አሜሪካ ኤርትራን ጨምሮ በስድስት አገራት ላይ የቪዛ እገዳ ጣለች

አሜሪካ ኤርትራን ጨምሮ ለስድስት አገራት ዜጎች የምትሰጠው የስደት ቪዛ ላይ እገዳ ጣለች።

እገዳው ከተጣለባቸው አገራት መካከል አራቱ ከአፍሪካ ሲሆኑ እነሱም ኤርትራ፣ ናይጄሪያ፣ ታንዛኒያና ሱዳን አሜሪካ አሜሪካ ከምትሰጣቸው የተወሰኑ የቪዛ አይነቶችን እንዳያገኙ እገዳ ጥላባቸዋለች።

ከአፍሪካ ውጭ ደግሞ ኪርጊዝስታን እና ሚያንማር በእገዳው የተጠቃለሉ አገራት ናቸው።

የእነዚህ አገራት ዜጎች የተወሰኑ አይነት ቪዛዎችን ለማግኘት እንደማይችሉ ቢገለጽም የቱሪስት ቪዛ ግን ለማግኘት ይችላሉ ተብሏል።

በ2018 አሜሪካ አሁን እገደ ከጣለችባቸው ሌሎች አምስት ዜጎች ካገኙት ቪዛ ከሁለት ዕጥፍ በላይ የስደተኞች ቪዛዎችን ለናይጄሪያ ሰጥታለች።

በዚሁ ዓመት አሜሪካ ከ8 ሺህ በላይ ቪዛ ለናይጄሪያዊያ፣ 2 ሺህ ለሱዳናዊያን፣ 290 ለታንዛኒያዊያንና 31 ደግሞ ለኤርትራዊያን ሰጥታለች።

አንድ ባለስልጣን እንደተናገሩት እነዚህ አገራት እገዳው የተጣለባቸው የአሜሪካን የጸጥታ ሕግና የመረጃ መጋራት ደረጃን (ስታንዳርድ) ማሟላት ባለመቻላቸው ነው።

"እነዚህ አገራት በብዙ መልኩ ጠቃሚ አገራት ናቸው፤ ነገር ግን ከእነርሱ የምንፈልገውን ዝቅተኛውን መስፈርት እንኳ ማሟላት ባለመቻላቸው እገዳው አስፈላጊ ሆኗል" በማለት ተጠባባቂ የአገር ውስጥ የደህንነት ሚንስትር ቻድ ዎልፍ አርብ ዕለት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

እሳቸው ጨምረው እንደተናገሩትም የአሜሪካ ባለስልጣናት ከአገሮቹ ጋር በመነጋገር የጸጥታ ሁኔታቸውን እንዲያሻሽሉና በሂደትም ከእገዳ ዝርዝሩ እንዲወጡ ይደረጋል ብለዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለመጀመሪያ ጊዜ የጉዞ እገዳ ያደረጉት በ2017 ነው። ያኔ በተረቀቀው መመሪያ መሰረትም ሰባት የሙስሊም አገራት የአሜሪካን ቪዛ እንዳያገኙ ክልከላ ተደርጎባቸው ይገኛሉ።

አሜሪካ ከዚህ ቀደምም በ2017 ለኤርትራዊያን የተወሰኑ የቪዛ ዓይነቶችን ከልክላ ነበር።

ለመሆኑ አዲሱ መመሪያ ምንድን ነው?

በአዲሱ መመሪያ መሰረት ከናይጄሪያ፣ ኤርትራ፣ ኪርጊዝስታንና ሚያንማር ለሚመጡ ዜጎች ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ይዘት ያለው ቪዛ አይሰጣቸውም።

ታንዛንያና ሱዳን ደግሞ የዲቪ ሎተሪ እድላቸው ይሰረዝባቸዋል።

በአዲሱ መመሪያ መሰረት ለጎብኝዎች፣ የንግድ ሥራ ለሚሰሩና ሕክምና ለሚያደረጉ ሰዎች የሚሰጠው ጊዜያዊ ቪዛ ግን ከእገዳው ጋር እንደማይገናኝ ባለስልጣኑ አረጋግጠዋል።

አሁን የተደረገው እገዳ እንደ ከዚህ ቀደሙ የሙስሊም አገራትን ብቻ ኢላማ ያደረገ አይመስልም። እገዳው ከተጣለባቸው አገራት መካከል ኪርጊዝስታን እና ሱዳን በአብዛኛው ሙስሊሞች ሲሆኑ ናይጄሪያና ኤርትራ ግን ሙስሊሙ ህዝባቸው ከጠቅላላ ህዝባቸው ግማሽ ብቻ የሚሸፍን ነው።

የጉዞ እገዳው ምንድን ነው?

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ስልጣን ላይ በወጡ በሰባተኛ ቀናቸው ነበር አወዛጋቢውን የጉዞ እገዳ የሚያትት መመሪያ የፈረሙት። እሳቤው የአሜሪካን ደህንነት ለመጠበቅ የግድ አስፈላጊ ነው በሚል ነበር።

እገዳው ሰባት በአብዛኛው የእስልምና እምነት ተከታይ ባላቸው አገራት ላይ ያነጣጠረ ሲሆን ከፍርድ ቤትም ብርቱ ሙግት ገጥሞት ነበር።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ባረቀቁት አወዛጋቢ መመሪያ መሰረትም የኢራን፣ ሊቢያ፣ሶማሊያ፣ ሶሪያ፣ የመን፣ ቬኒዙዌላ እና ሰሜን ኮሪያ የእገዳው ሰለባ ሆነዋል።

ከእነዚህ አገራት ወደ አሜሪካ ለሚመጡ ዜጎች የቪዛ እገዳው ቢጣልም ለተማሪዎችና አለፍ ሲልም ከአሜሪካ ጋር የተለየ ቁርኝት አላቸው ለተባሉ ግለሰቡች እገዳው የተጣለባቸው አገራት ዜጎች ቢሆኑም ቪዛ የማግኘት ልዩ እድል እየተመቻቸላቸው ነው።