የእሰራኤል መከላከያ ሚኒስትር አቪግዶር ሊበርማን በጋዛ ተኩስ አቁም ውሳኔ ምክንያት ለቀቁ

የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር አቪግዶር ሊበርማን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የእስራኤል ካቢኔ የጋዛ ተኩስ አቁም ውሳኔን ማስተላለፉን ተከትሎ የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ከስራ ለቀቁ።

ለሁለት ቀናት ያህል ከፍልስጥኤም ጋር የነበረውን ግጭት ተከትሎ የተወሰነውን ውሳኔ "ለአሸባሪዎች መንበርከክ" ሲሉ ሚኒስትሩ አውግዘውታል።

በተጨማሪም የቀኝ ዘመም ፓርቲው ይስራኤል ቢተይኑ ፓርቲ ኃገሪቷን ከሚመራው የጥምር ፓርቲ መውጣት እንዳለበትና ቀደም ያለ ምርጫ ሊካሄድ እንደሚገባ አስረድተዋል።

ሰኞና ማክሰኞ በነበረው ጥቃት 460 ሮኬቶች ወደ እስራኤል የተወረወሩ ሲሆን፤ ከእስራኤል በኩል በተሰነዘረ ጥቃት ደግሞ 160 ኢላማዎች በጋዛ ወድመዋል።

የተኩስ አቁሙ ረቡዕ እለት ከተከናወነ በኋላ በደቡብ እስራኤል የሚገኙ ትምህርት ቤቶችና የንግድ ተቋማት በኋላ የተለመደውን ተግባር ማከናወን ጀምረዋል።

ነገር ግን የእስራኤል የጦር ኃይል እንዳስታወቀው በጥይት በማቁሰል በእስራኤል ጋዛ ድንበር ላይ ቦምብ ይዞ የተገኘ ሰው በቁጥጥር እንደዋለ አስታውቋል።

የፍልስጥኤም የጤና ኃላፊዎች በበኩላቸው በሰሜናዊ ጋዛ በኩል አንድ አሳ አጥማጅ በእስራኤል እንደተገደለ አስታውቀዋል።

የእስራኤል የጦር ኃይል በበኩሉ ሰውየው የተመታው ወደ ድንበሩ በመጠጋቱ ነው ብለዋል።

በአውሮፓውያኑ 2014 ከተካሄደው የአምሳ ቀናት ጦርነት አስከፊ የተባለው ይህ ጥቃት የእስራኤል የጦር ኃይል በጋዛ ላይ ሚስጥራዊ የሆነ ክንውን ተከትሎ የተፈፀመ ነው።

እሱንም ተከትሎ ሰባት ፍልስጥኤማውያንና አንድ ወታደር ተገድሏል።