በዴምህት ወታደሮች ላይ በደረሰው የመኪና አደጋ የሰዎች ህይወት አለፈ

የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ዴምህት) ወታደሮች ዛሬ ጠዋት ከኤርትራ ወደ ዛላምበሳ በሚመጡበት ወቅት ነበር ሰገነይቲ በሚባለው የኤርትራ ድንበር ላይ የመኪና አደጋ ያጋጠማቸው።

በአደጋው አራት ወታደሮች ሕይወታቸው ሲያልፍ ከ 20 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸው በኤርትራ በደቀምሃሬ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው እንደሆነ በስፍራው የሚገኘው ሪፖርተራችን ዘግቧል።

ተሳፍረውበት የነበረው መኪናም የጭነት መኪና እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።

በአደጋው ብዙ የዴምህት ወታደሮች እንደተጎዱ ከአካባቢው ወደ ዛላምበሳ የመጣ የድርጅቱ አመራር አባል ለቢቢሲ ተናግሮ ነበር።

በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸውን የወታደሮች ቁጥር በውል ባይገልጽም፤ ሰራዊቶቹን የያዘች መኪና እንደተገለበጠች ግን ቀደም ሲል ለቢቢሲ ገልፆ ነበር።

መንግሥት ባቀረበው የሰላም ጥሪ መሰረት ከ2000 በላይ የደምህት ወታደሮች ዛሬ ማለዳ ዛላምበሳ ይደርሳሉ ተብሎ ተጠብቆ ነበር። ከተጓዦቹ መካከል ከፊሎቹ ዛላምበሳ መድረሳቸውን ለማወቅ ተችሏል። ከአደጋው መከሰት ጋር ተያይዞ ቀሪዎቹ የደምህት ወታደሮች ጉዟቸውን ወደ ዛላምበሳ ይቀጥሉ አልያም ወደ ኤርትራ ይመለሱ የሚታወቅ ነገር የለም።

የሠራዊቱን አባላት የሚቀበሉ የህዝብ አውቶብሶች በዛላምበሳ ከተማ ተዘጋጅተው እየተጠባበቁ ይገኛሉ።