ፌስቡክ የሞቱ ሰዎችን ገፅ ለማስተዳደር አዲስ አሰራር ቀየሰ

ሼሪይል ሳንድበርግ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የፌስቡክ አካውንት ያላቸው ግለሰቦች ከሞቱ በኋላ አንዳንድ ማሳወቂያዎች ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጆቻቸው መድረሱ ብዙዎቹን ማሳዘኑና ማበሳጨቱን ተከትሎ ፌስቡክ መፍትሄ አግኝቻለሁ ብሏል።

ኩባንያው እንዳሳወቀው አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን (ሰው ሰራሽ ንቃተ ህዋስን) በመጠቀም የሞቱ ሰዎችን ልደት ወይም የተለያዩ ዝግጅቶችን ለመጋበዝ የሚመጣውን ማሳወቂያ ያቆመዋል ተብሏል።

በሟቾቹም የፌስቡክ ገፅ ላይ ሰዎች የፃፏቸው የሀዘን መልዕክቶች ለብቻ ተከፍለው ፤ ገፃቸው ማቾቹ እንደተውት ተደርጎ እንደሚቀመጥ ኩባንያው አሳውቋል።

"ፌስቡክ ያጣናቸውን ግለሰቦች ትዝታቸውና መንፈሳቸውን የምናስታውስበትና ህያው የሚያደርግ መድረክ እንደሚሆን ተስፋ አለኝ" በማለት የፌስቡክ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሼሪል ሳንድበርግ ተናግራለች።

በተለያዩ ጊዜዎች ከሞቱ ሰዎች ጋር ግንኙነት እንዲፈጥሩ ፌስቡክ መልዕክት እንደሚልክላቸው በማስታወቅ ብዙዎች ቅሬታ ሲያቀርቡ ይሰማል።

ከጎርጎሳውያኑ 2009 ዓ.ም ጀምሮ ፌስቡክ ለሟች ቤተሰቦቻቸውና ወዳጆቻቸው የማቾችን ስም በመጠቀም ማስታወሻ እንዲፅፉ የሚያስችል ስርአት መዘርጋቱን ተከትሎም በየወሩ 30 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ይፅፋሉ (ፖስት ያደርጋሉ)።

ገፁ እንደማስታወሻነት ከተጠቀሙበት በኋላ ግን በህይወት እንዳሉ ሰዎች ማስታወቂያ መላክ እንዳይችል የሆነ ሲሆን ነገር ግን በማስታወሻነት ያልተጠቀሙበት የማቾች ፌስቡክ ገፆችን ግን አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን በመጠቀም እንደሚያስተካክሉት አስታውቋል።

ከዚህም በተጨማሪ ፌስቡክ እንዳሳወቀው የማስታወሻ የፌስቡክ ገፆቭ ማስታወሻ የሚል ክፍል ለብቻው የሚኖር ሲሆን ይህም የሟቾችን የፌስቡክ ገፃቸውን (አካውንታቸው) ምንም ሳይነካ ማስታወሻዎችንና የሀዘን መግለጫዎችን መፃፍ የሚያስችል ነው።

የሚፃፉ ማስታወሻዎችን የሚቆጣጠሩት ተወካያቸው ሲሆን፤ ይህም የፌስቡክ ገፃቸውን ከሞቱ በኋላ እንዲቆጣጠርላቸው በሚያምኑትና በሚተኩት የሚሰራ ይሆናል።

ማን ፖስት እንደሚያደርግና የአርትኦት ስራውን የሚሰራውን ሟች የወከለው ተተኪ ሰው ይሆናል።

ከአስራ ስምንት አመት በታት የሆኑት የሚወክላቸውን ሰው የማይመርጡ ሲሆን አሳዳጊዎችና ቤተሰቦች ግን ፌስቡክን መጠየቅ እንደሚችሉ ተጠቅሷል።

እንደዚህ አይነት ለውጦች ተግባራዊ እንዲሆኑ የተደረጉትም በአንዳንድ አጋጣሚዎች ሰዎች ለቀልድ በሀሰተኛ መንገድ ግለሰቦች እንደሞቱ አድርገው ለፌስቡክ ሪፖርት ማድረጋቸውን ተከትሎም እንደሆነ ተጠቅሷል።