ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኤልቲቪ ብሮድካስት ባለስልጣን ማስጠንቀቂያ እንዳልሰጠው ገለፀ
በቅርቡ በኤልቲቪ ቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ሊቀ መንበር ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) ከቤተልሄም ታፈሰ ጋር ያደረጉትን ቃለ መጠይቅ ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ለቴሌቭዥን ጣቢያው ማስጠንቀቂያ እንደሰጠ በማህበራዊ ሲነገር ነበር።
የኤልቲቪ የሰው ኃይል አስተዳደር አዲስ ብርሃኑ ግን ማስጠንቀቂያ እንዳልተሰጣቸው ለቢቢሲ በመግለፅ፤ ብሮድካስቲንግ ባለስልጣን ከሚዲያዎች ጋር ተደርጎ በነበረው የመገማገሚያ ውይይት ቃለ መጠይቁ ተነስቶ "ካለው የፖለቲካ ሁኔታ ጋር የማይጣጣምና ሁኔታውንም የሚያጋግል ስለሆነ ትክክል አይደለም" የሚል አስተያየት እንደተሰጣቸው ገልፀዋል።
ስብሰባው ላይ ተገኝተው እንደነበር የሚናገሩት አዲስ ኤልቲቪን ለብቻ ጠርቶ ማስጠንቀቂያ የሰጠ አካል እንደሌለ ገልፀዋል።
ጉዳዩን እንደ ማስጠንቀቂያ እንደማይወስዱት የተናገሩት አዲስ ቃለ-መጠይቁ ከማህበራዊ ሚዲያ ላይ የወረደበት ምክንያት ከብሮድካስት ባለስልጣን አስተያየት ጋር የተገናኘ አይደለም ብለዋል።
"ከማህበራዊ ሚዲያ ላይ ቃለመጠይቁን ያወረድነው በራሳችን ፍቃድ ነው። ጋዜጠኛዋን የግል ህይወት የሚነካና ስድብ ስለበዛ ጉዳዩን ለማቀዝቀዝ አውርደነዋል።" ብለዋል።
በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ቤተልሄም ሥራ እንደለቀቀች ተደርጎ የሚነገረውም ፍፁም እውነት እንዳልሆነ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ቤተልሄም ታፈሰ ከቢቢሲ ጋር በነበራት ቆይታ ብሮድካስት ባለስልጣን ቃለ መጠይቁ ከዩቲዩብ እንዲወርድ ቴሌቪዥን ጣቢያውን እንዳስጠነቀቀ እንዲሁም ''እኔም ከአሁን በኋላ አስተካክዬ እንደሰራ'' ነው ከቢሮዬ የተነገረኝ ትላለች።
ቤቴሌሄም ትናንት ምሽት ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ ያነጋገራቸው የኤልቲቪ የሰው ኃይል አስተዳደር አዲስ ብርሃኑ አስተያየት ትክክል አይደለም ትላለች።
''የግል አሰተያየታቸው እንደሆነ ነው የሚገባኝ'' ብላላች። ቤተልሄም አክላ እንደተናገረችው ''በጉዳዩ ላይ እኔን ሳትጠይቁኝ በሰራተኛ ቅጥር ላይ ያለችን ጉዳዩ ብዙም የማይመለከታትን ግለሰብ ማነጋጋራችሁ በዘገባው ቅር እንድሰኝ አድርጎኛል።'' ብላለች።
ቢቢሲ በወቅቱ አዲስን ባናገራት ወቅት ስብሰባው ላይ መገኘታቸውንና ኤልቲቪ በስራው እንደሚቀጥል የተናገሩ ሲሆን ጨምረውም "ጋዜጠኛዋ ስራ ለመልቀቅ ብታስገባ ቀጥታ የሚመለከተው እኔን ነው" ብለዋል።
ትናንት ምሽት ነዋሪነቱን አሜሪካን ሃገር ካደረገው የቅርብ አለቃዬ ነው ከምትለው የቴሌቪዥን ጣቢያው ባለቤት ጋር በጉዳዩ ላይ መነጋገሯን የምትናገረው ቤቲ ከአለቃዋ ጋር''በሥራዬም እቀጥላለሁ'' ብላለች።
ኤልቲቪ የቴሌቪዥን ጣቢያም በፌስቡክ ገፃቸው ባወጡት መልዕክት የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ሃላፊዎችን ጠርቶ እንዳናገረ ገልፀው፤ ባለስልጣኑ እንዲያስተካክሉም አስተያየት እንደተሰጣቸው አስፍረዋል። " ባለስልጣኑ ይስተካከሉ ባላቸው ጉዳዮች ማለት የቃላት አጠቃቀም፣ ወደ ብሄር ብሄረሰቦች ያዘነበሉ የሚመስሉ ጥያቄዎችና አስተሳሰቦች እንዲሁም መሰል ችግሮችን እንድናስተካከል ምክር አዘል ማሳሰቢያ ተሰጥቶናል" የሚል ፅሁፍ ሰፍሯል።
በዩቲዩብ የሚገኘውን ፕሮግራም ከገፃቸው ላይ እንዲያነሱ ማሳሰቢያ እንደተሰጣቸው ገልፀው በትዕዛዙም መሰረት በትናንትናው እለት ማንሳታቸውን አስታውቀዋል። በማህበራዊ ሚዲያ የሚራገቡት ጣቢያው ሊዘጋ ነው፣ ጋዜጠኛዋ ተባራለች የሚሉት ትክክለኛ መረጃም እንዳልሆነ አስፍረዋል።
እስካሁን በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡን የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ኃላፊዎችን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ባይሳካም ጥረት ማድረጋችንን እንቀጥላለን።