ሰራተኞች የፈለጉትን ያክል ሰዓት ብቻ ሰርተው የሚወጡበት ተቋም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከዓለም ግዙፍ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው ፕራይስ ዋተር ሃውስ ኮርፖሬሽን (PwC) ሰራተኞቹ ፈታ ዘና ብለው ሥራቸውን እንዲከውኑ የሚያደርግ አሰራር የሥራ ሰዓት ይፋ አድርጓል።
በአዲሱ የሥራ ሰዓት መሰረት ሰራተኞች በተለመደው ከ3 እስከ 11 ሰዓት ድረስ በቢሮ ውስጥ የመቀመጥ ግዴታ አይኖርባቸውም።
በምትኩ ሰራተኞች ሊሰሩበት የሚፈልጉትን የሰዓት ርዝመት እንደ ግል ፍላጎታቸው እንዲወሰኑ ፈቅዷል።
ከዚህ በተጨማሪ ሰራተኞች ከሙሉ ዓመት ውስጥ የተወሰኑ ወራትን ብቻ በስራ የሚያሳልፉበትን መብትም ሰጥቷል።
በተቋሙ ለመቀጠር የሚፈልጉ አመልካቾች በማመልከቻ ቅጽ ላይ ተሰጥኦና ዝንባሌያቸውን ብሎም ለሥራ ምቹ የሚሆንላቸውን ሰዓት የሚሞሉበትን አሰራር ጀምሯል።
በዓለማችን ከሚገኙ አራት ግዙፍ የሒሳብ ሥራ ኩባንያዎች ውስጥ የሚመደበው ራይስ ዋተር ሃውስ ኮርፖሬሽን (PwC)፤ ይህን አሰራር ይፋ ያደረገው 2000 ሰዎችን በጥናት ካሳተፈ በኋላ ነው።
በጥናቱ ከተሳተፉ 46 በመቶ ያህሉ እንዳሻቸው የሚለዋውጡት የስራ ሰዓት እንዲሁም ጥሩ የሥራ እና የህይወት ምጥጥንን እንዲኖር መርጠዋል።
የተቋሙ ሃላፊ ሎውራ ሂልተን ''ሰዎች በግዙፍ ኩባንያዎች ውስጥ መስራት ማለት በተለመደው የሥራ ሰዓት መግባት እና መውጣት ግድ የሚላቸው ይመስላቸዋል። ይህ ግድ መሆን የለበትም። ብቃት ያላቸውን ሰራተኞችን ለማግኘት በቅድሚያ የተወሰነ የሥራ ሰዓትን ማስቀረት ነበረብን'' ብለዋል።
''ሰራተኞች በተመቻቸው የሥራ ስዓት እንዲገቡ እና እንዲወጡ መፍቀዳችን፤ ለሰራተኛው ብቻ ሳይሆን ለተቋሙም እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል'' ብለዋል።












