በአማራ ክልል መሐል ሳይንት ገዳም ላይ በተፈጸመ "የከባድ መሣሪያ ጥቃት" ስድስት ሰዎች መገደላቸው ተሰማ

የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

በአማራ ክልል፣ ደቡብ ወሎ ዞን፣ በመሐል ሳይንት ወረዳ በሚገኘው ርዕሰ አድባራት ወታዕካ ነገሥት አትሮንሰ ማርያም ገዳም ላይ በተፈጸመ "የከባድ መሣሪያ ጥቃት" ስድስት ሰዎች እንደተገደሉ እና ከ20 በላይ ሰዎች እንደተጎዱ የገዳሙ አስተዳዳሪ እና የዐይን እማኞች ለቢቢሲ ገለጹ።

ቅዳሜ የካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም. ከረፋዱ ሦስት ሰዓት ተኩል አካባቢ "በሞርታር ጥቃት እንደተፈጸመ" የርዕሰ አድባራት ወታዕካ ነገሥት አትሮንሰ ማርያም አስተዳዳሪ መክብብ አባ ገብረእግዚአብሔር ኃይለማርያም ተናግረዋል።

ከዕለቱ ቅዳሴ በኋላ በደረሰው ጥቃት የገዳሙ አበው መነኮሳት፣ ዲያቆናት እና የድጓ ተማሪ መገደላቸውን የገዳሙ አስተዳዳሪው ተናግረዋል።

በተፈጸመው ጥቃት አባታቸው እንደተገደሉባቸው ለቢቢሲ የገለጹት መሪ ጌታ ስሙር፤ "ከቤተ ክርሰቲያኑ ጩኸት ሲሰማ እየሮጥኩ ብሄድ እንደዛ ሆኖ አገኘሁ። ብዙ አስክሬን ተመለከትኩ. . . አስከሬኖቹን አንስቼ ለቤተሰቦቻቸው ሰጠሁ" ብለዋል።

የገዳሙ አስተዳዳሪ በበኩላቸው፤ የገዳሙ መሪ ጌታ፣ የድጓ አድራሽ እና በዕለቱ ለሙት ዓመት መታሰቢያ መባ ይዘው ወደ ገዳሙ የሄዱ አዛውንት ሴት "እግራቸው እና እጃቸው እንደተቆረጠ" የተናገሩ ሲሆን፤ የደብሩ ጥበቃ ደግሞ "ዐይናቸውን እና እግራቸውን" እንዳጡ አስረድተዋል።

በተጨማሪም "የመሣሪያ ፍንጣሪ የመታቸው" 21 ሰዎች መቁሰላቸውን አስተዳዳሪው ገልጸዋል። በወረዳው በሚገኙ እንዲሁም ደሴ ከተማ ባሉ ሆስፒታሎች ሕክምና ላይ እንደሚገኙ አክለዋል።

ከቅዳሴ በኋላ የቤተ ክርስቲያኑ አገልጋዮች ለመባ በተሰባሰቡበት ወቅት ጥቃቱ እንደተፈጸመ እና የአካል ጉዳት የደረሰባቸውም ካህናት፣ መነኮሳት፣ የአብነት ተማሪዎች እና ዲያቆናት እንደሆኑ ተናግረዋል።

"አሁን ደብሩ ላይ ያለሁት እኔ ብቻ ነኝ። ከ100 ያላነሱ አገልጋዮች ነበሩ" ያሉት አባ ገብረእግዚአብሔር፤ የተቀሩት አገልጋዮች "እንደሸሹ" እና ሌሎች አገልጋዮች ደግሞ በሕክምና ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

የገዳሙ አስተዳዳሪ የቤተ ክርስቲያኑ አዳራሽ፣ የቤተ ክርሰቲያኑ ቆርቆሮ እና የምዕመናን ቤት ላይም ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪ እና የዐይን እማኝ በጥቃቱ ከተገደሉት አንደኛው የባለቤታቸው አባት መሆናቸውን ገልጸዋል።

"ከቅዳሴ በኋላ ከጓሜዳ ወደ አትሮንሰ በተተኮሰ ሞርታር የስድስት ሰዎች ሕይወት አልፏል። 28 ሰዎች ላይ ከባድ ጉዳት ደርሷል" ብለዋል።

በጥቃቱ ሳቢያ የአካል ጉዳት ከደረሰባቸው ሰዎች "ግማሾቹ እጃቸው ተቆርጧል፣ ግማሾቹ እግራቸው ተቆርጧል፣ ሌሎቹ ዐይናቸው ጠፍቷል" ሲሉም አክለዋል።

ከመካከላቸው ወደ 10 የሚጠጉት ሰዎች የደረሰባቸው "መጠነኛ ጉዳት" እንደሆነ ገልጸዋል።

የተገደሉት ሰዎች አካላቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው ስለነበር "ይሄ እከሌ ነው" ለማለት እንኳ እንዳልተቻለ የዐይን እማኙ አክለዋል።

የገዳሙ አስተዳዳሪም "ሬሳቸውን ለየብቻ ከፋፍለን እየለቀምን ነው ያነሳነው። ሙሉ አካላቸውን አላገኘንም" ብለዋል።

"እዚህ አካባቢ ያሉ ታጣቂዎች እንደዚህ ያለ መሣሪያ የላቸውም፤ ሊኖራቸውም አይችልም" ያሉት የዐይን እማኝ ጥቃቱ በአካባቢው በሚገኝ "የፀጥታ ኃይል" ሳይፈጸም እንዳልቀረ ተናግረዋል።

የፋኖ ታጣቂዎች እና የመንግሥት ኃይል በሚንቀሳቀሱበት በዚህ አካባቢ ቢቢሲ ጥቃቱ በማን እንደተፈጸመ በገለልተኛነት ለማረጋገጥ የሚችልበት ዕድል የለውም።

ስለተፈጸመው ጥቃት ከክልሉ እንዲሁም ከፌደራል መንግሥት በኩል እስካሁን በይፋ የተባለ ነገር የለም።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንም በደቡብ ወሎ ዞን በሚገኝ ገዳሟ ላይ ስለደረሰው ጉዳት እና የሰዎች ሞት በተመለከተ አስካሁን በይፋ የሰጠችው መረጃ የለም።

ቢቢሲ ከደቡብ ወሎ ዞን አስተዳዳሪዎች ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ስልካቸው ባለመነሳቱ አልተሳካም።

ጥቃቱ የተፈጸመበት የመሐል ሳይንት ወረዳ በአጅባር ወረዳ እና በመካነ ሰላም ወረዳ መካከል የሚገኝ ሲሆን፤ ከባድ መሣሪያው የተተኮሰው "ከአጅባር ዝቅ ብሎ ከሚገኘው ጓሜዳ" እንደሆነ የዐይን እማኙ ገልጸዋል።

የመከላከያ ሠራዊት በአካባቢው በሚገኝ "ጅምር ሆስፒታል" እና አጅባር በሚገኝ "ሙያ እና ቴክኒክ ተጠግተው" እንደሚገኙ የተናገሩት የዐይን እማኙ፤ "ከአጅባር ወጥተው፣ ዝቅ ብሎ ባለው ጓሜዳ የገጠር ቀበሌ ሆነው ሲያስወነጭፉ ነው የተተኮሰው" ብለዋል።

የገዳሙ አስተዳዳሪም "የጦር መሣሪያው የወረደው ከአጅባር ነው" በማለት ገልጸዋል።

ጥቃቱ ሲፈጸም በቦታው የነበሩት የገዳሙ አስተዳዳሪ መክብብ አባ ገብረእግዚአብሔር፤ "ሦስት [መሣሪያ] ተወረወረ። አንደኛው ከእኛ በታች አምባ ሥር አረፈ። ሁለተኛው አልፎ ሄደ። ሦስተኛው ደብሩ ላይ አረፈ" ብለዋል።

በተፈጸመው ጥቃት የተደገሉት መክብብ አባ ሞገስ ፍስሐ (የደብሩ ቀዳሽ)፣ ዲያቆን ከናፈርግብ አንዳርጌ (የዕለቱ ቀዳሽ)፣ እማሆይ ድንቄ ታከለ (የደብሩ ዐቃቢ)፣ ዲያቆን በለጠ አስቻለው (የዕለቱ ቀዳሽ)፣ ዲያቆን በአማን ገብረማርያም (የድጓ ተማሪ) እና ዲያቆን አይመረ መርሻ (የዕለቱ ቀዳሽ) መሆናቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከተገደሉት መካከል የሦስቱ የቀብር ሥነ ሥርዓት የካቲት 29 ቀን 2018 ዓ. ም. እዚያው ገዳሙ ውስጥ ተከናውኗል።

ጥቃቱ ለምን እንደተፈጸመ "የምናውቀው ነገር የለም" ያሉት የገዳሙ አስተዳዳሪ "የከባድ መሣሪያ መጥቶ ሲጨፈጭፈን አየን እንጂ. . . ለኢትዮጵያ እና ለዓለም መጸለያችንን እና ሥርዓተ እግዚአብሔር ማድረሳችንን ብቻ ነው የምናውቀው። ጉዳት እና ውድመት ይደርስብናል ብለን የምናስበው የለም" ሲሉም አስረድተዋል።

የዐይን እማኙ በበኩላቸው፤ ገዳሙ በደን የተከበበ በመሆኑ "ጫካ ውስጥ ታጣቂዎች ይኖራሉ በሚል ሆነ ተብሎ [የተፈጸመ] ነው ብዬ ነው የምገምተው" ብለዋል።

ቅዳሜ የካቲት 28 ቀን 2018 ዓ. ም ጥቃቱ ከተፈጸመ አንስቶ በመሐል ሳይንት አካባቢ "በተከታታይ ሲተኮስ ነበር" ሲሉም አክለዋል።

ከዚህ ቀደም በደቡብ ወሎ ዞን፣ መሐል ሳይንት ወረዳ ኅዳር 30 ቀን 2016 ዓ. ም. በተፈጸሙ ሁለት የድሮን ጥቃቶች በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ መናገራቸው ይታወሳል።

በዞኑ ልዩ ስማቸው መሳለሚያ እና ቀይ ዋሻ በተባሉ አካባቢዎች ላይ በተፈጸሙት የድሮን ጥቃቶች የተገደሉ ሰዎችን በተመለከተ ትክክለኛ አሐዝን ለማወቅ ባይችልም፤ የሟቾች ቁጥር 40 እንደሚደርስ ቢቢሲ ያነጋገራቸው አምስት የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች ገልጸውም ነበር።

ሦስት ዓመት ሊማላው በተቃረበው በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በአማራ ክልል ውስጥ እየተካሄደ ባለው ግጭት መካከል በሚፈጸሙ ጥቃቶች በሰላማዊ ሰዎች እና በተቋማት ላይ ጉዳት መድረሱን የመብት ተቋማት ሪፖርት ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወሳል።

በእምነት ቦታዎች ላይ እንዲህ ያለው ጥቃት ሲፈጸም እምብዛም ተሰምቶ የማያውቅ ሲሆን፣ በመሐል ሳይን በሚገኝ ቤተክርስቲያን ላይ የተፈጸመው የከባድ መሣሪያ ጥቃት ያልተጠበቀ እና አሰቃቂ መሆኑን ቢቢሲ ያናገራቸው አምስት ዐይን እማኞች ገልጸዋል።

በሰው ሕይወት እና በአካል ላይ ጉዳት የደረሰበት ጥቃት የተፈጸመባት በደቡብ ወሎ ዞን በመሐል አምሃራ ሳይንት የምትገኘው ታዕካ ነገስት አትሮንሰ ማርያም ገዳም ጥንታዊት ታሪክ ያላት ገዳም መሆኗን የመሃል ሳይንት ወረዳ ኮሙኒኬሽን በገጹ ላይ ያወጣው መረጃ የመለክታል።