ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የፓስተር ቲሞቲ የችሎት ውሎ በደቡብ አፍሪካ ቁጣን ቀሰቀሰ
በደቡብ አፍሪካ በቴሌቪዥን በቀጥታ የተላለፈው የፓስተር ቲሞቲ ኦሞቶሶ የችሎት ውሎ ከፍተኛ ቁጣን ቀሰቀሰ።
ናይጄሪያዊው ፓስትርና ግብረ አበሮቾቹ በአስገድዶ መድፈር በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርና በጾታ ትንኮሳ ወንጀል ነበር የተከሰሱት።
ፓስተር ኦሞቶሶና አብረውት የተከሰሱት ሁለት እንስቶች 'ጂሰስ ዶሚኒየን ዓለም አቀፍ ቤተክርስቲያን' በተሰኘ እና በደቡብ አፍሪካ በሚገኘው ፀሎት ቤታቸው ላይ 97 ክሶች ተመስርተውባቸዋል። ክሶቹም ከፆታ ጥቃት፣ አስገድዶ መድፈር እና ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ያካትታል። እነርሱ ግን ሁሉንም ክሶች አለመፈፀማቸውን ክደዋል።
ከ14 ዓመቴ ጀምሮ በተደጋጋሚ ደፍሮኛል ስትል ለፍርድ ቤት ቃሏን የሰጠችውን ተበዳይ፤ የተከሳሽ ጠበቃ ረጅም ሰዓት በፈጀ መስቀለኛ ጥያቄ ሲያጣድፋት መታየቱ ነው ለቁጣው መቀስቀስ ምክንያት የሆነው።
የስድሳ ዓመቱን ፓስተር ቲሞቲን ወክሎ የሚከራከረው ጠበቃ ለረዥም ሰዓት አንዳንዴም ቁጣ በተቀላቀለበት ሁኔታ ጥያቄ ሲያቀርብላት ታይቷል።
በሳምንቱ መጨረሻ በፖርት ኤልዛቤጥ የሚገኘው የፓስተር ቲሞቲ ኦሞቶሶ ፀሎት ቤት በተናደዱ ነዋሪዎች ጥቃት ሊደርስበት እንደሚችል በመስጋት ተዘግቶ ነበር።
እሁድ ዕለት የሚታተም አንድ ጋዜጣ እንደዘገበው ለችሎት ምስክርነታቸውን ከሰጡ ሴቶች መካከል አንዷ የሆነችው የ22 ዓመቷ ቼርሊ ዞንዲ "የእንገልሻለን" ዛቻና ማስፈራሪያ እንደደረሳት አስነብቧል።
የፓስተር ኦሞቶሶ ፀሎት ቤት በደቡብ አፍሪካ ውስጥ እያደጉ ከመጡ ወንጌላውያን አብያተ ክርስትያናት መካከል አንዱ ሲሆን ድንቅና ተአምራት ይደረግላችኋል፤ በሚል ለተከታዮቹ ቃል በመግባት፣ ከዚህ ቀደም በደቡብ አፍሪካ የተሰጥኦ ውድድር ላይ ቀርበው በሚያውቁ የደንብ ልብስ በሚለብሱ ሴት ዘማሪያን ይታወቃል።
በፓስተሩ እና ግብረ አበሮቹ ላይ የቀረበው ክስ ባለፈው ሳምንት መታየት የጀመረ ሲሆን ደቡብ አፍሪካውያን በንቃት እየተከታተሉት ነው። በተጨማሪም ለተበዳይም ያላቸውን ድጋፍ በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን በከፍተኛ ሁኔታ ያሳዩበት ሆኗል።
ተበዳይዋ በዳይ የሚያስረተዳድረውን ፀሎት ቤት በልጅነቷ እንደተቀላቀለች ተናግራ የመፅሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን እየጠቀሰ ለእግዚአብሔር ቃል ካልተገዛች ቁጣው በእርሷ ላይ እንደሚሆን በመግለፅ በተደጋጋሚ እንደደፈራት ተናግራለች።
የተከሳሽ ጠበቃ ምስክሯን "ጥሩ ተዋናይ ነሽ" "እንዲደፍርሽ ዝግጁ ነበርሻ?" "ተስማምተሽ ነበር?" በማለት ሲጠይቃት ታይቷል።
የደቡብ አፍሪካ የችሎት ሥነ ሥርዓት ተጋፋጭ ነው። ጠበቆች ምስክሮችን ፈትረው በመያዝ ይታወቃሉ። ነገር ግን ይህ ጠበቃ እንደ አንዳንድ ባለሙያዎች አስተያየት መስመሩን የሳተ ነው ተብሏል።
ምስክሯ በ14 ዓመቷ ፓስተሩ ሲደፍራት የነበረውን ሁኔታ በዝርዝር ስታስረዳ 'እንዴት አወቅሽ?' "ተሰምቶሽ ነበር?" የሚሉና ሌሎች ጥያቄዎችን በመጠየቁ በችሎቱ ውስጥ ለቅሶና ቁጣ ተሰምቷል።
በኋላም ዳኛው ጠበቃውን በማቋረጥ ጥያቄውን እንዲያስተካክል ያደረጉ ሲሆን ወደ ምስክሯም በመሄድ ለዚህ ችሎት ስትል ትታ የመጣችውን የዩኒቨርስቲ ፈተና እንድትቀጥል መልካም ምኞታቸውንም ገልፀውላታል።
ይህ ግን በተከሳሽ ጠበቃ በኩል በበጎ አይን አልታየም አድልዎ ፈፅመዋል በሚል ተወንጅለዋል።
የኔልሰን ማንዴላ የልጅ ልጅ የሆነችውና በ2017 በቀድሞ ፍቅረኛዋ እንደተደፈረች የተናገረችው ንዲልካ ማንዴላ ተበዳይዋን ደግፈው ከተናገሩ ደቡብ አፍሪካውያን መካከል አንዷ ናት።
ተበዳይዋ በምስክር ሳጥን ውስጥ ሆና የደረሰባት ነገር ሌሎች ተበዳዮች በደላቸውን ውጠው በየቤታቸው እንዲቀመጡ የሚያደርግ ነገር ነው ስትል አስረድታለች።
በሚቀጥሉት ቀናት በርካታ ምስክሮች እንደሚቀርቡ ይጠበቃል። ፓስተሩ ግን አሁንም ንፁህ ነኝ እያለ ሲሆን አሁንም የበርካታ ሴት ምዕመናን ድጋፍ አለው። በችሎቱ ሥነ ሥርዓት ወቅት የተከሳሹ የትዳር አጋር ምስክሯ ቃሏን ስትሰጥ በመሳቋ ተግሳፅ የደረሰባት ሲሆን ፓስተር ኦሞቶሶ ራሱ ዘና ብሎ አንዳንዴም ፈገግ እያለ ታይቷል።