ከቤተሰቦቿ አምልጣ ካናዳ የገባችው የሳዑዲዋ ወጣት፡ 'ምንም የሚጎልብኝ የለም'

ራሃፍ ሞሐመድ አል-ቁኑን ከሶስት ቀናት በፊት ካናዳ መግባቷ ይታወሳል

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ራሃፍ ሞሐመድ አል-ቁኑን ከሶስት ቀናት በፊት ካናዳ መግባቷ ይታወሳል

ከቤተሰቦቿ አምልጣ በካናዳ ጥገኝነት ያገኘቸው የሳዑዲዋ ወጣት ራሃፍ ሞሐመድ አል-ቁኑን ''የወሰድኩት እርምጃ አደገኛ ቢሆንም ትክክለኛ ውሳኔ ነው'' በማለት በካናዳ ነጻነት የሞላበት ህይወት እንደምትጀምር ተናግራለች።

የ18 ዓመቷ ወጣት ከቀናት በፊት ነበር ከቤተሰቦቿ ጋር በጉዞ ላይ ሳለች ወደ አውስትራሊያ ለማምለጥ በማሰብ ባንኮክ ከተማ በሚገኝ ሆቴል ውስጥ እራሷ ላይ በመቆለፍ ወደ ሳዑዲ አልመሰም ያለችው።

ራሃፍ በትዊተር ገጿ ላይ በምትለቃቸው ተንቀሳቃሽ ምስሎች የእስልምና ሀይማኖትን መካዷን እና ወደ ሳዑዲ ብትመለስ ጨቋኝ ናቸው የምትላቸው ቤተሰቦቿ ሊገድሏት እንደሚችሉ የተናገረችው።

የወሰድኩት እርምጃ አደገኛ እንደሆነ ይገባኛል ይሁን እንጂ ትክክለኛ ውሳኔ ነው። ምንም የሚጎድልብኝ ነገር አይኖረም ስትል ቶሮንቶ ስታር ለተሰኘ ጋዜጣ ተናግራለች።

''የህይወት ታሪኬን እና የሳዑዲ ሴቶች የሚደርስባቸውን በደል በይፋ መናገር እፈልጋለሁ። እንደ እቃ ነው የምንቆጠረው፤ እንደ ባሪያ።'' ብላለች ራሃፍ።

"ይህ ይሆናል ብዬ በጭራሽ አላሳብኩም ነበረ። የሰው ልጆች መብት በሚከበርባት ካናዳ ደህንነቴ እንደተጠበቀ ይሰማኛል።'' ስትልም ተናግራለች።

ራሃፍ ከወላጆቿ ጋር ወደ ኩዌት እየተጓዘች ሳለ ነበር የአውስትራሊያ ቪዛ እንዳላት በመናገር በባንኮክ አድርጋ ወደ አውስትራሊያ ለመግባት ከወላጆቿ ያመለጠችው።

ይሁን እንጂ ባንኮክ አየር ማረፊያ እንደደረሰች የሳዑዲ ዲፕሎማት ፓስፖርቴን ስለቀማኝ ጉዞዬን መቀጠል አልቻልኩም ብላ ነበር። ወንድሟና አባቷ ራሃፍን ወደ ሳዑዲ ለመመለስ ባንኮክ አየር ማረፊያ ድረስ ሄደውም ነበር።

ራሃፍ ባንኮክ የሆቴል ክፍል ውስጥ እራሷ ላይ ቆልፋ፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የተለያዩ ሀገራት መንግሥታት እንዲታደጓት ጥሪ አቅርባ ነበር።

የወጣቷ ጉዳይ የበርካቶችን ቀልብ ስቦ ነበረ። የታይላንድ መንግሥት በባንኮክ እንድትቆይ ፍቃድ ሰጥቶ የነበረ ሲሆን፤ የተባበሩት መንግሥታትም የጥገኝነት ጥያቄዋን ሲያስፈጽምላት ነበረ።

ካናዳ ለራሃፍ ጥገኝነት በመስጠቷ ወጣቷ ከሦስት ቀናት በፊት ቶሮንቶ ገብታለች። በቶሮንቶ አውሮፕላን ማረፊያ የካናዳ የውጪ ጉዳይ ሚንስትርን ጨምሮ በርካታ ደጋፊዎቿ አቀባበል አድርገውላታል።

ራሃፍ አል-ቁኑን የሚለውን የቤተሰብ ስሟን ከዚህ በኋላ እንደማትጠቀምበት አስታውቃለች።