በህንድ ሴቶች ወደ አምልኮ ቦታ አይገቡም በሚል ጥቃት ደረሰባቸው

በህንድ የሚገኙ ሴቶች ወደ ሂንዱ ቤተ አምልኮ ለመግባት ሲሞክሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በንዴት የተሞሉ የሂንዱ እምነት ተከታዮች በሂንዱ እምነት ቅዱስ ወደሚባለው የአምልኮ ቦታ ሴቶች እንዳይገቡ ከለከሉ።

ምንም እንኳን ከፍተኛው ፍርድ ቤት ሴቶች እንዲገቡ ውሳኔ ቢያስተላልፍም የተናደዱ ግለሰቦች ሴቶች ላይ ጥቃት በመጀመራቸው ምክንያት ሴቶቹ ወደ ኋላ አፈግፍገው ተመልሰዋል።

በኬራላ ግዛት በደረሰውም በዚህ ጥቃት በዕድሜ የገፉ ሴቶች ጭምር በድንጋይ እንደተመቱ፣ ከዚህም በተጨማሪ መኪኖች የተሰባበሩ ሲሆን የፖሊስ አባላትም ጥቃት ደርሶባቸዋል።

ሳባሪማላ ተብሎ የሚጠራው ይህ የአምልኮ ቦታ ዕድሜያቸው ለአቅመ ሔዋን ለደረሱ ሴቶች ዝግ ሆኖ ቆይቷል።

በሂንዱይዝም እምነት መሰረት የወር አበባ የሚያዩ ሴቶች "ንፁህ" እንዳልሆኑ ተደርገው የሚቆጠሩ ሲሆን የትኛውንም የእምነት ክንውኖች ላይ እንዳይሳተፉ ይደረጋሉ።

ምንም እንኳን ብዙዎቹ የሂንዱ ቤተ አምልኮዎች ሴቶች የወር አበባ በማያዩበት ወቅት መግባት ቢፈቅዱም፤ ሳብሪማላ የአምልኮ ቦታ ግን ዕድሜያቸው ለአቅመ ሔዋን የደረሱ ሴቶች በሙሉ እንዳይገቡ ከልክሏል።

ይህንን በመሻር ከፍተኛው ፍርድ ቤት ዕምነት የሴቶችም ሆነ የወንዶች መብት ነው የሚል ውሳኔን አስተላልፏል።

ምንም እንኳን ቤተ አምልኮው በፍርድ ቤት ትዕዛዝ መሰረት በራቸውን ክፍት ቢያደርጉም ከፍተኛ በሆነው ተቃውሞ ምክንያት ሴቶቹ መግባት አልቻሉም።