ባለዋሽንቱ ዮሐንስ አፈወርቅ ሲታወሱ

ዮሐንስ አፈወርቅ

የፎቶው ባለመብት, EBC

'ፍቅር እስከ መቃብር' ሲታወስ ለሰብለወንጌልና በዛብህ ልቦለዳዊ ታሪክ ህይወት የዘራው የወጋየሁ ንጋቱ አተራረክ አይዘነጋም። ሌላው መጽሐፉ ከብዙዎች ህሊና እንዳይጠፋ ያደረገው የዮሐንስ አፈወርቅ የዋሽንት ዜማ ነው።

በርካቶች 'ፍቅር እስከ መቃብር'ን ሲያነሱ ዮሀንስን፤ የዮሐንስን የዋሽንት እንጉርጉሮ ሲሰሙ የሀዲስ አለማየሁን 'ፍቅር እስከ መቃብር'ን ያስባሉ።

"አባቴ 'ፍቅር እስከ መቃብር' ላይ ህይወት ዘርቷል"

አፈወርቅ ዮሐንስ፣ የባለ ዋሽንቱ ዮሀንስ አፈወርቅ ልጅ ነው።

አባቱ የ'ፍቅር እስከ መቃብር' ማጀቢያ የሆነውን ሙዚቃ ሲሠሩ አልተወለደም ነበር። መጽሐፉ በኢትዮጵያ ራዲዮ ሲተረክ ይንቆረቆር የነበረው ጥዑም ሙዚቃ የአባቱ መሆኑን አወቀ።

"ሙዚቃው የእሱ መሆኑን ሲነግረኝ እኔ ብቻ ሳልሆን ሁሉም ቤተሰብ ስሜቱን መቆጣጠር አልቻለም። ያን ሙዚቃ የተጫወተው በሚያስደንቅ ሁኔታ ነበር።"

አባቱ ሙዚቃውን እንዴት እንደተጫወቱ የነገሩትን ታሪክ ዛሬም ያስታውሳል።

ይህ በዋሽንት የተሰራው ማጀቢያ ሙዚቃ አባቱ በተወለዱበት ጎጃም ይሰሟቸው የነበሩ ሙዚቃዎችን እያሰቡ የሠሩት ሙዚቃ ነው። እንዲህ ይሁን፤ እንዲያ ይሁን ብለው ወጥነው የሠሩት ሳይሆን ስሜታቸውን የተከተሉበት ሙዚቃ ነበር።

"ድርሰቱን ሀዲስ አለማየሁ ሲጽፉት ነፍስ የዘሩበት ወጋየሁና የዮሐንስ ዋሽነት ናቸው። ከሕዝብ ህሊና ሳይጠፋ የቆየውም ለዚያ ይመስለኛል"

አፈወርቅ በአባቱ የሕዝብ ለሕዝብ ተሳትፎም ኩራት ይሰማዋል።

ሙዚቀኛው ዋሽንት መጫወት የጀመሩት ልጅ ሳሉ ነበር። ቤተሰቦቻቸው ዋሽንት እንዳይጫወቱ ሲከለክሏቸው ከጎጃም ወደ አዲስ አበባ ኮበለሉ።

ከዚያ በኋላም በኦርኬስትራ ኢትዮጵያ እንዲሁም በአገር ፍቅር ቴአትር ደማቅ አሻራቸውን ማኖር ችለዋል። ዘለግ ላለ ሰዓት መድረክ ላይ ዋሽንት በመጫወት ተወዳዳሪ አልነበራቸውም።

"ሁሌም ከልቤ የማይጠፋው በሠራው ነገር ተጠቃሚ አለመሆኑ ነው። ሕዝብን አስደስቷል፤ ሀገሩን ጠቅሟል። የሙዚቃ ፍቅሩ የተለየ ስለነበረ በነጻም ይሠራ ነበር።"

ዮሐንስ ከስኳር ህመምና ከደም ግፊት ጋር ለዓመታት ታግለዋል። በስተመጨረሻ አይናቸውን ጋርዷቸው ነበር። ከመስከረም ጀምሮም ከቤት መውጣት እንዳልቻሉ ልጃቸው ይናገራል።

የካቲት 18 ቀን 2011 ዓ. ም በ72 ዓመታች ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ሙዚቀኛው የካቲት 19 ቀን 2011 ዓ. ም በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን ስርዐተ ቀብራቸው ተፈጽሟል።

አፈወርቅ ዮሐንስ ካፈሯቸው አምስት ልጆች አንዱ ነው። ዮሀንስ ልጆቻቸው ትምህርት ገፍተው እንዲማሩ ቀን ከሌት መሥራታቸውን ይናገራል።

"እሱ ትምህርቱን ሳይገፋበት እኛ አንድንማር መከራውን አይቷል። ለሊት ሁሉ እየሠራ እዚህ ያደረሰን ልዩ አባታችን ነበር።"

ባለ ዋሽንቱ ዮሐንስ

የፎቶው ባለመብት, EBC

የምስሉ መግለጫ, ባለ ዋሽንቱ ዮሐንስ

"ዮሐንስ ምትክ የለውም"

ዮሐንስ አፈወርቅ በባህላዊ ሙዚቃ ዘርፍ በግንባር ቀደምነት ከሚጠቀሱ ሙዚቀኞች አንዱ ናቸው።

የሙዚቃና ቴአትር ሙያተኛው ተስፋዬ አበበ "ዋሽንት ከኢትዮጵያ ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያዎች ከባዱ ነው" ይላሉ።

"ዋሽንት ትንፋሽ ይጠይቃል። አለስልሶ ለመጫወትም ብቃት ይጠይቃል። ዮሐንስ በዚህ በኩል አንቱ የተባለ ነው፤ ምትክ የለውም።"

ዮሐንስ ኦርኬስትራ ኢትዮጵያ በነበሩ ጊዜ 'ሶሎ' ሲጫወቱ የተስተዋለውን ጥበብ ተስፋዬ ያስታውሳል። ትዝታ፣ አምባሰል፣ ባቲ. . . የኢትዮጵያ ቅኝቶችን በረቀቀ ሁኔታ ያስደምጡ ነበር።

ተስፋዬ አንጋፋ የጥበብ ሰዎች ከሞቱ በኋላ ሳይሆን ሳያልፉ በፊት ላበረከቱት አስተዋጽኦ መመስገን አለባቸው ይላል።

"ዮሐንስን የሚያህል የሙዚቃ ጠበብት ጡረታ መውጣት የለበትም ነበር። እዚያው ማዘጋጃ ቤት ሳለ ሌሎቹን እያስተማረ ምትክ አፍርቶ መውጣት ይችል ነበር። ነገር ግን 'መቼ ጡረታቸው በደረሰ' እያሉ ያሰናብቷቸዋል። ይሄ ልክ አይደለም።"

"ዮሐንስን የተዋወቅኩት ሙዚቃውን የስልኬ መጥሪያ አድርጌ ነበረ"

ዛሬ ዛሬ በባህላዊ ሙዚቃ ዘርፍ ስማቸው እየገነነ ከመጡ የባህላዊ ሙዚቃ ባንዶች 'መሶብ' አንዱ ነው።

ዮሐንስ የመሶብ የባህል ሙዚቃ ቡድን መስራች ለሆነው ዋሽንት ተጫዋቹ ጣሰው ወንድም የሙዚቃ ህይወቱ መሰረት ከጣሉ ቀዳሚው ናቸው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያሳተመው አልበም ላይ ዮሐንስ አፈወርቅ ዋሽንት የሚጫወቱባችን ሙዚቃዎች ደጋግሞ ሰምቷል። እንደ ሙዚቀኛ ህይወቱን የቀየረው ግን የ 'ፍቅር እስከ መቃብር' ማጀቢያ ሙዚቃ ነው።

ይህን ሙዚቃ በዋሽንት ተጫውቶ፣ ድምጹን ቀድቶ የስልኩ መጥሪያ ድምጽ አድርጎት ነበር። አንድ ቀን አገር ፍቅር ቴአትር ቤት ውስጥ ስልኩ ሲጠራ አንድ ሰው ይህ ሙዚቃ የማን ነው? ብለው ይጠይቁታል።

ሙዚቃው በጣም የሚያደንቃቸው ዋሽንት ተጫዋች ዮሐንስ አፈወርቅ እንደሆነ ይነግራቸዋል። እሱም ዋሽንት ተጫዋች እንደሆነ ይገልጽላቸዋል።

ፊታቸውን አይቶ ማን እንደሆኑ እንዳላወቀ የተረዱት ግለሰብ "ዮሐንስ አፈወርቅ እኮ እኔ ነኝ" አሉት።

ጣሰው ያን ቅጽበት አይረሳውም። ዮሐንስ በዋሽነት አጨዋወቱ ላይ የሰጡትን አስተያየትም አይዘነጋም።

"የኢትዮጵያን ቀለም ሳይለቅ ዋሽንትን አሟልቶ ነበረ የሚጫወተው። በሚገርም ፍጥነት በጣቶቹ ሲጫወት ዜማ አይስትም። የእሱ አይነት አጨዋወት የለም ማለት እችላለሁ።"

ጣሰው ዋሽንትን ወደ ባንድ ሙዚቃ ለመቀላቀል ሲሞክር የዮሐንስን ሙዚቃ መነሻ አድርጎ ነበር። መሶብ ባንድ 'ጥሞና ' የተሰኘ አልበም ሲያሳትም መታሰቢያ ካደረገላችው አራት ሙዚቀኞች አንዱ ዮሐንስ አወርቅ አንዱ ናቸው።

"የእሱ አጨዋወት ትልቅ ደረጃ ላይ ያለ ስለሆነ የእሱን ፈለግ ተከትያለሁ" ይላል።

ሙዚቀኛው ዮሐንስ አፈወርቅ በባህላዊ ሙዚቃ ዘርፍ ገናና ናቸው

የፎቶው ባለመብት, EBC

የምስሉ መግለጫ, ሙዚቀኛው ዮሐንስ አፈወርቅ በባህላዊ ሙዚቃ ዘርፍ ገናና ናቸው

"ዮሐንስ ኢትዮጵያን ለዓለም አስተዋውቋል"

ዮሐንስ አፈወርቅ እድሜያቸው ከገፋ በኋላም ከሙዚቃው መድረክ አልጠፉም። ከወጣት ሙዚቀኞች ጋርም በጥምረት ይሠሩ ነበር።

'ኢትዮ ከለር' በተወዛዋዡ መላኩ በላይ የተመሰረተ የባህል ሙዚቃ ቡድን ሲሆን፤ ወጣትና አንጋፋ ሙዚቀኞችን በጋራ መድረክ ላይ በማቅረብ ይታወቃል።

ከዮሐንስ ጋር በአንደ መድረክ የተጫወተው መላኩ በላይ፤ ዮሐንስን የሚያስታውሳቸው ዋሽንትን የላቀ ደረጃ በማድረሳቸው ነው።

"የሸምበቆ መሳሪያው ዋሽንት ተንቆ በግለሰብ ደረጃ ብቻ የሚጫወቱት ተብሎ ነበር። እሱ ግን ዋሽንት ከባንድ ጋር ተቃኝቶ እንዲቀርብ አድርጓል።"

ዮሐንስ የኢትዮጵያ ባህላዊ ሙዚቃን ከማሳደግ ባለፈ በዓለም አቀፍ ደረጃ ማስተዋወቃቸውን ይናገራል። ለዓመታት ከዮሐንስ አፈወርቅ ጋር መሥራት ከማያልቅ እውቀታቸው መቅሰም መሆኑን ያወሳል።

"ሰዓት ላይ ጥንቁቅ ነበረ፤ ቀድሞን ይደርሳል። በሥራው አመስጋኝ ነበር። ከክፍያው በላይ ሥራው ላይ ያተኩራል፤ ሥራውን ይወዳል።"

መላኩ እንደሚለው አዝማሪዎች እንዲሁም ዋሽንት ተጫዋቾች ሙያው ትልቅ መሆኑን በዮሐንስ ስኬት ውስጥ አይተዋል።

"እረኞችን ዋሽንት ለካ እንደዚህ እውቅና ያሰጣል አስብሏል። አልበም ማውጣትም ይቻላል የሚል ተስፋ የሰጠ፣ ብዙዎችን ያነቃቃም ሙዚቀኛ ነበረ።"