ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሥመራ፡ ከመኪኖች ይልቅ ብስክሌቶች የሚበዙባት ከተማ
ጦርነትና ከዓለም መድረክ መነጠልን ጨምሮ በሌሎችም በርካታ ምክንያቶች ታስቦባቸው ባይሆንም ኤርትራን ለብስክሌትና ለብስክሌተኞች ምቹ ስፍራ እንድትሆን አድርጓታል።
አሥመራ 500 ሺህ ብቻ ነዋሪዎች ሲኖሯት ዝቅተኛ ደሞዝ፣ ከፍተኛ ቀረጥና የነዳጅ እጥረት ከተማዋ ትንሽ ተሽከርካሪ እንዲኖራት ምክንያት ናቸው። ብዙ ጊዜ የሚታዩት ሰዎችም በተለየ የእድሜ ክልል ውስጥ ናቸው።
የአሥመራ መንገዶች በአንፃራዊነት ከመኪና ብቻ አይደለም ነፃ የሆኑት። ሃገሪቱ ዜጎች እንደሚሉት ኤርትራዊያን ባለፉት 20 ዓመታት አካባቢያዊ ግጭት በፈጠረው ጫናና የግዳጅ ብሔራዊ አገልግሎትን ሸሽተው በርካታ ወጣቶች ሃገራቸውን ጥለው ተሰደዋል።
አሥመራ በተለያዩ ምክንያቶች በመኪና ከተጨናነቁ ሌሎች የአፍሪካ ከተሞች የተለየ መልክ አላት። ይህ አስገራሚ ከሆነው የከተማዋ አየር ንብረት ጋር ተጨምሮ ብስክሌተኞች በከተማዋ እንዲያንዣብቡ ድንቅ ስፍራ ሆናለች። የ25 ዓመቱ ወጣትም "ብስክሌት መጋለብ አንዱ ባህላችን ሆኗል" በማለት ይገልፃል።
የአሥመራ የኪነ ሕንፃ ስብስብም በቅርብ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት የተመዘገበ ሲሆን እ.አ.አ. ከ1897 እስከ 1943 የቆየው የጣልያን ቅኝ ግዛት ትሩፋቶች ነው።
የብስክሌት መጠገኛ ሱቆች አሥመራ ውስጥ በስፋት ይገኛሉ። ከ30 ዓመታት ጦርነት በኋላ ከኢትዮጵያ ተነጥላ ሉዓላዊት ሃገር የሆነችው ኤርትራ ከነጻነት በኋላ በገጠማት ከዓለም አቀፍ ግንኙነት መገለል ምክንያት ብስክሌትም ሆነ የመለዋወጫ አካላትን ወደ ሃገሪቷ ማስገባት እጅግ በጣም ውድ እንዲሆን አድርጎታል።
ኤርትራዊያን በቀለምም ሆነ በዓይነታቸው የተለያዩ ዓይነት ብስክሌቶችን ይነዳሉ። የተራራ ብስክሌቶች፣ የከተማ ብስክሌቶችና የውድድር ብስክሌቶች ይጠቀሳሉ። ኤርትራዊያን ከህፃን እስከ አዋቂ፣ ሴቶችና ወንዶች፣ አትሌቶችና የቤት እመቤቶች ሁሉም ብስክሌትን ተላምደዋል።
የህዝብ አውቶብስ የሚጠቀሙ ነዋሪዎች ከመጠን በላይ የተጨናነቀው አውቶብስ ላይ ከመግባታቸው በፊት ለረጅም ሰዓታት ቆመው መጠበቅ አለባቸው። "አውቶብሶች በጣም ጥቂትና ያገጁ ናቸው። በአስመራ ብስክሌት ህይወትን ነው የሚያድነው" ትላለች የ30 ዓመቷ ሰላም።
መንግሥት የአካባቢ ጥበቃን ለረጅም ጊዜ ሲቀሰቅስ ቆይቷል። የፕላስቲክ ምርትንና አጠቃቀምን መቀነስ፣ ደንን ማልማት፣ የሃገሪቷን አረንጓዴ ቦታዎች መንከባከብና የቻይናና የዱባይ ብስክሌቶችን መጠቀም ከወሰዳቸው አንዳንድ እርምጃዎች መካከል ናቸው።
ለብዙ ኤርትራዊያን መኪኖች ቢኖሩ እንኳን እንደ ብስክሌት ዋጋ ተመጣጣኝ አይደሉም።
ከኢትዮጵያ ጋር በቅርብ በተደረገው የሰላም ስምምነት አማካኝነት ድንበሩ በ20 ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ተከፍቷል። አሁን ርካሽ የኢትዮጵያ ሸቀጣ ሸቀጦች በሃገሪቷ ሙሉ ይሸጣሉ፤ ይህም የኑሮ ውድነቱን እያቀለለ ነው።
የግጭት፣ ከዓለም መገለልና የተባበሩት መንግሥታት ማዕቀብ ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ ባለፈው ህዳር ቢያበቁም፤ በኤርትራ አሁንም የብዙ ምርቶች እጥረት አለ። የነዳጅ እጥረት መኪኖች ለረጅም ሰዓታት እንዲቆሙ በማድረግ ሰዎች በእግራቸው ከመሄድና ብስክሌት ከመንዳት ሌላ ብዙ ምርጫ እንዳይኖራቸው አድርጓል።
ብስክሌት መንዳት በኤርትራዊያን ዘንድ በጣም የታወቀ ስፖርት ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ በጣልያዊያን የተዋወቀው የብስክሌት ውድድር ለኤርትራ ህዝብ የኩራት ምንጭ ነው። ሞሳና ድበሳይን ያካተተው የሃገሪቱ ብሔራዊ ቡድን በዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች በጣም ስኬታማ ነው።
በቅርብ ከኢትዮጵያ ጋር የተደረገው ግንኙነት ብዙ ኤርትራዊያን የሃገራቸው ኢኮኖሚ በፍጥነት እንደሚያድግና የዕለት ከዕለት ኑሯቸውን እንደሚያቀልላቸው ተስፋ ያደርጋሉ።
በአንትሮፖሎጂስት ሚሊና ቤሎኒ እና በጋዜጠኛ ጄምስ ጄፍሪ