ጥቁር ለመሆን የሚጥሩት ነጭ እንስቶች

የፎቶው ባለመብት, AGA BRZOSTOWSKA/JAIDEN GUMBAYANA
«ቀዶ ጥገና አልተደረግኩ፤ ከናፍሬን ላስወገዳቸው አልችል። በቀዶ ጥገና ያገኘሁትን መቀመጫም ፍቄ ልጥለው አልፈቅድም።»
በፈረንጅ አፍ 'ብላክፊሽ' ሲሉ ይጠሯታል፤ ጥቁር ለመሆን የማትፈነቅለው ድንጋይ እንደሌለ ያስተዋሉ።
ቃሉ ማሕበራዊ ድር-አማባዎችን ተጠቅመው ባለጥቁር ወይንም ቅልቅል ደም ያለበት ቆዳ ለመላበስ የሚጥሩ ሰዎችን ለመግለፅ ጥቅም ላይ ይውላል።
አጋ ብርዞስቶውስካ ግን ይህ ስያሜ አይዋጥላትም፤ እንዲያውም ነገሩ እንግዳ ሆኖባታል።
የበርሚንግሃም ዩኒቨርሲቲ ተማሪና የ20 ዓመቷ ኮረዳ «ቆዳዬ በተፈጥሮ በጣም ነጣ ያለ አይደለም» ትላለች፤ ጠቆር ለማለት መሞከሯን ግን አትክድም።
«ታኒንግ አለ አይደለ እንዴ?» ትላለች፤ ሰዎች ጠቆር ለማለት የሚጠቅሙበት የተለመደ ዘዴ በማጣቀስ።
«እኔ ቆዳዬን ማጥቆሬን እርግፍ አድርጌ መተው አልፈልግም፤ ሳደርገው ደስ ይለኛል፤ ጥቅምም አገኝበታለሁ» ትላለች አጋ።
አጋ ትቀጥልና «የነጭ የበላይነት የለም ብዬ የማምን ሰው አይደለሁም፤ ነገር ግን እኔን የሚተቹ ሰዎች መጥፎ ድርጊት እንደፈፀምኩ እንዲያስቡ አልፈቅድም» ስትል አቋሟን ታስረግጣለች።
አጋ ቆዳቸው ጠቆር ብሎ እንዲታይ ከሚሹ እና ከሚያደርጉ የትየለሌ የማሕበራዊ ድር-አምባ ተጠቃሚዎች አንዷ ናት።
ኢንስታግራም በተሰኘው የማህበራዊ መገናኛ መድረክ ላይ ከሚገኙ 'ጥቋቁር ነጮች' መካከል 200 ሺህ ያክል ተከታይ ያላት ስዊዲናዊቷ ኤማ ሃልበርግ ትጠቀሳለች።
በተፈጥሮ ቀለሟ የተነሳችው ልሙጥ ፎቶ ጠቁራ ከተነሳችው ጋር ተነፃፅሮ ማሕበራዊ ድር-አምባውን የሞላባት ኤማ «እኔ ራሴን እንደ ነጭ ሴት ነው የማየው ትላለች»፤ በእርግጥም ነጭ ናት።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ
«ቆዳዬ ጠቁሮ ሊታይ የቻለው ከፀሐይ ብርሃን ከማገኘው ተፈጥሯዊ ኃይል ነው» ትላለች ኤማ።
አጋ፤ ነገሩ እንደውም እኔ እና የሃገሬ ሰዎች ላይ እየደረሰ ያለ በደል ነው ባይ ናት። በልጅነቷ ከነበራት ቀለም ጋር የማይገናኝ ቀለም እና የሰውነት ቅርፅ ነው ያላት ብለው ለሚተቿት ምላሽ ስትሰጥ «ሰውነቴ ጂም ገብቼ ጠብ እርግፍ ብዬ ያመጣሁት ነው» በማለት ሰዎች ለፖላንዳዊያን ያላቸው አመለካከት የተዛባ እንደሆነ ትጠቁማለች።
ሰዎች ስለ ፖላንዳዊያን ሲያስቡ ነጭ እና ስስ ከናፍር ያላቸው አድረገው ማሰባቸው ዋናው ችግር እንደሆነ ታሰምራለች።
ጉዳዩ ምን ያህል አሳሳቢ ይሆን?
ጉዳዩን ወደሰው እዝነ ሕሊና ያመጣችው የትዊተር ተጠቃሚዋ ዋና ቶምፕሰን ናት፤ «ኧረ ሰዎች ይህ ነገር አሳስቦኛል» በማለት።
አንዳንድ የትዊተር መንደር ሰዎች «ታድያ ምን ይጠበስ?» ቢሏትም በርካቶች ግን ነገሩ ዘልቆ የገባቸው ይመስላል።
ዳራ ቱርሞንድ «እኔ የሚያንገበግበኝ እኒህ ነጭ ሴቶች እኛን መስለው መታየታቸው ሳይሆን፤ ጥቁር ሴቶች በተፈጥሯዊ መልካቸው ለመታየት የሚያደርጉትን ትግል አለመረዳታቸው ነው» ትላለች።
«እኛ ጥቁሮች እኮ በተፈጥሯዊ ፀጉራችን መታየት እየከበደን ነው፤ አፍሮ ወይም ቁጥርጥር መሰራት ንፅህና እንደሌለው እና ያፈነገጠ እንደሆነ እየተቆጠረብን ነው።»
ኪም ካርዳሺያን የተሰኘችው አሜሪካዊት ታዋቂ ሴት 'ብላክፊሺንግ' ከተባለው ሃሳብ ጋር ስሟ በተደጋጋሚ ሲነሳ ይደመጣል። ምክንያቱ ደግሞ የኪም አድናቂዎች፤ በተለይ ወጣቶች፤ የሰውነት ንቅለ ተከላ በማድረግ ባህል 'መበከላቸው' ነው ተብሎ ሲነገር ይደመጣል።
ዳራ ነገሩ ብዙም የሚደንቅ አይደለም ትላለች፤ «በርካታ ጥቁር ሴቶች በተፈጥሯዊ ውበታቸው ወደፊት ብቅ ብቅ ማለታቸው የፈጠረው ተፅዕኖ ነውና።»
የአጋን ትክክለኛ ማንነት የተረዱ ሰዎች በማህበራዊ ገፆቿ ውስጥ መስመር በመግባት 'ራስሽን ብታጠፊ ይሻላል' በማለት በነገር እንደሚሸነቁጧት ሳትደብቅ ትናገራለች።
«እውነት ለመናገር. . .» ትላለች አጋ፤ «እውነት ለመናገር አሁን አሁን ጉዳዩ እየገባኝ መጥቷል፤ ለጥቁር ሴቶች ጉዳዩ ምን ያህል ትርጉም እንዳለው ገብቶኛል።»
ግን ፎቶሽን ትቀይሪ ይሆን? ለአጋ የቀረበላት ጥያቄ ነው።
«እኔ ምኔን እንደምቀይር አላውቅም፤ ምክንያቱም ትክክለኛው እኔ ነኛ።»












