በደቡብ አፍሪካ ዝቅተኛው የሠራተኛ ወርሃዊ ክፍያ 7ሺ ብር ሊሆን ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከትናንት በስቲያ ማክሰኞ የደቡብ አፍሪካ ፓርላማ ለሠራተኞች ዝቅተኛውም የክፍያ መጠን የሚወስን ረቂቅ ሕግ ማጽደቁ ተዘግቧል።
ደቡብ አፍሪካ በዓለም ላይ ከፍተኛ የክፍያ ልዩነት ከሚታይባቸው አገሮች አንዷ ናት።
የፓርላማውን ይሁንታ ያገኘው ይህ ሕግ በሰዓት ትንሹ የክፍያ ልክ 20 የደቡብ አፍሪካ ራንድ መሆኑን ይደነግጋል። ይህም በሰዓት አንድ ዶላር ከስድሳ ሳንቲም ወይም 45 ብር ይጠጋል።
ምንም እንኳ ፕሬዚዳንት ራማፉሶ ረቂቁን ወደ ሕግ የሚቀይረውን ፊርማ እስከ አሁን ባያኖሩም የክፍያው ማደግ በትንሹ 6 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎችን ኑሮ ያሻሻል ተብሎ ይጠበቃል።
ገዢው ፓርቲ ኤኤንሲ ረቂቁን ታሪካዊ ብሎታል። የሠራተኛ ጉዳዮች ሚኒስትር የሆኑት ኦሊፋንታ በበኩላቸው ማሻሻያው በመጠኑ ትንሽ ቢሆንም መልካም ጅምር ነው ብለውታል።
"ረዥም ጉዞ ከእርምጃ ይጀምራል። የጉልበት ሠራተኞች እዚህ ግባ የሚባል ክፍያ ሳያገኙ አስቸጋሪ ሕይወትን አሳልፈዋል፤ ተበዝብዘዋል። የአሁኑ እርምጃ የረዥሙ ጉዞ መጀመርያ ነው" ብለዋል ሚኒስትሯ።
ዲኤ የሚባለው ሁነኛው ተገዳዳሪ ፓርቲ በበኩሉ ባወጣው መግለጫ እርምጃውን ተቃውሞታል። "ረቂቅ ሕጉ በቂ ሕዝባዊ ውይይት አልተደረገበትም፤ በርካቶችንም ለሥራ አጥነት ያጋልጣል" ሲል ኮንኖታል።
በዝነኛው ጁሊየስ ማሌማ የሚመራው ግራ ዘመሙ ኢኮኖሚክ ፍሪደም ፋይተርስ ረቂቅ ሕጉን ተቃውሞታል።
ይህ ሕግ በፕሬዚደንቱ ፊርማ ሲጸድቅ የደቡብ አፍሪካ ሠራተኞች ወርሃዊ የክፍያ ወለል በወር 3500 የደቡብ አፍሪካ ራንድ ይሆናል። ይህ ወደ ብር ሲመነዘር ከ7ሺ ብር ይልቃል።












