ጄኔራል አብረሃ ወልደ ማርያም (ኳርተር) ማን ነበሩ?

መታመማቸው እምብዛምም ሳይሰማ ነው ሞታቸው የተሰማው፤ ከወደ ባንኮክ።
ምናልባትም አገሪቱ ሁለት ውድ ጄኔራሎቿን በአሰቃቂ መልኩ ያጣችበት ማግስት መሆኑ የጄኔራሉን የሞት ዜና ጎልቶ እንዳይወጣ አድርጎት ይሆን? እንጂማ የጄኔራል አብረሃ የትግል ታሪክ ደማቅም ዘለግ ያለም ነበር።
የትግል ጓዶቻቸው እነ ጄ/ል ታደሰ ወረደና ጀኔራል ቢተው በላይ ለቢቢሲ የመሰከሩትም ይህንኑ ነው።
ለመሆኑ ጄ/ል አብረሃ ለምን ኳርተር ተባሉ?
ጄኔራሉን የሚያውቁት ሰዎች የቅጽል ስማቸውን አመጣጥ እንዲህ ይተርካሉ።
በአንድ ወቅት ደቡብ ትግራይ ዋጅራት አካባቢ 12 የሚሆኑ የሕወሓት ወታደሮች እጅግ ተራቡ። የሚላስ የሚቀመስ ጠፋ። ታጋይ አብረሃ ተረኛ የሌሊት ጠባቂ ነበር። ተጨነቀ። ሌሊቱ ከመጋመሱ በፊት ከየትም ተሯሩጠው ሦስት እንጀራ ከአንዲት እናት አገኘና ለታጋይ ጓዶች «ዛሬ እንጀራ ኳርተር ኳርተር ነው የሚደርሰን» አለ። ሩብ እንጀራዋን ለ12 ጓዶቹ አከፋፈለ። ለዚያች የረሀብ ምሽት መታሰቢያ ጓዶቹ «ኳርተር» አሉት። አንድ አራተኛ እንደማለት። ቅጽል ስሙ የትግል ስሙ ሆነና በዚያው ጸና። እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ ከዋና ስሙ በላይ ኳርተር የሚለው ስሙ ገነነ።
በትግራይ ማዕከላዊ ዞን በእንዳባፃህማ ወረዳ እንዲጪዋ ቀበሌ ነሐሴ በ1953 ዓ.ም የተወለዱት ጀኔራል አብርሃም ይቺን ምድር ሲለዩ ዕድሜያቸው 58 ደርሶ ነበር።
ከተራ ወታደርነት የጀመረው የትጥቅ ትግል ታሪካቸው እስከ ጦር አዛዥነት በኋላም እስከ የዘመቻ መምሪያ ኃላፊነት አድርሷቸዋል።
ከደርግ ሥርዓት መወገድ በኋላ በመካከለኛና ከፍተኛ ኃላፊነቶች በጦር ሠራዊቱ ውስጥ ያገለገሉት ጄኔራል አብረሃ በርዋንዳ የሰላም ማስከበር ተልእኮ የመጀመርያው የጉና ሻለቃን በምክትል አዛዥነት የመሩትም እርሳቸው ነበሩ።

ጡረታ እስከሚወጡበት ቀን ድረስ በተለይም በቀደምው ጠቅላይ ሚኒስትር የመጨረሻ ወራት የኳርተር ስም በክፉም በበጎም ሲነሳ ቆይቷል። ጄኔራሉ በደቡብ ምሥራቅ እዝ ዋና አዛዥ በነበሩበት ወቅት ተፈጸሙ በሚባሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እጃቸው ነበረበት ብለው የሚከሷቸው ጥቂት አይደሉም።
የሂውማን ራይትስ ዎች የኢትዮ-ኤርትራ ተመራማሪ ፌሊክስ ሆርን ለቢቢሲ በሰጡት አጭር የድምጽ ማስታወሻ ስለ ጄኔራሉ ይህንን ብለዋል።
«ጄ/ሉ በምሥራቅ እዝ አዛዥ ሳለ ሠራዊቱ በኦጋዴን ነጻ አውጪ ላይ ጥቃት ሰንዝሯል። በዚያን ጊዜ በሠራዊቱ የጦር ወንጀሎች የሰብአዊ መብት ጅምላ ጥሰቶች ተፈጽመዋል። የጅምላ ግድያዎች ከመፈጸማቸውም በላይ ሴቶች ተደፍረዋል። በ2007/8 እና 9 ጄ/ሉ የሚመሩት ሠራዊቱ በዚህ ድርጊት ውስጥ ተሳትፎ ካደረገ በኋላ በክልሉ ልዩ ኃይል ወደ ማደራጀት ነው የተገባው። አብዲ ኢሌ የክልሉ ፕሬዝዳንት ከሆኑ በኋላ ልዩ ፖሊስም የተለያዩ ተመሳሳይ ሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሲፈጽም ነው የነበረው። ሂውማን ራይትስ ዎች በዚህ ረገድ በርካታ ሰነዶችን ሰንዷል።
እኔም በቅርቡ አካባቢው በነበርኩ ጊዜ እዚያ የተፈጸሙ ወንጀሎችን በተመለከተ ተጠያቂነት እንዲኖር ሕዝቡ ጥያቄ ሲያነሳ ነበር። ጄ/ል አብረሃ በሚመሩት ሠራዊት ስለተፈጸሙ የጅምላ ግድያዎች እንዴት ተጠያቂነት አይኖርም? እንዴትስ ምርመራ አይደረግም ሲሉ ነበር። ቢያንስ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ደረጃ ወንጀል ስለመፈጸሙ እንዴት አይገለጽም ሲሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ይህን ጉዳይ በስፋት አንስተውልኛል።"
ባልደረባችን ግርማይ ገብሩ ያነጋገራቸው በጄኔራሉ የቀብር ሥነ ሥርዓት ተገኝቶ ያነጋገራቸው ነባር ታጋይ ጄኔራል ታደሰ ወረደ በበኩላቸው ኳርተር በክልሉ ሰላምንና መረጋጋትን ያመጣ ቆፍጣና ወታደር ነበር ይላሉ።
«ጄኔራል አብረሃ የተሰጠውን ኃላፊነት ቆንጥጦ የሚሰራ፣ በእልህ የሚፈጽም ሰው ነበር። እሱ ግዳጅ ተሰጥቶት ያልፈጸመው ነገር የለም። የምሥራቅ እዝ አዛዥ ሳለ መደበኛ ያልሆኑ ዊጊያዎች ነበር የሚደረጉት ኦብነግንና አልሸባብ ጋር ነበር የሚታገለው። በተለይም በጸረ ሽምቅ ዉጊያዎች ክልሉን በማጽዳት ልማትንና መረጋጋትን ለማምጣት በኩል ትልቅ ሥራ ሠርቷል። አካባቢውን በጥሩ ሁኔታ ያረጋጋ እንደነበር ነው የማውቀው። ኳርተር ንቁ፣ ጥንቁቅና ተጠራጣሪ ሰው ነበር።»

ትምህርታቸውን ገታ አድርገው ወደ ትግል የገቡት ጄኔራል አብረሃ ከድል በኋላ ያቋረጡትን ትምህርት ቀጥለውበታል። በአዲስ አበባ ግንቦት 20 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከተማሩ በኋላ በአስተዳደር የመጀመርያ ዲግሪ በአመራር ሳይንስ ደግሞ ከግሪንዊች ዩኒቨርስቲ ሁለተኛ ዲግሪን አግኝተዋል።
አብረሃ ወ/ማርያም ኳርተር የሙሉ ጄኔራልነት ማዕረግ ያገኙት በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጊዜ ሲሆን በጡረታ የተሰናበቱት ደግሞ የጠ/ሚ ዐብይ አህመድን መምጣት ተከትሎ ነው።
ጄኔራል አብረሃ ለሁለት ሳምንት በአይደር ሪፈራል ሆስፒታል ተኝተው ታከሙ፤ አልተሻላቸውም። ለከፍተኛ ሕክምና ወደ ታይላንድ አቀኑ። ሰኔ 21፣ 2011 የሞታቸው ዜና ተሰማ።
የጄኔራሉ የቀብር ሥነ ሥርዓት በመቀሌ ካቴድራል ቅዱስ ገብርኤል ከጄራናል ሰዓረ መኮንንና ጄኔራል ገዛኢ አበራ ጎን ተቀብረዋል።
ጄኔራል አብረሃ የሁለት ወንድና የሁለት ሴት ልጆች አባት ነበሩ።
ዛሬ ለክብራቸው 15 ጊዜ መድፍ ተተኩሷል።












