦቻቸው የሸኘው ነባር ተማሪዎች ትምህርታቸውን ጨርሰዉ የማጠቃለያ ፈተና ሳይፈተኑ እና አዲሶቹ ደግሞ ትምህርታቸውን ሳይጨርሱ መሆኑን ተማሪዎች ይናገራሉ።
ተማሪዎቹ አክለውም በዩኒቨርስቲው ቅጥር ግቢ ውስጥ ሠላም ቢሆንም በአካባቢው ያለው አለመረጋጋት ግን የዩኒቨርስቲው መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች በነጻነት ተንቀሳቅሰው የትምህርት ሥራውን ለማካሄድ ተቸግረዋል።
በዚህም የተነሳ ሁኔታው እስኪረጋጋ ድረስ በሚል ለሦስት ሳምንት ያህል ትምህርት መቋረጡንረና ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲሄዱ መወሰኑን ይናገራሉ።
በዩኒቨርስቲው የሥነ ሕይወት (ባዮሎጂ) መምህር የሆኑት አቶ ድሪባ ወርቅነህ ዩኒቨርስቲው እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰበን ምክንያት ሲያስረዱ ከሦስት ሳምንት በፊት ትምህርት መቋረጡን በማስታወስ ነው።
"ተማሪዎች ፈተና እንዳይቀመጡ በታጣቂዎች ማስፈራሪያ ይደርስባቸው ነበር" ሲሉም ይናገራሉ። ከዚያ በኋላም ለተማሪዎቹ ደህንነት ሲባል ከግቢ እንዲወጡ ተወሰነ ይላሉ።
በአሁን ሰዓት ዩኒቨርስቲው የትራንስፖርት አገልግሎት አቅርቦ ተማሪዎችን ከአካባቢው የማስወጣት ሥራ እየተሰራ መሆኑን ይናገራሉ።
አካባቢው ስለሚገኝበት ሁኔታ የጠየቅናቸው የሸካ ዞን ሕዝብ ግንኙነት አቶ አስማማው ኃይሉ ሲናገሩ ከሳምንት ወዲህ ሁኔታው መሻሻል ቢያሳይም "ትንኮሳው አልቆመም" ይላሉ።
በአካባቢው አሁንም ተኩስ እንደሚሰማ በሰውና በንብረት ላይም ጉዳት እየደረሰ መሆኑን አቶ አስማማው ጨምረው ያስረዳሉ።
የፀጥታ ኃይሉ፣ የዞኑ አመራር፣ ኮማንድ ፖስትና የክልሉ ደጋፊ ኃይሎች ችግር ፈጣሪ ናቸው ያሏቸውን አካላት ለመቆጣጠር ጥረት እያደረጉ መሆኑን ያስረዳሉ።
"ጥቃት አድራሾቹ እዚህም እዚያም ስላሉ የሕዝብ ተሳትፎና ድጋፍ ያስፈልጋል" የሚሉት አቶ አስማማው፣ በሚፈፀሙ ተኩሶች ሰዎች እየሞቱ ነው በማለት ስጋቱ መኖሩን ይናገራሉ።
ይህ የከተማው ችግር በዩኒቨርስቲውም ላይ ስጋት በመፍጠሩ ተማሪዎች አንድ ፈተና ከተፈተኑ በኋላ ተቋርጦ ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲሄዱ መወሰኑን ይገልጻሉ።
ማስፈራሪያ የሚያደርሱ አካላት መኖራቸውንም ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የምትገኘው ሸካ ዞን የተለያዩ ግጭቶች መሰማት ከጀመሩ ከዓመት በላይ አስቆጥረዋል።
ይህም ያለመረጋጋት በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ የተመደቡ ተማሪዎችን የትምህርት ጉዳይ ሲያስተጓጉል ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
የዚህ ችግር መንስኤ በእነዚህ ጥቂት ዓመታት የተከሰተ ሳይሆን ከ1985 ዓ.ም ጀምሮ የሸኮ ሕዝብ ራሳችንን በራሳችን እናስተዳድር የሚለው ጥያቄ ምላሽ ሳያገኝ በመቅረቱ እንደሆነ በአንድ ወቅት ያነጋግርናቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ገልፀውልን ነበር።
ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ተከስቶ በነበረ የጸጥታ ችግር ምክንያት አካባቢው ለረጅም ጊዜ በኮማንድ ፖስት ስር እየተዳደረ ይገኛል።
















