ሳሙኤል ኤቶ እግር ኳስ ሊያቆም ነው

አራት ጊዜ የአፍሪካ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ተብሎ መመረጥ የቻለው ካሜሩናዊው ሳሙኤል ኤቶ ከ22 ዓመታት የእግር ኳስ ህይወት በኋላ ጫማውን ሊሰቅል ስለመሆኑ ጠቁሟል።

የ38 ዓመቱ የቀድሞው የካሜሩን ብሄራዊ ቡድንና የባርሴሎናው አጥቂ በኢንስታግራም ገጹ ላይ ባሰፈረው መልእክት ''ተፈጸመ፤ ወደ ሌላ የፈተና ጉዞ ተጀመረ'' ሲል ጽፏል።

ኤቶ ለሃገሩ ካሜሩን በ118 ጨዋታዎች 56 ግቦችን ማስቆጠር የቻለ ሲሆን በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ በኤልሲና በኤቨርተን ተጫውቷል። ባለፈው ዓመት ደግሞ ለቱርኩ ኮንያስፖር ለአጭር ጊዜ ከተጫወተ በኋላ የኳታሩን ስፖርት ክለብ ተቀላቅሏል።

እ.አ.አ. ገና የ16 ዓመት ታዳጊ እያለ የስፔኑን ሪያል ማድሪድ በ1996 ቢቀላቀልም መጫወት የቻለው ሶስት ጨዋታዎችን ብቻ ነበር። ከዛም በውሰት ለሌጋኔዝ፣ ኤስፓኞል እና ማሎርካ ተጫውቷል።

በ2000 ለማሎርካ በ133 ጨዋታዎች 54 ግቦችን በማስቆጠር የቡድኑ የምን ጊዜም ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ በመሆን ታሪክ ሰርቷል።

በ2004 ደግሞ ባርሴሎናን ከተቀላቀለ በኋላ ሶስት ጊዜ የስፔን ላሊጋን ማሸነፍ የቻለ ሲሆን በ2006 እና በ2009 ቡድኑ የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ አሸናፊ እንዲሆን አስችሏል። በሁለቱም የፍጻሜ ጨዋታዎችም ግብ አስቆጥሮ ነበር።

በ2006 የውድድር ዘመን ለባርሴሎና በ34 ጨዋታዎች 26 ግቦችን ካስቆጠረ በኋላ በሊጉ የወርቅ ጫማ ማሸነፍ የቻለ ብቸኛው አፍሪካዊ ተጫዋች መሆን ችሏል።

በአጠቃላይ በ144 ጨዋታዎች 108 ግቦችን ለባርሴሎና ያስቆጠረው ኤቶ በ2009 ወደ ኢንተር ሚላን በመሄድ ለሶስተኛ ጊዜ የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን ማንሳት ችሏል። የጣሊያን ሴሪ አ እና የፊፋ ክለቦች የዓለም ዋንጫዎችን ከቡድኑ ጋር አንስቷል።

በመቀጠል ኤቶ ያመራው ወደ ራሺያ ነበር። አንዚ ማካቻካላ ከሚባለው ቡድን ጋርም ለሁለት ዓመታት ከቆየ በኋላ በ2013 ቼልሲን ተቀላቀለ። ኤቨርተን፣ ሳምፕዶሪያ እና አንታሊያስፖር ደግሞ የተጫወተባቸው ሌሎች ቡድኖች ናቸው።

ለካሜሩን ብሄራዊ ብድን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲጫወት ሳሙኤል ኤቶ ገና የ17 ዓመት ታዳጊ ነበር። በ1998 በተካሄደው የዓለም ዋንጫ ሃገሩ ከኮስታሪካ ስትጫወት በመሰለፍ የጀመረው ኤቶ በውድድሩ ትንሹ ተጫዋች ተብሎ ነበር።

ከብሄራዊ ቡድን እራሱን እስካገለለበት ጊዜ ድረስ ሃገሩን ወክሎ በአራት የዓለም ዋንጫ ውድድሮች ላይ ተሳትፏል።

በ2000 እና በ2002 የተካሄዱትን ተከታታይ የአፍሪካ ዋንጫዎችንም ከሃገሩ ጋር አንስቷል። በውድድሮቹም 18 ጎሎችን በማስቆጠር ኮኮብ ግብ አግቢ ሆኖ መጨረስ ችሎ ነበር።

ከዚህም በተጨማሪ በ2000 በተካሄደው ኦሎምፒክ ከቡድን አጋሮቹ ጋር በመሆን ለሃግሩ የወርቅ ሜዳሊያ አስገኝቷል።