ማረጥን በአስር ዓመት የሚያዘገየው ህክምና ጥያቄ ተነሳበት

በህክምናው ዘርፍ ፈር ቀዳጅ የተባለለትና ማረጥን በአስር ዓመት የሚያዘገየው ሂደት በዘርፉ ባለሙያዎች ዘንድ ጥያቄን አጭሯል።
የዘላቂነቱ ሁኔታ እንዲሁም የደህንነቱ ሁኔታ ሳይፈተሽ በተግባር ላይ ውሏል በሚል ጥያቄ ቢነሳበትም አንዳንድ ሴቶች ግን ወደ 250 ሺህ የሚገመት ብር በማፍሰስ የሚያርጡበትን ጊዜ ለማስረዘም በህክምናው ሂደት ቀጥለውበታል።
በርሚንግሃም ተቀማጭነቱን ያደረገውና ሂደቱን የፈጠረው ፕሮ ፋም የተሰኘው ኩባንያ የሥራ ሂደት መሪ ፕሮፌሰር ሲሞን ፊሸል ግን ጥርጣሬዎችን ችላ በማለት ይህ ሂደት በአምሳዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ሴቶች ልጆችን መውለድ የሚያስችልና፤ ከማረጥ ጋር ተያይዘው የሚመጡ እንደ ልብ ድካምና የአጥንት መሳሳትን የሚያስወግድ ነው በማለት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
ሂደቱ እንቁላል የምታመርተውን አካል እንቁልጢ (ኦቫሪ) በቀዶ ጥገና ማስወገድን የሚያካትት ሲሆን፤ ይህም የሰውነት አካል ለተወሰነ ጊዜ እንዲቀዘቅዝ ይደረጋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከዚያም ከሰውነት ጋር እንዲጣበቅ ይደረጋል።
ህክምናውን እያከናወኑ ያሉት አንድ ዶክተር እንደሚያስረዱት በዚህ ሂደት ያለፈች ሴት ልጅ መውለድ ብትፈልግ እንደገና ማህፀን ቱቦዋ ጋር እንዲተከል ይደረጋል።
ነገር ግን የሴትዮዋ ፍላጎት ልጅ አለመውለድና ማረጥን ብቻ ማዘግየት ከሆነ በሰውነቷ ውስጥ ጥሩ የሆነ የደም ስርጭት ካለበት አብዛኛውን ጊዜ ብብት ስር ይተከላል።
ሂደቱ ቀደም ባለ እድሜ ቢካሄድ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው የሚናገሩት ፕሮፌሰር ፊሸል ለዚህም እንደ ምክንያትነት የሚያስቀምጡት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው እንቁላሎች መመረት የሚያስችልና በሆርሞንም የበለፀጉ እንደሚሆኑ ነው።
እስካሁንም ባለው አስራ አንድ ሴቶች ሂደቱን አከናውነዋል።

ፕሮፌሰር ፊሸል አጠቃላይ ሂደቱ ሙከራ መሆኑን ቢያምኑም አንዳንድ ሂደቶቹ ግን እሰከዛሬ ሲሰራባቸው የነበሩ ናቸው ብለዋል።
ተመሳሳይ ሂደትም ከዚህ ቀደም የሚፈፀም ሲሆን በተለይም በካንሰር የተጠቁ ሴቶችን መውለድ ለማስቻል በተሳካ መልኩ ይሰራበት ነበር ብለዋል።
እናም እስካሁን ያለውንም መረጃ በመፈተሽ ሂደቱ ደህንነቱ የተጠበቀ ነው ማለት ይቻላል ብለዋል።
'የመረጃ እጦት'
ምንም እንኳን ፕሮፌሰር ፊሸል ይህንን ይበሉ እንጂ በእንግሊዝ ወላድነት ላይ የሚሰራው ተቋም ሊቀመንበር የሆኑት ዶ/ር ሜላኒ ዴቪስ በበኩላቸው አይስማሙም "ጤነኛ የሆኑ ሴቶች አላስፈላጊ የሆነ ቀዶ ጥገና እያደረጉ ነው" ብለዋል።
በካንሰር ህመምተኞች ዘንድ በተወሰነ መልኩ ወላድነትን መመለስ የሚያስችል ሂደት መኖሩን ጠቅሰው ጤነኛ ሴቶች ግን በዚህ ሂደት አለማለፋቸው እንዲሁም በቀዶ ጥገና ተወግዶ ወደ በረዶነት የተቀየረው አካል ከአስር ዓመት በላይ ይቆያል ለሚለውም ምንም አይነት ማስረጃ የለም ብለዋል።
ነገር ግን እስካሁን ባለውና እየተሰራበት ያለው ሆርሞን የሚቀየርበት ህክምና (ሆርሞን ሪፕሌስመንት ቴራፒ) በከፍተኛ ደረጃ ምርምር የተሰራበትና መውሰድም ለሚፈልጉ ሴቶችም በቀላሉ የሚያገኙት ሂደት እንደሆነ ዶክተር ዴቪስ አፅንኦት በመስጠት ይናገራሉ።
ወደ በኋላ እድሜያቸው መውለድ ለሚፈልጉ ሴቶችም እንቁላልን ማቀዝቀዝ (ኤግ ፍሪዚንግ) ፕሮፌሰር ፊሸል ከሚያቀርቡት አማራጭ በተሻለ መልኩ ስኬታማ ነው ብለዋል።
ማረጥን ማከም
ምንም እንኳን ከማረጥ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ምልክቶችን ብዙ ሴቶች ማከም ባይፈልጉም፤ ለሚፈልጉት ግን አማራጭ መፍትሄዎች ተቀምጠዋል።
ዋነኛው ህክምናም ሆርሞንን የመቀየር ቴራፒ ሲሆን በማረጥ ወቅት የሚከሰት ትኩሳትና ላብ ላብ የሚያሰኙ ምልክቶችን ቢያስቀሩም ነገር ግን ለአንዳንድ ሴቶች አይመከርም።
ሆርሞን የመቀየር ህክምናን መውሰድ ለማይፈልጉ ደግሞ ሌሎች አማራጭ መንገዶች አሉ
- የተመጣጠነ ምግብ መመገብ፣ የስብ መጠናቸው ዝቅተኛ የሆነና በካልሺየም የበለፀጉ ምግቦችን መመገብ አጥንትን ከማጠንከሩም በላይ የልብ ደህንነትንም ይጠብቃል።
- በየቀኑ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ጭንቀትን ለመቀነስ እንዲሁም ከልብ በሽታ ለመከላከል ይረዳል።
- ሲጃራ ማጤስ ማቆም
- የመጠጥ ፍጆታዎቸን መቀነስ የመሳሰሉት ናቸው።
ምንም እንኳን ፕሮፌሰር ሲሞን ፊሸል ባቀረቡት ሂደት ጥርጣሬዎች ቢኖሩም የራሳቸው ልጅ ገና በሃያ ሁለት ዓመቷ ሂደቱን እንደምታከናውን ገልፃለች።
"ልጅ በቅርቡ የመውለድ እቅድ የለኝም፤ አሁን ማተኮር የምፈልገው ሥራዬ ላይ ላይ ነው፤ ከዚህም በተጨማሪ ልጅ ከመውለዴ በፊት ማከናወን የምፈልጋቸው ጉዳዮች አሉኝ" ብላለች።
"መውለድ ብፈልግ አሁን መውለድ አለብኝ ብዬ ልገደድ አይገባም፤ ቀለበት አሁን ማሰር እንዳለብኝ አይሰማኝም" ብላለች።












