በአውሮፓ የኢትዮጵያዊያን ፌስቲቫል፡ ሙዚቃ፣ ኳስ፣ ፍቅርና ቡጢ..

በጋ ፈረንጆቹን ያፈካቸዋል። ኮምጫጫ አውሮፓዊ ለማያውቀው መንገደኛ ሳይቀር ፈገግታ የሚመጸውትበት ጊዜ ነው። ለሀበሾችስ ቢሆን? በጋው የፌሽታ ነው። በረዶ ያቆፈነው በጓንት የተጀቦነ እጅ እንጀራ ለመጠቅለል የሚፍታታበት ወቅት ነው። ካፖርታና ጋቢ ወዲያ የሚሽቀነጠርበት ወቅት ነው። በከፊል ዕርቃን መዘነጥ የሚያስችል በቂ ንዳድ አለ።

ከሁሉ በላይ ዓመታዊው የባህልና ስፖርት አውደፌሽታ አለ። ቁርጥ አለ፤ በቂቤ ያበደ ሽሮ አለ፤ ጎረድ ጎረድ አለ። ቡናው ይንከሸከሻል…እጣኑ ይንቦለቦላል…፤ የአገር ሰው ከዚህ በላይ ምን ይሻል?

ይህ አገር ቤት እየኖረ እንግሊዝኛ ለሚቀናው ሰው ‹‹ሶ ዋት?›› የሚያስብል ሊሆን ይችላል። ከአገር ለራቀ ሰው ግን ትርጉሙ ራስ ዳሽን ነው። ለዚህም ነው ለዓመታዊው የሐበሾች ‹‹መካ›› በየዓመቱ በሺዎች የሚተሙት፡፡ ዘንድሮ ተረኛዋ ዙሪክ ነበረች። እጅግ አምሮባት ተኩላ ነበር እንግዶቿን የጠበቀችው።

እርግጥ ነው በነዚህ መድረኮች ላይ ሀበሾቹ የሚገናኙት ለሳቅ ለጨዋታ ነው። የሚጠራሩት ለእስክስታና ፌሽታ ነው። ሆኖም ክትፎና ቁርጥ ቀማምሰው ሲጨርሱ ቡጢ ይቀማመሳሉ። መነሻው ምንም ሊሆን ይችላል። በሐበሾች መንደር ግን ጸብ ጠፍቶ አያውቅም። በዙሪክ ይህ ባይሰተዋልም በስቱትጋርት ሆኗል።

እንዴት እጅግ የተነፋፈቀ የአገር ልጅ ለያውም በሰው አገር፣ ለያውም ለሳቅ ለጨዋታ ተጠራርቶ ቡጢ እንደሚሰነዛዘር መተንተን የቻለ ሊቅ ለጊዜው አልተገኘም።

ብቻ የአገር ልጆች በየዓመቱ ተሰባስበው የ‹‹ፍቅር ቡጢ››ን እንካ ቅመስ-እንቺ ቅመሽ ሲባባሉ ዓመታት አስቆጥረዋል።

ለምሳሌ የዛሬ ዓመት የፌሽታው አስተናጅ ስቱትጋርት ነበረች። ቴዲ አፍሮ መጥቶ አፍሮ ተመልሷል፤ ሳይዘፍን። ንብረት ወድሟል። የአዳራሽ መስታወት እንዳልነበር ሆኗል። የጀመርን ፖሊስ ‹‹ኤሎሄ! ዘንድሮ ምን ጉድ ላ'ክብን›› ብሏል። ጸቡ ከእኛም አልፎ ወንድም ኤርትራዊያንን ያሳተፈ ነበር።

የቢራ ጠርሙስ ከአንድ ኢትዮጵያዊ እጅ ተምዘግዝጎ ሌላ ኢትዮጵያ የራስ ቅል ላይ አርፏል። ሀበሾች ሲገናኙ ‹‹አብሿቸው›› ይነሳል መሰለኝ ፍቅራቸው በጸብ ካልደመቀ…። ኢትዮጵያዊያኑ ወደ ዙሪክ የከተሙት ይህንኑ የጸብ ትዝታ ይዘው ነበር። ዙሪክ አላሳፈረቻቸውም። ለሰላሙ ቅድሚያ ሰጥታ አጫውታ፣ አዝናንታ አፋቅራ ሸኝታቸዋለች።

በአሉታዊነቱ ስቱትጋርት እንደ ምሳሌ ተነሳ እንጂ፣ ሮም በ2012 ‹‹የፌዴሬሽኑን ገንዘብ ይዘው ተሰውረዋል›› በሚሉና ‹‹እንዲያውም አዘጋጅተን ከሰርን›› በሚሉት መሀል መራር ጸብ ነበር።

ደግነቱ የሮም ጸበኞች ዘንድሮ በዙሪክ ይቅር ለእግዛብሔር ተባብለዋል።

በ2014 ሙኒክ ላይም ምክንያቱ መናኛ የሆነ ዱላ መማዘዝ ነበር።

‹‹ሐበሻ ድሮም አብሮ መብላት እንጂ…አብሮ መሥራት…›› የሚል ተረት የሚያስተርቱ አጋጣሚዎች በርካታ ነበሩ። ሆኖም ይህን ሁሉ ዓመት ከጸብና መወነጃጀል መራቅ ለምን አልተቻለም? የሚለው ጥያቄ ዛሬም ሙሉ በሙሉ ምላሽ አላገኘም።

አንድ ሁለት ምክንያቶችን መዘርዘር ግን ይቻላል። አንዱ በየዝግጅቶቹ ውስጥ የአገር ቤቱ ፖለቲካ የሚያጠላው ጥላ ሰፊ መሆኑ ነው። ሌላው በጎ ፈቃድ እንጂ የአመራር ክህሎት በሌላቸው ሰዎች ትልቅ ድግስ መሰናዳቱ የሚፈጥረው ትርምስ ነው። ሦስተኛው ለጥቅም መንሰፍሰፍ ነው።

‹‹እንዲህ ዓይነቱን ሺህዎች የሚታደሙበት አውደ ፌሽታ ለማሰናዳት ከመቶ እስከ ሁለት መቶ ሺህ ዩሮ ፈሰስ መደረጉ አይቀርም›› ይላሉ ወጪውን የሚያውቁት። ይህንን ወጪ ለመመለስ፣ ብሎም በትርፍ ለመንበሽበሽ አድብቶ የሚጠብቀው ብዙ ነው፤ በዚህ መሀል ትርምስ ይፈጠራል። ከፍተኛ የጥቅም ግጭት ይነሳል።

‹‹ስልጡን አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በሰለጠነ መንገድ መነጋገር ይሳናቸዋል። በሰለጠነ መንገድ ሂሳብ ኦዲት አያስደርጉም። በሰለጠነ መንገድ ወጪና ገቢ አያሰሉም። መጨረሻው የማያምረው ለዚህ ይመስለኛል›› ይላል በዓመታት ውስጥ ባየው ነገር ተስፋ ቆርጦ ራሱን ከአዘጋጅነት ተሳትፎ ያገለለ ወጣት ለቢቢሲ።

የዙሪኩ መሰናዶ ግን በሁሉም መለኪያ የተሻለና የተዋጣለት መሆኑ ለብዙዎች መልካም ስሜትን ፈጥሯል። ለሌሎች ቀጣይ አዘጋጅ ቡድኖችና ከተሞችም ምሳሌ መሆን የሚችል ነበር።

ኢትዮጵያ መግባት የማይችሉ ኢትዮጵያዊያን

ከደርግ ጀምሮ ከዚያም ቀደም ብሎ ከአገር የወጡ ኢትዮጵያዊያን አሉ። በአውሮፓ የሚኖሩ የድሮ የብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች ብዛታቸው ለጉድ ነው።

ይህ ዓመታዊ አውደ ፌሽታ ታዲያ ለአንዳንዶች የፌሽታ ያህል ፌዝ አይደለም። የምር ጉዳይ ነው። የአገር ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያን ናፍቀው ኢትዮጵያ መግባት የማይችሉ በርካታ ዜጎች ነበሩ። በፖለቲካም ይሁን በያዙት የስደተኛ ወረቀት ምክንያት።

ስለዚህ ኢትዮጵያዊን ባይረግጡም ‹‹የኢትዮጵያን ኮፒ›› መርገጥ ይፈልጋሉ። በአውሮፓ የኢትዮጵያ ኮፒ ደግሞ ይህ ዓመታዊ አውደ ፌሽታ ብቻ ነው። በዚህ ምክንያት ዝግጅቱን እንደዋዛ አያዩትም።

በማንከሽከሻ የሚቆላ ቡና…እጅ የሚያስቆረጥም ቁርጥ…ምራቅ የሚያስውጥ ክትፎ፣ ከሸክላ የሚንቆረቆር አገርኛ ሙዚቃ…ከኢትዮጵያ ብዙ ሚሊየን ማይሎች ርቆ ለሚኖር ሰው ቀልድ አይደለም፡፡ መዝናኛ ብቻ አይደለም። አገር የመግባት ያህል ነው።

ለነዚህ ኢትዮጵያዊያ የአገርን፣ የአገር ልጅን ናፍቆትም ለመወጣት ሁነኛ ሥፍራ ይኸው መድረክ የሆነውም ለዚሁ ነው።

ጎረቤታሞች ቡና ሊጠራሩ ቀርቶ በማይተያዩበት፣ በሁለት ሦስት ሥራ ደፋ ቀና ካላሉ ሕይወት በማይገፋበት፣ ጥሬ ሥጋ መጉረስ ዜና በሚሆንበት አውሮፓ ኢትዮጵያዊያንን የሚያገናኘው ፌስቲቫል ከተጀመረ ዘንድሮ 17ኛ ዓመቱን ይዟል። አውሮፓ ውስጥ ኢትዮጵያውያን የሚገናኙበት ምናልባትም ብቸኛው ፌስቲቫል ነው።

ለዚህም ነው ጁላይ 31 እስከ ኦገስት 2! ብዙ ሺህ ኢትዮጵያውያን በቀን መቁጠሪያቸው ላይ በደማቅ ቀለም ያከበቡት። ቀኑ ሲደርስ ራቅ ካሉቱ እንደ ኖርዌይ እና ስዊዲን በጢያራ በረሩ። ቀረብ ካሉቱ ከጀርመን፣ ከፈረንሳይ፣ ከእንግሊዝ…በአውቶቡስ ተሳፈሩ፣ የባቡር ትኬት ቆረጡ፣ የመኪናቸውን ሞተር ቀሰቀሱ። ሆኖም ድንበር ሲደርሱ ስዊዘርላንድ ‹‹የማይደረገውን!?›› አለች።

ስዊዘርላንድ ከተቀሩት የአውሮፓ አገሮች የድንበሯን ነገር በዋዛ ባለመመልከት ትታወቃለች። በቂ የጉዞ ሰነድ የላቸውም ያለቻቸውን ኢትዮጵያዊያንን ወደመጡበት መልሳቸዋለች።

ከእነዚህ መካከል በዙሪክ ለመጫወት የተንቀሳቀሱት የፈረንሳዩ ኢትዮ-ማርሴይ የእግር ኳስ ቡድን እና ከኢትዮ-ፍራንክፈርት ሁለት ቡድኖች አንዱ፣ እንዲሁም የጀመርኑ ዳርምሽታት የእግር ኳስ ቡድን አባላት በከፊል ይገኙበታል።

አብዛኞቹ በሚኖሩበት አገር ጊዜያዊ የመኖሪያ ፍቃድ ተሰጥቷቸው የዜግነት ማረጋገጫ ወረቀት የሚጠብቁ ወይም የጥገኝነት ጥያቄ አቅርበው ምላሽ በመጠባበቅ ላይ ያሉ ወይም ጭርሱኑ ያላገኙ ናቸው።

የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ አሳየኸኝ ጥላሁን ለቢቢሲ እንደተናገሩት እንግሊዝ ከ40ሺ የሚልቁ ኢትዮጵያዊያን የሚገኙባት አገር ሆኖ ነገር ግን ይህ ፌስቲቫል እንግሊዝ የማይዘጋጅበት አንዱ ምክንያት እንዲህ ዓይነቱ ችግር እንዳያጋጥምና ኢትዮጵያዊያኑ እንዳይንገላቱ በመስጋት እንደነበር ያስረዳሉ።

‹‹ይህ ዝግጅት ለብዙ ኢትዮጵያዊያን ዓመታዊ የሥነ ልቦና ቴራፒ የሚያገኙበት ነው። በጉጉት የሚጠብቁት ነው፤ ከድንበር መመለሳቸው ያሳዘነን ጉዳይ ነው›› ይላሉ አቶ አሳየኸኝ።

ፌስቲቫሉ ሲጠነሰስና ዛሬ

ፌስቲቫሉ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር 2001 ላይ ሲጀመር ከአንድ ቀን የእግር ኳስ ግጥሚያ የዘለለ አልነበረም። 2003 ላይ ግን የቀድሞ እግር ኳስ ተጫዋቾች ማለትም ግርማ ሳህሌ፣ ዩሀንስ መሰለ፣ ከበደ ኃይሌና ሌሎችም፤ በተዋቀረ ሁኔታ የሚንቀሳቀስ ፌደሬሽን መመሥረታቸውን በአውሮፓ የኢትዮጵያውያን የባህልና የስፓርት ፌደሬሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዳንኤል ብስራት ይናገራል።

ፌስቲቫሉ በተጀመረበት ወቅት አውሮፓ ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እንደዛሬው አልተበራከቱም ነበር። የእግር ኳስ ቡድኖቹ በቂ ኢትዮጵያዊ ተጫዋች ስለማያገኙ አውሮፓውያንን ያካትታሉ። ያኔ ፌስቲቫሉ እንደዛሬው ብዙ ኢትዮጵያውያን ታዳሚዎችም አልነበሩትም።

"ከ2007 ወዲህ የሊቢያ መንገድ ሲከፈት ወጣቱ ግልብጥ ብሎ ወደ አውሮፓ መጣ። እዚያ የሚኖሩ ህጻናትም እያደጉ የእግር ኳስ ቡድኖችን መቀላቀል ጀመሩ። በጣም ጠንካራ ኳስ መጫወት የተጀመረው ከዚያ ወዲህ ነው" ይላል ዳንኤል።

ባለፈው ዓመት ፌስቲቫሉ የተካሄደው በጀርመኗ ስቱትጋርት ነበር። ከዚያ በፊት ሮም፣ ጄኔቭ፣ ስቶኮልም፣ አምስተርዳምና ሌሎችም የአውሮፓ ከተሞች ፌስቲቫሉን አስተናግደዋል።

አውሮፓ ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እግር ኳስ ተጫዋቾች ባቋቋሟቸው ቡድኖች መካከል የሚካሄድ የእግር ኳስ ግጥሚያ ፌስቲቫሉን ደማቅ ያደርገዋል። ዘንድሮ አበበ ቢቂላ፣ ሻላ እና ቡና የተባሉ የጤና ቡድኖች መቀመጫቸውን አውሮፓ ካደረጉት ቡድኖች ጋር ለመፋለም ከኢትዮጵያ ወደ ዙሪክ አቅንተዋል።

በስም ከሚታወቁት የቀድሞ ተጨዋቾች መካከል ሳሙኤል ደምሴ (ኩኩሻ)፣ ስንታየሁ ጌታቸው (ቆጬ)፣ ተክሌ ብርሃኔ፣ ቴዎድሮስ ቦካንዴ፣ ሃብቶም ብርሃኔ፣ ሰይፈ ውብሸት፣ ጌታቸው ካሳ (ቡቡ)፣ ኃይሉ አድማሱ (ቻይና)፣ግርማ ሳህሌ ይጠቀሳሉ። በነዚህ ጨዋታዎች በየዓመቱ ይገኛሉ።

በዘንድሮው የሦስት ቀን ፌስቲቫል ከአምስት ሺህ እስከ አስር ሺህ ሰዎች ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የፌስቲቫሉ አዘጋጅ የሆነው ኢትዮ-ዙሪክ ቡድን ፕሬዘዳንት ሙሉጌታ በየነ በመክፈቻው ዕለት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በፌስቲቫሉ ላይ ኢትዮጵያዊያን፣ ኤርትራዊያን እንዲሁም የኢትዮጵያን ባህል የሚወዱ የሌሎች አገሮች ዜጎችም ይገኛሉ። ኢትዮጵያዊያንን ያገቡ ዜጎች ይህ ዝግጅት ነፍሳቸው ነው።

ከሰሜን አሜሪካው ፌስቲቫል ቀጥሎ ኢትዮጵያዊያን ከኢትዮጵያ ውጪ የሚገናኙበት ፌስቲቫል እንደመሆኑ ፍቅርና አንድነትን የሚያስተጋቡ ሙዚቀኞች መጋበዛቸውን ሙሉጌታ ይገልጻል።

ዘንድሮ ጋሽ ማሕሙድና ስለሺ ደምሴ (ጋሽ አበራ ሞላን) ጨምሮ በርካታ ስመ ገናና ድምጻዊያን ሥራዎቻቸውን አቅርበዋል።

ፌስቲቫሉና የዳያስፖራ ፖለቲካ

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ራስ ምታት ከኢትዮጵያ ውጪ ለሚኖሩ ኢትዮጵዊያን ትኩሳት ይለቅባቸዋል።አሰላለፋቸው ያሸብራል። ልዩነታቸው የሀበሻ ሬስቶራንት ድረስ ይዘልቃል። የእንቶኔ ብሔር በቀነጠሰው በርበሬ የተሰራ ዶሮ ወጥ በአፌም አይዞር እስከማለት…

በፖለቲካ አሰላለፍ ጎራ ተለይቶ መራኮት ዕለታዊ በሆነበት አውሮፓ 'አንዲት ኢትዮጵያ' በሚል ፌስቲቫል ማዘጋጀት ምን ይመስል ይሆን? የየወቅቱ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ሁኔታስ ፌስቲቫሉ ላይ ጥላውን አላጠላም? ብለን አቶ ዳንኤልን ጠይቀነው ነበር።

"…ፖለቲካው ፌስቲቫሉን ሊያፈርስ የደረሰበት ወቅትም ነበር" ሲል መልሷል።

የእግር ኳስ ቡድኖች የመንግሥት ተቃዋሚና ደጋፊ በሚል እንደሚከፋፈሉ ካስታወሰ በኋላ በተለይ በምርጫ 97 ሰሞን የተካሄደውን የእግር ኳስ ግጥሚያ ያሸነፈው ቡድን አባላት በፖለቲካ አቋም ልዩነት ምክንያት አኩርፈው ዋንጫ ሳይቀበሉ ወደ መጡበት አገር መመለሳቸውን እንደ አብነት ያነሳል።

"ከፖለቲካ ጋር ግንኙነት ያላቸው መገናኛ ብዙኃን ሲመጡ እንደ ፌደሬሽን የማስተናገድ ግዴታ አለብን ስንል የሚቃወሙ አካላት አሉ። ሜዳ ላይ ያለውን መንፈስ ይረብሻል። እነ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ፣ ታማኝ በየነ፣ ተስፋዬ ገብረአብ ይመጡ ነበር። ያ አንዳንዶች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊፈጥር ይችላል። ግን ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የመምጣት መብት አለው። አትምጡ ልንላቸው አንችልም›› ይላል፤ ያም ሆኖ መድረኩ ከፖለቲካ የጸዳ የባህልና የስፖርት ፌስቲቫል ብቻ እንዲሆን አዘጋጆቹ ይተጋሉ።

ፌስቲቫሉን በየዓመቱ ማን ያዘጋጀው በሚለው ላይ ሁለት ተሞክሮዎች እንዳሉ አቶ ዳንኤል ያብራራል። እንደ ሰሜን አሜሪካው ውድድር ፌዴሬሽኑ ያሰናዳው ወይስ አዘጋጅ አገር?

2017 ላይ የፌስቲቫሉ አዘጋጅ ፌደሬሽኑ እንዲሆን ተወስኖ ጣልያን ውስጥ ፌስቲቫሉን ለማካሄድ መሰናዶ ተጀምሮ ነበር። ሆኖም የፌደሬሽኑ አመራሮች ከገንዘብ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ እሰጣ ገባ መፈጠሩን ይናገራል።

ከዚህ የሮሙ ክስተት በኋላ ፌስቲቫሉ በየዓመቱ በተለያዩ የእግር ኳስ ቡድኖች እንዲዘጋጅ ውሳኔ ተላለፈ። በዚህም መሠረት የዘንድሮውን ፌስቲቫል ያዘጋጀው ኢትዮ-ዙሪክ ቡድን ነው።

የኢትዮ ዙሪክ ቡድኑ ፕሬዝዳንት ሙሉጌታ፤ ፖለቲካው ለጊዜው እንዲቆይ ይማጸናል። ወደ ፌስቲቫሉ የሚሄዱ ሰዎች "ፖለቲካን ማሰብ የለባቸውም። እንዲያውም እዚያ ሜዳ ላይ ፌስቡክን አጥፍቶ፤ ሰላም ተባብሎ መጫወት፣ መብላት፣ መጠጣት፣ መሳቅን ነው ማየት የምንፈልገው" ሲል በበዓሉ መክፈቻ ዕለት ለቢቢሲ ምኞቹን አጋርቷል።

አማርኛ የሚኮላተፉ ሕጻናት በአውሮፓ

የኢትዮጵያ ባህል እና ስፖርት ፌስቲቫል አውሮፓ ውስጥ የተወለዱ የኢትዮጵያ ልጆች እነሱን ከሚመስሉ ልጆች ጋር የሚገናኙበትም መድረክ ነው። ብዙዎቹ ታዲያ በግማሽ ኢትዮጵያዊ ካልሆኑ ወላጆች የተገኙ ናቸው። በተለይ ኢትዮጵያን ረግጠው የማያውቁ የኢትዮጵያዊያን ልጆች በእናት በአባታቸው ቋንቋ እየተኮላተፉ ሲያወሩ መስማት አንዳች ልዩ ስሜት ያጭራል።

በየዓመቱ የሚጋበዙት ኢትዮጵያዊያን ሙዚቀኞች ታዳጊዎቹን ከአገሪቱ ባህል ጋር በመጠኑም ቢሆን ያስተዋውቋቸዋል። ‹‹ፌስቲቫሉ የአዋቂዎች ብቻ መሆን የለበትም፤ ለነዚህ ሕጻናት በቂ ትኩረት መሰጠት አለበት›› ይላል ለዚሁ መሰናዶ ዙሪክ የሚገኘው ጋሽ አበራ ሞላ።

የእግር ኳስ ተሰጥኦ ያላቸው ታዳጊዎች ዕድለኛ ከሆኑ ለተለያዩ አገራት ብሔራዊ ቡድኖችና ክለቦች ሊታጩ የሚችሉትም በዚሁ ፌስቲቫል ላይ ነው። በደቡብ አፍሪካ የአፍሪካ ዋንጫ ብሔራዊ ቡድናችን ላይ የተሰለፈው ዩሱፍ ሳሊህ ከዚሁ መድረክ የተገኘ ነው።

ፌስቲቫሉን ለመታደም በዙሪክ፣ ክሎተን ስቴድየም ከተገኙ ኢትዮጵያዊያን አንዷ የቀድሞዋ የኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቭዥን ጋዜጠኛ ቅድስት በላይ ናት።

በልጆች ክፍለ ጊዜ መርሀ ግብር የምትታወቀው ቅድስት የምትኖረው ስዊዘርላንድ ሲሆን፤ የኢትዮጵያዊያን ፌስቲቫል ላይ ስትሳተፍ የዘንድሮው የመጀመሪያዋ ነው።

ፌስቲቫሉ፤ አውሮፓ ውስጥ ተወልደው በምዕራባውያን ባህል የሚያድጉ ልጆች ስለ ኢትዮጵያ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ትናገራለች።

"ስብስቡ ማኅበራዊ ትስስሩን ያጠነክራል። ልጆችም በጣም ደስተኛ ይሆናሉ። ለምሳሌ የጓደኛዬ ቤተሰቦች ከኖርዌይ መጥተው ከሌሎች ልጆች ጋር ስለ ስዊዝና ኖርዌይ ባህል ሲያወሩ ነበር።"

ኢትዮጵያዊያን በብዛት በሌሉበት አካባቢ ለሚኖሩ ልጆች፣ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ በሚውለበለብበት፣ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች በሚነገሩበት፣ የኢትዮጵያ ባህላዊ ምግቦች በሚበሉበት ቦታ መገኘትን የሚተካ ነገር እንደሌለም ቅድስት ታስረዳለች።

ፌስቲቫሉን ማን ያስቀጥለው?

አውሮፓ በሮቿን ለስደተኞች ባትዘጋም ከጊዜ ወደ ጊዜ ሽንቁሩ እየጠበበ ይመስላል። ምናልባትም ለወደፊት ወደ አውሮፓ የሚሄዱ ኢትዮጵዊያን ቁጥር ያሽቆለቁል ይሆናል።

ይህ መላ ምት፤ አሁን በአውሮፓ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የጀመሩትን ፌስቲቫል ለወደፊት የሚረከባቸው ይኖራልን? የሚል ጥያቄ ማጫሩ አይቀርም።

ከኢትዮጵያዊያን እና ከሌሎች አገሮች ዜጎች የሚወለዱ ህጻናት እየተበራከቱ መጥተዋል። እነዚህ በከፊል ብቻ ኢትዮጵያዊ የሆኑ ልጆች ከኢትዮጵያዊ ማንነታቸው ጋር የሚያስተሳስራቸው ፌስቲቫል አስፈላጊነት የሚታያቸው እስከ መቼ ነው? ሌላው ጥያቄ ነው።

ዳንኤል የፌስቲቫሉ ቀጣይነት አያጠራጥርም ይላል። አንድም "በቀጣይ ለሚመጣው ትውልድ ብቸኛ መገናኛው ይህ ፌስቲቫል ነው" ሲል ያስረዳል።

በልጅነታቸው ወደ አውሮፓ ቢሄዱም የእግር ኳስ ፌደሬሽኑን ለዓመታት ያገለገሉ ወጣቶች መኖራቸውም ተስፋ ይሰጠዋል።

ዳንኤል፤ አውሮፓ ተወልደው ያደጉ ልጆች በፌስቲቫሉ ድምቀት በመማረክ ከዓመት ዓመት ቀጠሮ ሲይዙ አስተውሏል። ለነጭ ጓደኞቻቸው 'የኢትዮጵያ ፌስቲቫል ሄጄ ነበር' ብለው በኩራት እንደሚያወሩም ሰምቷል።

እነዚህ ልጆች አሁን ያለውን ሥርዓት እንዲረከቡ ከተደረገ የፌስቲቫሉ ዕድሜ እንደሚረዝም ያምናል።የቡናው መዓዛ ሳይጠፋ…እስክስታው ሳይለዝዝ፣ ቁርጡ ሳይወደር፣ ሙዚቃው ሳይጎትት የዛሬ ዐሥር፣ ሀያ፣ ሠላሳ ዓመት ኢትዮጵያዊያኑ ይገናኙ ይሆን? ከብዙ ፍቅርና ከትንሽ ቡጢ ጋ'ም ቢሆን…