ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቻይና ለኮሮና ቫይረስ ህሙማን የገነባችውን ሆስፒታል ልትከፍት ነው
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በፍጥነት መዛመትን ተከትሎ ቻይና ለኮሮና ቫይረስ በብቸኝነት አገልግሎት የሚሰጥ ሆስፒታል ገንብታ ጨርሳለች።
ሆስፒታሉን የገነባችው የቫይረሱ መነሻ በሆነችው ዉሃን ከተማ ሲሆን የግንባታው ስራን አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት ስምንት ቀናት ብቻ ነው ያስፈለጉት።
ሆዎሸንሻን የሚል ስያሜ ያለው ይህ ሆስፒታል አንድ ሺ የህሙማን አልጋዎች አሉት።
ቻይና ከዚህ ሆስፒታል በተጨማሪ ለኮሮናቫይረስ ህሙማንን ብቻ የሚያክሙ ሆስፒታሎችን በመገንባት ላይ ናት።
በመላው ቻይና በተስፋፋው ኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር እስካሁን 17 ሺ የደረሰ ሲሆን ለ361 ህይወት መቀጠፍም ምክንያት ሆኗል።
ኮሮናቫይረስ ለቻይና ብቻ ሳይሆን ለዓለም ስጋት መሆኑ ቀጥሎ ፊሊፒንስ ውስጥ አንድ ግለሰብ በቫይረሱ ህይወቱ ማለፏ ተረጋግጧል።
ከቻይና ውጪ በቫይረሱ ሰው ሲሞት ይህ የመጀመሪያው ነው።
የ44 ዓመቱ ቻይናዊ ግለሰብ ከዉሃን የመጣ ሲሆን፤ የዓለም ጤና ድርጅት እንዳስታወቀው ግለሰቡ ፊሊፒንስ ከመድረሱ በፊት በቫይረሱ ተይዞ ነበር።
ይህንንም ተከተሎ አሜሪካ፣ አውስትራሊያ እና ሌሎች በርካታ አገራት ከቻይና የሚመጡ በረራዎችን አግደዋል።
ነገር ግን የአለም ጤና ድርጅት በረራዎችን ማገድ ከሚጠቅመው በላይ ሊጎዳ እንደሚችል ምክሮችን እየለገሰ ነው።
መረጃዎች እንዳይተላለፉ እንቅፋት ከመሆኑ በተጨማሪ፣ የህክምና ቁሳቀሱሶች በቀላሉ እንዳይንቀሳቀሱ ማድረግ፤ እንዲሁን አጠቃላይ የአገራትን ኢኮኖሚ ይጎዳል።
ከዚህ በተጨማሪም ተጓዦች በህገወጥ መንገድ ድንበሮችን እንዲያቋርጡ በር ስለሚከፍት የቫይረሱን በፍጥነት የመዛመቱን ሁኔታ በከፍተኛ ሁኔታ ሊያሻቅበው ይችላል ይላል ከአለም ጤና ድርጅት የተገኘው መረጃ።
አለም አቀፍ በረራ እግዶችን ተከትሎ ቻይና የአለም ጤና ድርጅትን ምክር የተላለፈ ነው በማለት ተችታዋለች።
ከቻይና የጤና ኮሚሽን የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው
- 21 ሺ 558 በበሽታው መያዛቸው የተጠረጠሩ ሰዎች
- 152 ሺ 700 የህክምና ክትትትል እየተደረገላቸው ያሉ
- 475 ግለሰቦች ህክምናቸውን ጨርሰው ከሆስፒታል የወጡ
እንዲሁም ከቻይና ውጭም 150 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውም ተረጋግጧል።
በሁቤ ግዛት በምትገኘው ዉሃን ከተማም ሆስፒታሎች በከፍተኛ ሁኔታ እያሻቀበ የመጣውን የህሙማንን ቁጥር ለማከም ከአቅማቸው በላይ ነውም ተብሏል።
ከሰሞኑም የሆንግ ኮንግ ዶክተሮች ቻይናን የሚያገናኘው ድንበር ሊዘጋ ይገባልም በሚል አድማ መትተዋል።
የቻይና ባለስልጣናት ግን በአለም ጤና ድርጅት ምክር መሰረት ድንበሩ እንደማይዘጋና መመርመሪያ ቦታዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።
ነገር ግን የቻይና ባለስልጣናትን ምላሽ አጥጋቢ አይደለም ያሉት እነዚህ ዶክተሮች ቻይና የጠየቁትን የማታደርግ ከሆነ ከነገ ጀምሮ ዶክተሮችም ሆነ ነርሶች የህክምና አገልግሎት ለመስጠት በቦታቸው ላይ እንደማይገኙ ነው።
ከሰሞኑም የዓለም የጤና ድርጅት የኮሮናቫይረስ የወቅቱ አሳሳቢ የምድራችን የጤና ስጋት ነው ሲል አውጇል።
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክትር ዶክትር ቴድሮስ አድሃኖም ይፋ እንዳደረጉት ለዚህ ውሳኔ ዋነኛው ምክንያት "በቻይና የተከሰተው ነገር ሳይሆን በሌሎች አገሮች እየሆነ ያለው ነው" ብለዋል።
የዓለም የጤና ድርጅት የበሽታ ወረርሽኝ ተከስቶ ከዚህ አይነት ውሳኔ ላይ ሲደርስ ይህ ስድስተኛው ሲሆን ከዚህ ቀደም ኤችዋን ኤን ዋን የተባለው ኢንፍሉዌንዛ፣ ኢቦላ፣ ፖሊዮ፣ ዚካና በድጋሚ የተከሰተው ኢቦላ ምክንያት ነበሩ።
በሽታው ሲጀምር በትኩሳት ቀጥሎም ደረቅ ሳል ተከትሎት ይከሰታል፤ ከዚያም ከሳምንት በኋላ የትንፋሽ ማጠርን በማስከተል አንዳንድ ህሙማንን የሆስፒታል ውስጥ ህክምና እንዲያስፈልጋቸው ሊያደርግ ይችላል።
በአራት ሰዎች ላይ ከሚከሰተው ይህ በሽታ አንዱ እጅግ የከፋ ሊሆን እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ። በቫይረሱ የተጠቃ ሰው ማስነጠስና የአፍንጫ ፈሳሽ ላይታይበት ይችላል።
የኮሮናቫይረስ ቀለል ካለ የጉንፋን ምልክቶች አንስቶ እየከፋ ሲሄድ እስከሞት ሊያደርስ ይችላል።
በሽታው የተያዙ ሰዎችን ለሞት እስከሚዳርጋቸው የተወሰነ ጊዜን ስለሚወስድ በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጡ ሰዎች መካከል የተወሰኑት እስካሁንም ሊሞቱ ይችላሉ ተብሎ ተሰግቷል።
በተጨማሪም ምን ያህል እስካሁን ያልተመዘገቡ በበሽታው የተያዙ ሰዎች እንዳሉ ማወቅ አስቸጋሪ በመሆኑ ቁጥሩ ከዚህም በላይ ሊሆን እንደሚችል ይታመናል።