በኦሮሚያና በሐረሪ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ ተከስቶ በነበረው አለመረጋጋት የሟቾች ቁጥር 86 መድረሱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዐብይ አስታወቁ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ

የፎቶው ባለመብት, Walta Tv

ከሳምንት በፊት በኦሮሚያና በሐረሪ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ተከስቶ ከነበረው አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 86 መድረሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዕሁድ አመሻሽ ላይ በሰጡት መግለጫ ከሞቱት ሰዎች መካከል 76ቱ በእርስ በርስ ግጭት እንዲሁም 10 ሰዎች ደግሞ በጸጥታ ኃይሎች በተወሰደ እርምጃ ህይወታቸው ማለፉን አመልክተዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ መግለጫ ላይ ሟቾቹ ከቁጥር ባሻገር በብሔር፣ በጾታና በሐይማኖት ተዘርዝረው የተጠቀሱ ሲሆን ከ86ቱ ውስጥ 4ቱ ሴቶች ናቸው።

"ይህ ክፉ ክስተት በኢትዮጵያ የግጭት እሳት ሲነሳ አንዱን ክፍል አቃጥሎ ሌላውን አሙቆ የሚያልፍ እንዳልሆነ ያሳየ ነው" በማለት እንዲህ አይነት ሁኔታ ሲከሰት ጉዳት የሚደርሰው በተወሰነው በአንድ ብሔር ወይም የሐይማኖት ተከታይ ላይ ብቻ ሳይሆን ሁሉንም የሚነካ መሆኑን ተናግረዋል።

ከ80 በላይ የሚሆኑ ዜጎችን ህይወት የቀጠፈው አለመረጋጋትን ተከትሎም መንግሥታቸው "ያለፉ ስህተቶች ለማረም እየሰራን በሌላ በኩል ደግሞ ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ ህጋዊና ተመጣጣኝ እርምጃ እንወስዳለን" በማለት በድርጊቱ ውስጥ እጃቸው ያለ ሰዎች ሁሉም በጥፋታቸው መጠን ተጠያቂ እንደሚሆኑ ገልጸዋል።

ይህንን ለማድረግም መንግሥታቸው በህግ በተቀመጠውና በተፈቀደው መሰረት አስፈላጊውን ለማድረግ አቅም፣ ዝግጁነትና ብቃት እንዳለው አመልክተዋል።

መንግሥት አንዳንዶች እንዲማሩበት ብሎ የሰጠውን "ሰፊ ልብና ትከሻ ሳይጠቀሙበት ቀርተው የዜጎች ህይወት ለአደጋ የሚጋለጥበት ምክንያት ፈጥሯል" በማለት ወቅሰው ከዚህ በኋላ "መንግሥት የዜጎችንና የተቋማትን ደህንነት ለመጠበቅ የአገሪቱ ህግ ባስቀመጠው መሰረት" አስፈላጊውን ሁሉ እንዲያደርግ አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪም መንግሥታቸው አገሪቱ ያለው የፖለቲካና የዴሞክራሲ መድረክ እንዲሰፋ በማሰብ ሆደ ሰፊነቱን አብዝቶ ነገሮችን ሲያስታምም መቆየቱንና "ከኃይል ይልቅ መመካከርን በመምረጥ መታገሱን" ጠቅሰው "ትዕግሰትን ፍርሃት፤ ማስታመሙ ድካም የመሰላቸው ካሉ ግን ተሳስተዋል" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ መንግሥታቸው ከጀመረው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሥራው ወደኋላ እንደማይል በመግለጫቸው ላይ የተናገሩ ሲሆን "በአንድ በኩል የፖለቲካውንና የዴሞክራሲውን ምህዳር ለማስፋት፤ በሌላ በኩል ደግሞ ፍትህንና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ" እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የአገሪቱ የፀጥታ አካላትም በሁሉም ቦታ "ሰላም፣ ደህንነት፣ የህዝቦችን አብሮ መኖርና አንድነት፣ የተቋማትንና የኢንዱስትሪዎችን ደህንነት በህግ አግባብ የመጠበቅ ግዴታቸውን" በተገቢው ሁኔታ እንዲያከናውኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ወቅት አሳስበዋል።

"የፍትህ አካላትም በእንዲህ አይነቱ ድርጊት ውስጥ የተሳተፉ አጥፊዎች ትምህርት፤ ለተጎጂዎች ደግሞ ካሳ የሚሆን የተፋጠነ ፍትህ በማስፈን ፍትህን እንዲያረጋግጡ" ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ጥሪ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዋልታ ረገጥ ብለው በጠሩት የተካረረ "የብሔርና የእምነት ጫፍ ላይ ቆመው ችግሮችን የሚያባብሱ ወገኖች ባላቸው አመለካከትና በሚያስተላልፉት መልዕክት ተጨማሪ እልቂትና ጥፋት እንዳይከሰት" እራሳቸውን እንዲቆጥቡ አሳስበዋል።