የሰኔ 16ቱ ጥቃትና ብዙም ያልተነገረላቸው ክስተቶች

ወደ መሪነት መንበሩ ከመጡ ሦስት ወራት ያልሞላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ስልጣን ከተረከቡበት እለት ጀምሮ ባደረጓቸው ንግግሮችና በአጭር ጊዜ በወሰዷቸው ቁልፍ እርምጃዎች የበርካታ ኢትዮጵያዊያንን ድጋፍ ማግኘት ችለዋል።

ይህንንም አደባባይ ወጥቶ ለመግለጽ አንድ ኮሚቴ ተሰባስቦ ቅዳሜ ሰኔ 16/2010 ዓ.ም ሕዝባዊ ሰልፍ በመስቀል አደባባይ ለማድረግ ማቀዱን በመገናኛ ብዙሃን ያሳወቀው ሰልፉ ሊደረግ ቀናት ሲቀሩት ነበር። አንዳንዶች የጥድፊያ ዝግጅት በመሆኑ ላይሳካ ይችላል የሚል ጥርጣሬ አሳድረው ነበር።

ነገር ግን የሰልፉ አስተባባሪዎች ባደረጉት ርብርብ ከሰልፉ ቀን ቀደም ብሎ የአዲስ አበባና የአካባቢዋ ነዋሪዎች ለሰልፉ በስፋት እየተዘጋጁ መሆናቸውን የሚያሳዩ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ተስተዋሉ። የጠቅላይ ሚኒስትሩን ምስሎች የያዙ ካኒቴራዎችና የተለያዩ ህትመቶች የመዲናዋ ጎዳናዎች ላይ በስፋት ተሸጡ።

በሰልፉም ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚገኙ ስለተነገረ ቅዳሜ ሰኔ 16 በማለዳ ነበር የሰልፉ ታዳሚዎች ከተለያዩ የከተማዋ አቅጣጫዎች ወደ መስቀል አደባባይ መትመም የጀመሩት። በዚህም ከዝግጅቱ መጀመሪያ ሰዓት ቀደም ብሎ መስቀል አደባባይና አካባቢው በመቶ ሺዎች በሚቆጠሩ ሰዎች ተጥለቀለቀ።

በአደባባዩ ከተሰበሰበው የድጋፍ ሰልፉ ተሳታፊ አብዛኛው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምስል ያለበት ከነቴራና ምስላቸውን እንዲሁም እየወሰዷቸው ያሉትን እርምጃዎች የሚደግፉና ሚያሞግሱ ጽሁፎችን ይዞ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩም ዘወትር ከሚታዩበት ልብስ ውጪ ቀለል ያለ ልብስ ለብሰው ባርኔጣ ደፍተውና ጥቁር መነጽር አድርገው ከሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ጋር በመሆን አደባባዩ ሲደርሱ ተሰብሳቢው በሆታና በፉጨት ነበር የተቀበላቸው። እሳቸውም ከመድረክ ላይ ወደተለያየ አቅጣጫዎች እየተዘዋሩ ምስጋናቸውን አቀረቡ።

ከማለዳው ጀምሮ እየተካሄደ የነበረውን ይህንን ሰልፍ በሃገሪቱ የሚገኙ አብዛኞቹ የመገናኛ ብዙሃን የቀጥታ ሽፋን ሰጥተው በየሰከንዱ በመስቀል አደባባይ የሚከናወነውን ነገር ያቀርቡ ስለነበር፤ በርካታ ሰዎች ሰልፉን እንዲከታተሉ አስችሏል።

መስቀል አደባባይ ካስተናገዳቸው ሕዝባዊ ሰልፎች አንዱ የሆነው የዚህ ሰልፍ ታዳሚ ዋነኛ ጉዳይ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይም በደማቅ ሆታና ጭብጨባ የታጀበውን ሕዝቡን በማመስገንና የወደፊት ዓላማቸውን በማመላከት ላይ ያተኮረውን ንግግራቸውን ፈጽመው ወደመቀመጫቸው ከተመለሱ በኋላ አስደንጋጩ ነገር ተከሰተ።

ፍንዳታ

የመድረኩ አጋፋሪ መነጋገሪያውን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ተረክቦ በአማርኛ የተናገረውን በእንግሊዝኛ እየደገመ ሳለ እምብዛም ጉልህ ያልሆነ የፍንዳታ ድምጽ ጠቅላይ ሚኒስትሩና ባለስልጣኖቻቸው ካሉበት መድረክ አቅራቢያ ተሰማ። ነገር ግን በዚያው ቅጽበት ፍንዳታው ቦንብ መሆኑን ያወቁት በመድረኩ ላይና እዚው አቅራቢያ የነበሩት ብቻ ናቸው።

የፍንዳታው ድምጽ ወደተሰማበት አቅጣጫ ለመመልከት ጠቅላይ ሚኒስትሩና በዙሪያቸው የነበሩ ሰዎች ከመቀመጫቸው ተነስተው የነበረ ሲሆን በዚያው ቅጽበትም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠባቂዎች መሪውን ዙሪያቸውን በመክበብ እያጣደፉ ከመድረክ ይዘዋቸው በመውረድ ወደ መኪናቸው ወስደው ወደ ጽህፈት ቤታቸው አቀኑ።

ቦንቡ በፈነዳበት የመድረኩ አቅራቢያ ትርምስ በመፈጠሩ የጸጥታ ሰራተኞች ተሰማርተው ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ለመርዳት ጥረት ያደርጉ ነበር። ይህም ሆኖ ከመድረኩ እርቀው የነበሩ የሰልፉ ታዳሚዎችና በቴሌቪዥን ሲከታተሉ የነበሩ ሰዎች ግን ምን እንደተከሰተ አላወቁም ነበር።

በመድረኩ ላይ ይካሄድ የነበረውን ሥነ ሥርዓት በቀጥታ ሲያስተላልፉ ከነበሩት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች መካከል ቀዳሚው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የነበረ ሲሆን ከፍንዳታው መከሰት በኋላ ያቀርባቸው የነበሩት ምስሎች ከመድረኩ የራቁትን ብቻ ነበር።

የፍንዳታው ክስተት በማህበራዊ ሚዲያዎችና በሌሎች መገናኛ ብዙሃን በኩል ከተገለጸ በኋላ በአጠቃላይ በሕዝቡ ላይ በተለይ ደግሞ በአደባባዩ ታድመው በነበሩ ሰዎች ላይ ድንጋጤና ቁጣን ቀሰቀሰ። አንዳንዶችም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ጉዳት የደረሰ ስለመሰላቸው ስሜታዊ እስከመሆን ደርሰው ነበር።

ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ጽህፈት ቤታቸው በተመለሱ በደቂቃዎች ውስጥ በብሔራዊው ቴሌቪዥን ላይ ቀርበው ደህና መሆናቸውንና በቦንብ ጥቃቱ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን በማሳወቃቸው ወዳልታወቀ አቅጣጫ ሊያመራ የነበረው ቁጣ ጋብ ብሏል። ቢሆንም ግን በታዳሚው መካከል የተወሰኑት ከጥቃቱ ጋር ሊገናኙ ይችላሉ ባላቸው ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት አድርሰዋል።

ከፍንዳታው በኋላ

  • የቴሌኮምና የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት በመስቀል አደባባይና በአካባቢው ተቋርጦ ነበር። በዚህም የስልክ ግንኙነት ማድረግ አዳጋች ሆኖ ነበር።
  • በመስቀል አደባባይ የቦንብ ጥቃት መፈጸሙ ከተሰማ በኋላ ከቦታው ወደሌላ አካባቢ እንዲሁም ከሌላ አካባቢ ወደ አደባባዩ የስልክ ጥሪ ማድረግ ባለመቻሉ በርካቶች የድጋፍ ሰልፉን ለመታደም የሄዱ ሰዎች ደህንነትን ለማወቅ ስላልቻሉ ጭንቅ ውስጥ ገብተው ነበር።

ከቀናት በኋላም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት እንዳለው "የሰልፉ ሂደት እንዲስተጓጎል መብራት እንዲጠፋ እና የቴሌኮም ኔትወርክ የማቋረጥ ተግባር ተከናውኗል" ሲል ድርጊቱ የታሰበብት እንደሆነ አመልክቷል።

  • በእለቱ የድጋፍ ሰልፉን በቀጥታ ያስተላልፉ ከነበሩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች መካከል ዋነኛው ብሔራዊው ቴሌቪዥን ኢቲቪ ነበር። ጣቢያው ከመስቀል አደባባይ የተለያዩ ስፍራዎች ምስሎችን እያሳየ የነበረ ቢሆንም ከፍንዳታው በኋላ ግን የተወሰኑ ካሜራዎቹ ምስል ማስተላለፍ እንዳልቻሉ በስፍራው የነበረ የጣቢያው ባልደረባ ለቢቢሲ ተናግሯል።
  • ለዚህም ምክንያቱ በኋላ ላይ እንደተረጋገጠው የካሜራዎች ገመዶች ባልታወቁ ሰዎች በመቆረጣቸው እንደሆነ እንዲሁም በካሜራዎች ላይ ጉዳት በመድረሱ ነበር። ጥቃቱ ከተከሰተ በኋላ ስሜታዊ የሆኑ የሰልፉ ታዳሚዎች በፍንዳታው በጠረጠሯቸው ሰዎች ላይ ድብደባ ፈጽመዋል። ፖሊስም ይህንን ለማስቆም ጣልቃ ገብቷል። ተሽከርካሪዎች ላይም ጥቃት ደርሷል።
  • ከፍንዳታው እለት ከሰዓት በኋላ አንስቶ ባሉት ተከታይ ቀናት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ሆስፒታል በመሄድ ጠይቀዋል፤ በተጨማሪም የድም ልገሳ አድርገዋል።
  • በተከታይነትም ኃላፊነታቸውን አልተወጡም ፤ በድርጊቱ እጃቸው አለበት ተብለው የተጠረጠሩ የፖሊስና የደኅንነት ኃላፊዎችና ሰራተኞች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ።
  • የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት እየተካሄዱ ያሉ ለውጦችን ለማደናቀፍ እየተፈፀሙ ያሉ ሴራዎችን የሚመረምሩና ድርጊቶቹን በማጣራት ለህግ የሚያቀርብ ኮሚቴ መቋቋሙን አስታወቀ።
  • የሃገር ውስጥ የደኅንነትና የጸጥታ ተቋማት የሚያደርጉትን ምርመራ ለማገዝ አሜሪካው ውስጥ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በመከላከልና በመመርመር የታወቀው ኤፍቢአይ ባለሙያዎችን መላኩ ተገልጿል።

በዚህ ዓመት ኅዳር ወር መጀመሪያ ላይም የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ ይፋ እንዳደረጉት የቦምብ ጥቃቱ በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የቀድሞ ኃላፊ የተመራ ነው።

አቃቤ ሕጉ ጨምረውም ጥቃቱ ሃገር ውስጥና በውጭ ሃገር ባሉ ኃላፊዎች በቅንጅት መፈጸሙንና ኬንያ ውስጥ ያለችና ያልተያዘች አንዲት ግለሰብም በጥቃቱ ቁልፍ ሚና እንደነበራት ጠቅሰዋል።

በወቅቱ በትንሹ ለሁለት ሰዎች መሞትና ለበርካታ ሰዎች የአካል ጉዳት ምክንያት ለሆነውና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ጉዳት ቢደርስ ኖሮ ከባድ ምስቅልቅልን ሊያስከትል ይችል በነበረው የሰኔ 16ቱ የቦንብ ጥቃት በርካታ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ይገኛል።