ሆንግ ኮንግ፡ በኮሮና ምክንያት በተከሰተ እጥረት አንድ ቡድን የሶፍት ጥቅሎችን ዘረፈ

በሆንግ ኮንግ በኮሮና ምክንያት በተከሰተ እጥረት የታጠቀ ቡድን የሶፍት ወረቀት ዘረፉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሆንግ ኮንግ አንድ ቡድን በመቶዎች የሚቆጠሩ የሶፍት ጥቅሎችን መዝረፉ መነጋገሪያ ሆኗል። ጥቅሎቹ አራት ሺ ሁለት መቶ ብር የሚያወጡ መሆናቸውም ታውቋል።

የኮሮና ቫይረስ ወረረሽኝን ተከትሎ ብዙዎች እጥረት ሊከሰት ይችላል በሚል ስጋት የሶፍት ወረቀት ጥቅሎችን በመሸመታቸው ገበያ ላይ ከፍተኛ እጥረት አጋጥሟል ተብሏል።

ዝርፊያው የተፈፀመው ሞንግ ኮክ ግዛት በሚገኝ ሱፐር ማርኬት በር ላይ ሲሆን የሶፍት ጥቅሎችን ለማድረስ አንድ ተላላኪ በሚንቀሳቀስበት ወቅት እንደሆነ ፖሊስ አስታውቋል።

ፖሊስ ሁለቱን ሰዎች በቁጥጥር ስር አውሎ የተወሰነውን የሶፍት ጥቅልም ማስመለስ እንደቻለ የሃገሪቱ ሚዲያ ዘግቧል።

ግለሰቡ የሶፍት ጥቅሎችን ወደ ሱፐር ማርኬቱ ለማስገባት ከመኪና ላይ ሲያወርድ በነበረበት ወቅት እንደዘረፉት ተገልጿል።

አንድ የሃገሪቱ ሚዲያ እንደዘገበው 7 ሺ ብር እንደሚያወጡ የመሚገመቱ 600 የሚሆኑ የሶፍት ጥቅሎች ተዘርፏል ብሏል። በግዛቷ የሶፍት ጥቅሎች በሚደርስበት ወቅት ረዥም ሰልፎችም ተስተውለዋል።

ምንም እንኳን መንግሥት በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የአቅርቦት እጥረት አይኖርም የሚል ማስተማመኛ ቢሰጥም ነዋሪዎች የሶፍት ጥቅሎችን በማከማቸት ላይ ናቸው።

የሶፍት ጥቅሎችን ብቻ ሳይሆን ነዋሪዎች ሩዝ፣ ፓስታና የቤት ማፅጃ ቁሳቁሶችንም በፍራቻ ምክንያት በማከማቸት ላይ ናቸው ተብሏል።

ከዚህም በተጨማሪ የፊት ጭምብልም ሆነ የእጅ ማፅጃ ማግኘት በጣም አዳጋች ሆኗል።

ባለስልጣናቱ በበኩላቸው ሃሰተኛ የሆኑ ዜናዎች በድረገፅ በመሰራጨታቸው ነዋሪዎች እጥረት ይከሰታል በሚል መሸመትና ማከማቸታቸውን ቀጥለዋል። ነገር ግን አሁንም ቢሆን ገበያው እንደተረጋጋ ነው ይላሉ።

በሆንግ ኮንግ ብቻ ሳይሆን በሲንጋፖርም ነዋሪዎች እጥረት ይከሰታል በሚል ፍራቻ የሶፍት ጥቅሎችን፣ የእጅ ማፅጃና የፊት ጭምብል እየሸመቱ ሲሆን፤ እስካሁን ባለው 75 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ተይዘዋል።