ኤርትራ አሜሪካ የጣለችው የቪዛ እገዳ አግባብነት የለውም አለች

አሜሪካ ከሰሞኑ ኤርትራን ጨምሮ ለስድስት አገራት ዜጎች የምትሰጠው የስደት ቪዛ ላይ እገዳ መጣሏን ተከትሎ የኤርትራ መንግሥት አግባብነት የሌለውና ውሳኔው ወዳጅነትን ከግምት ውስጥ ያላስገባ ነው ብሎታል።

የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ በውሳኔው ቅሬታውን ገልፆ "ውሳኔው አሉታዊ መልእክት የሚያስተላልፍ ነው ብሎታል።

መግለጫው እንዳተተው ባለፉት 20 ዓመታት የኤርትራን ህዝብ ''በተቀናጀ ሁኔታ ለመቀነስ ድብቅ ፍላጎት ያላቸው ሀገራት'' የጥገኝነት ጥያቄዎችን ያለቅድመ ሁኔታ በመቀበል እና በተሳሳቱ መረጃዎች ላይ በመመስረት የሚወስዱትን እርምጃ በተደጋጋሚ ሲቃወም እንደነበር ጠቅሷል።

መንግሥታቸውም ከዚህ በፊት የነበሩት የአሜሪካ አስተዳደሮች ተመሳሳይ ፖሊሲዎችን በመከተላቸው በጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር 2004 እና 2009 ላይ ያለውን አቤቱታ ህጋዊ በሆነ መንገድ ማስገባቱን ገልጿል።

''የአሁኑ ውሳኔ ከዚህ በፊት የነበሩትን ከግምት ውስጥ ያስገባ አይደለም። ነገር ግን ዘዴያዊ በሆነ መልኩ ኤርትራን ነጥሎ የሚለይና ስለሀገሪቱ አሉታዊ መልእክት የሚያስተላልፍ ነው።''

''ስለዚህም የኤርትራ መንግሥት በውሳኔው የተሰማውን ቅሬታ መግለጽ ይወዳል። ውሳኔው ወዳጅነትን ከግምት ውስጥ ያላስገባና ከዚህ በፊት ገንቢ በሆነ መልኩ ስህተቶችን ለማረም የሚወሰዱ የአስተዳደሩ ፖሊሲዎች ጋር የሚጣረስ ነው።'' በማለት መግለጫው አስፍረወል

ከሰሞኑ አሜሪካ ኤረትራን ጨምሮ ናይጄሪያ፣ታንዛኒያ፣ ሱዳን፣ ኪርጊዝስታን እና ሚያንማር ላይ ከምትሰጣቸው የተወሰኑ የቪዛ አይነቶችን እንዳያገኙ እገዳ መጣሏን አስታውቃለች።

እገዳው ይፋ ከተደረገ በኋላ ናይጀሪያ ያለባትን የፀጥታና ደህንነት ክፍተት ለማሻሻል እንደምትሰራ የሃገሪቱ ፕሬዚዳንት ሙሃመድ ቡሃሪ ቢያስታውቁም የኤርትራ መንግስት ግን እገዳው ተገቢ አይደለም ብሏል።