የታይላንድ ፏፏቴ፡ ከሞት ለመትረፍ ሲደጋገፉ የነበሩ ዝሆኖች ሞቱ

በታይላንድ ፏፏቴ ውስጥ ከሞት ለመትረፍ ሲደጋጋፉ የነበሩ ስድስት ዝሆኖች መሞታቸው ተገለጸ።

ባለሥልጣናቱ እንዳሉት አደጋው የተፈጠረው በታይላንድ ሃኦ ያኢ ብሔራዊ ፓርክ አንድ የዝሆን ግልገል ወደ ፏፏቴው ተንሸራታ በመግባቷ ምክንያት እርሷን ለማትረፍ ሲረባረቡ በነበረበት ወቅት ነው።

በዚያው ፏፏቴው ገደል ጫፍ ሕይታቸውን ለማትረፍ ሲፍጨረጨሩ የነበሩ ሌሎች ሁለት ዝሆኖችም በታይላንድ ባለሥልጣናት ሕይወታቸው ሊተርፍ ችሏል።

ሄው ናሮክ በመባል የሚታወቀው ፏፏቴ ተመሳሳይ አደጋዎችን ሲያስተናግድ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

በጎርጎሳውያኑ 1992 ስምንት ዝሆኖች መንጋ ወደ ፏፏቴው ወድቀው መሞታቸው የአገሪቷን ትኩረት የሳበ ክስተት ነበር።

የታይላንድ ብሔራዊ ፓርክ የዱር እንስሳትና እፅዋት ጥበቃ እንዳለው፤ ባለሥልጣናቱ አደጋው የተከሰተበት ቦታ የጎበኙ ሲሆን በፏፏቴው የተወሰዱ ዝሆኖች መንገዱን ዘግተው እንደነበር ተመልክተዋል።

ከሦስት ሰዓታት በኋላ የ3 ዓመት ዕድሜ ያላት ዝሆን በሄው ናሮክ ፏፏቴ ውስጥ ሞታ የተገኘች ሲሆን ሌሎች አምስቱም በዚያ አቅራቢ ሞተው ተገኝተዋል።

የብሔራዊ ፓርኩ ኃላፊ ሃንችት ስሪኖፓዋን፤ ሌሎች ከአደጋው የተረፉት ሁለት ዝሆኖች ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በታይላንድ የዱር እንስሳት ፋውንዴሽን መስራች ኤድዊን ዊክ እንደሚሉት ዝሆኖች ምግብ ለመፈለግም ሆነ ራሳቸውን ከአደጋ ለመጠበቅ የሚንቀሳቀሱት በመንጋ ነው።

በመሆኑም "በሕብረት የአኗኗር ዘይቤ ያላቸው ዝሆኖች እንዲህ አይነት አደጋ ሲገጥማቸው በሃዘን ልባቸው ይሰበራል። ይህ የዝሆኖች ባህሪ ነው" ብለዋል።

በዚህም ምክንያት ከአደጋው የተረፉት ዝሆኖች ምን አልባት በሕይወት ለመቆየት ችግር ሊገጥማቸው እንደሚችል ተሰግቷል።

"አደጋው ግማሽ ያህል ቤተሰብን የማጣት ያህል ነው" የሚሉት ኤድዊን ዊክ የእንስሳቱ ስሜት ተፈጥሯዊ በመሆኑ ምንም ሊያደርጉ እንደማይችሉ ያስረዳሉ።

በታይላንድ 7 ሺህ የሚጠጉ እስያዊ ዝሆኖች የሚገኙ ሲሆን ግማሽ ያህሉ የሚኖሩት በእንስሳት ማቆያ ውስጥ ነው።