ኢትዮጵያ ይበልጥ የምትጠቀመው ከማን ብትወዳጅ ነው? ከቱርክ ወይስ ከእስራኤል?

የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

የቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን በአዲስ አበባ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ባደረጉ በሳምንቱ የእስራኤል ፕሬዝዳንት አይዛክ ሄርዞግ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ነበር። ሁለቱም መሪዎች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ተወያይተዋል።

ቱርክ እና እስራኤል በዓለም አቀፉ የፖለቲካ መድረክ በተቃርኖ የሚንቀሳቀሱ አገራት ናቸው።

እስራኤል ለሶማሊላንድ የአገርነት ዕውቅና ስትሰጥ በጽኑ ከተቃወሙት መካከል ቱርክ ትጠቀሳለች። ኢትዮጵያ ደግሞ ከሁለቱም አገራት ጋር የረዥም ጊዜ ወዳጅነት አላት።

ለመሆኑ ከወቅታዊው የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ አንጻር የእስራኤል እና የቱርክ መሪዎች ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወደ አዲስ አበባ መሄዳቸው አንድምታው ምንድን ነው? ኢትዮጵያ ሁለት ተቃራኒ አቋም ያላቸውን አገራት ፍላጎት እንዴት ማጣጣም ትችላለች?

ሌላው ተያይዞ የሚነሳው ጥያቄ ኢትዮጵያ ካሏት ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ፍላጎቶች አንጻር ከየትኛው አገር ጋር ብትወዳጅ የበለጠ ታተርፋለች? የሚለው ነው።

ተቃራኒ ፍላጎት ያላቸው ሁለት የኢትዮጵያ አጋሮች

የቱርክ እና እስራኤል መሪዎች በሳምንት ልዩነት ወደ ኢትዮጵያ የሄዱበትን ምክንያት ከወቅታዊው የአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካ ትኩሳት ጋር አያይዞ መመልከት ይቻላል።

በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ የፖሊሲ ጥናት ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ሙከረም ሚፍታህ፤ የኤርዶዋን ጉብኝት ከምሥራቅ አፍሪካ የደኅንነት ስጋት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ያምናሉ።

በሌላ በኩል የእስራኤል ፕሬዝዳንት ጉብኝት አገሪቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት "ለማጠበቅ እና ለማስቀጠል" ከምታደርገው ጥረት ጋር ይተሳሰራል።

በአፍሪካ ቀንድ የደኅንነት ስጋት ማንዣበቡ "በቀጥታም በተዘዋዋሪም" ኢንቨስትመንቷን የሚያናጋባት ቱርክ "ነገሩን ለማብረድ" እንደምትፈልግ ይናገራሉ።

በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል የቀጠለው የቃላት ጦርነት በቀጣናው ስትራቴጂያዊ ፍላጎት ያላቸው አገራትን አስግቷል። ስለዚህም ኤርዶዋን በቀጥታ በአካል ኢትዮጵያ ሄደው ጉዳዩን ለመከታተል መርጠዋል።

በአፍሪካ ቀንድ ከአሜሪካ ጋር ተመሳሳይ የሆነ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የምታራምደው እስራኤል ከኢትዮጵያ ጋር ጥብቅ ግንኙነት አላት። ይህንን ግንኙነት "ለማስጠበቅ እና ለማስቀጠል" ፕሬዝዳንት አይዛክ ሄርዞግ ወደ አዲስ አበባ መጓዛቸውን ባለሙያው ይገልጻሉ።

የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፕሬዝዳንቱን ጉብኝት በተመለከተ ባወጣው መግለጫ "ኢትዮጵያ አፍሪካ ውስጥ ወሳኝ አገር" እንደሆነች ጠቅሷል።

ኤርዶዋንም በኢትዮጵያ ሳሉ ቱርክ "ከወዳጅ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ያላትን ለዘመናት የዘለቀ ግንኙነት የበለጠ ለማጎልበት ትልቅ ትኩረት እንደምትሰጥ" ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ እና የሶማሊላንድ ጉዳይ

በቱርክ እና በእስራኤል ካሉ ዘርፈ ብዙ ልዩነቶች መካከል የቅርብ ጊዜውን እናንሳ። እስራኤል ለሶማሊላንድ የአገርነት ዕውቅና መስጠቷ ቱርክን አላስደሰተም።

የቱርክ ፕሬዝዳንት አዲስ አበባ ሳሉ እስራኤል ለሶማሊላንድ የሰጠችው የአገርነት ዕውቅና "ለሶማሊላንድም ሆነ ለአፍሪካ ቀንድ ምንም ጥቅም አይኖረውም" ብለዋል።

ሶማሊላንድ ይሄንን የኤርዶዋን ንግግር ኮንናለች። የአገርነት ዕውቅና የማግኘት ሒደት "ሰላማዊ፣ ሕጋዊ እና ዴሞክራሲያዊ" እንደሆነም ገልጻለች።

ሶማሊላንድ በሰጠችው ምላሽ ቱርክ "የቀጣናው ውጥረትን የሚያባብስ" አቋም ከማንጸባረቅ እንድትታቀብ አሳስባለች።

ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ሰነድ ሰላም እና መረጋጋት በራቀው ቀጣና ሌላ ውጥረት የጫረ ክስተት ነበር።

ቱርክ፤ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያን በአንካራ ስምምነት አማካኝነት ብታስታርቅም ውጥረቱ ሙሉ ለሙሉ ረግቧል ለማለት ያዳግታል።

ከሳምንት በፊት ሶማሊላንድ በእስራኤል አምባሳደር ሆነው የሚወክሏትን ከፍተኛ ዲፕሎማት ሾማለች።

የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ ሹመቱ በሶማሊላንድ እና በእስራኤል መካከል በተደረሰው ስምምነት መሠረት የተከናወነ መሆኑን በመግለጽ እንደተቀበለው አሳውቋል። እስራኤል በቅርቡ በሶማሊላንድ አምባሳደር እንደምትሾምም ተገልጿል።

እስራኤል ለሶማሊላንድ የአገርነት ዕውቅና መስጠቷን በተመለከተ ኢትዮጵያ እስካሁን በይፋ የሰጠችው አስተያየት የለም።

ይዘቱ ይፋ ባልተደረገው እና አሁን ላይ ዕጣ ፈንታው ግልጽ ባልሆነው የኢትዮጵያ እና የሶማሊላንድ ስምምነት ውስጥ ሲነሱ ከነበሩ ነጥቦች አንዱ ለሶማሊላንድ የአገርነት ዕውቅና መስጠት ነው።

ለዚህም በምላሹ ኢትዮጵያ ለባሕር በር ጥያቄዋ ምላሽ እንደምታገኝ ጭምጭምታዎች ተሰምተው እንደነበር አይዘነጋም።

በሌላ በኩል እስራኤል ለሶማሊላንድ የአገርነት ዕውቅና መስጠቷን ተከትሎ ሶማሊያ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር ያላትን ግንኙነት አቋርጣለች።

ከኢትዮጵያ ጋር በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ምክንያት ለዓመታት ስትወዛገብ የቆየችው ግብፅ የእስራኤል የቅርብ ወዳጅ ናት።

በሌላ በኩል ደግሞ ግብፅ እና ሳዑዲ አረቢያ ጥብቅ ቁርኝት ያላቸው ሲሆን፤ ከሰሞኑ የግብፁ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አል-ሲሲ ወደ ሳዑዲ ተጉዘው ከልዑል አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሳልማን ጋር ተወያይተዋል።

የባሕር በር ጥያቄ

የኢትዮጵያ የቅርብ አጋር የሆነችው የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄን "እንደምትደግፍ" የሚጠቁሙ መረጃዎች ሲወጡ ነበር።

የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂም ከኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ጀርባ "የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አለች" ብለው በተደጋጋሚ ከስሰዋል።

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዋነኛ ተገዳዳሪ የሆነችው ሳዑዲ አረቢያ በዚህ ረገድ ከኤርትራ ጎን የተሰለፈች ይመስላል።

ከሳምንታት በፊት ኤርትራ የነበሩት የሳዑዲ አረቢያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋሊድ አልኬሬጂ፣ በማስከተል ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ጋር ተወያይተዋል።

ከኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ያለው ውጥረት እየተባባሰ መጥቷል። በዚህ ውስጥ ቱርክ እና እስራኤል ያላቸው ሚና ምንድን ነው?

የአፍሪካ ቀንድን በተመለከተ እስራኤል እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ተቀራራቢ አቋም አላቸው።

በሌላኛው ጽንፍ ያለችው ቱርክ በቀጣናው የምታሳድረውን ተጽዕኖ "ማመጣን" አንደኛው የእስራኤል ፍላጎት ሊሆን እንደሚችል ዶ/ር ሙከሪም ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የፈጠረው ውጥረት፤ በቀጣናው ፍላጎት ያላቸው አገራት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ጣልቃ እንዲገቡ ያነሳሳ ነው።

የኢትዮ-ኤርትራ ውጥረት የፈጠረው ስጋት

ቱርክም እስራኤልም ለኢትዮጵያ ጠቃሚ አጋሮች ከመሆናቸው አንጻር ወደየትኛው አገር ማጋደል ኢትዮጵያን ተጠቃሚ ያደርጋል?

የፖሊሲ ጥናት ባለሙያው ዶ/ር ሙከረም፤ ከወቅታዊው ሁኔታ አንጻር ኢትዮጵያ ቅድሚያ መስጠት ያለባት ለራሷ ጥቅም መሆኑን ያስረዳሉ።

ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ሥልጣን መምጣት በኋላ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ፖሊሲ ላይ ለውጥ እየታየ ነው።

"ኃያላን አገራት ደካማ ከሆኑ አገራት ጋር በፖለቲካም በምጣኔ ሃብትም ያላቸው ግንኙነት የሁለትዮሽ የመሆን ዕድሉ እየጠበበ መጥቷል" ሲሉ ባለሙያው ይናገራሉ።

"ሰጥቶ ከመቀበል" ይልቅ ደካማ የሚባሉ አገራት ፍላጎታቸው በኃያላን የሚዋጥበት ዓለም አቀፍ አካሄድ ይስተዋላል።

ዓለም አቀፍ ሕግጋት፣ ደንቦች እና ሥርዓት ገሸሽ እየተደገረ ከመምጣቱ አንጻር ኢትዮጵያ ጥቅሟን ማስቀደም እንዳለባት ያስረዳሉ።

የዓለም አገራት ግንኙነት "የጎንዮሽ ሳይሆን የተዋረድ" እየሆነ እንደመጣም ሳይጠቅሱ አያልፉም።

የረዥም ጊዜ ጥቅምን ከግምት ውስጥ ሳያስገቡ ፍላጎታቸውን ለማስጠበቅ ብቻ ከሚንቀሳቀሱ ኃያላን አገራት ጎራ መሰለፍ በጊዜ ሒደት ዋጋ ማስከፈሉ አይቀርም።

ለኢትዮጵያን የባሕር በር እንደሚያስፈልጋት እስራኤል፣ ቱርክ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና የቀጣናው አገራትም "ያውቁታል" የሚሉት ባለሙያው ጥያቄው እንዴት ይስተናገድ? የሚለውን ያነሳሉ።

በአንድ በኩል ሰላማዊ በሆነም ባልሆነም መንገድ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጥያቄው ምላሽ እንዲያገኝ ፍላጎት አለ። በሌላ በኩል ደግሞ በሰላማዊ ስምምነት ጉዳዩ እንዲፈታ መፈለግ ይጠቀሳል።

"በግራም በቀኝም ጫና ለማሳደር የሚሞክሩትን መቋቋም መቻል አለብን። ሰላማዊ አማራጭ ላይ ግፊት ሊደረግ ይገባል" ይላሉ ዶ/ር ሙከረም።

እስራኤልም ሆነ ቱርክ የየአገራቸውን ስትራቴጂያዊ ጥቅም ለማስጠበቅ አስልተው እንደሚንቀሳቀሱት ሁሉ ኢትዮጵያም ተጠቃሚነቷን ቅድሚያ እንድትሰጥ ያሳስባሉ።

ኢትዮጵያ ወደ እስራኤልም ወደ ቱርክም እንድትጠጋ ዶ/ር ሙከረም አይመክሩም። ይልቁንም የኢትዮጵያ መንግሥት "በስሌት እና በምክንያታዊነት፤ ጥቅሙን ከፊት አድርጎ፤ ጥቅሙን ሊያሳካለት ከሚችል ከየትኛውም አካል ጋር በተጠና መልኩ አብሮ መሥራት አለበት" ይላሉ።

በዓለም አቀፍ ግንኙነት ኢትዮጵያ "መሀል ላይ በመሆን" እንደምትታወቅ ጠቅሰው፤ ማንንም ሳያስከፉ መጓዝን እንደተሻለው አማራጭ ያቀርባሉ። "አንድን አካል አስደስታለሁ ብሎ የራሱን ጥቅም አሳልፎ መስጠት" እንደማያዋጣም ይጠቅሳሉ።

ቱርክ እና እስራኤል በኢትዮጵያ ያላቸው ሚና

ቱርክ በኢትዮጵያ ያላት ፍላጎት ምጣኔ ሃብታዊ ብቻ ሳይሆን ደኅንነትን ከግምት ያስገባ ጭምርም ነው።

በኢትዮጵያ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ ከሚያፈሱ አገራት በግንባር ቀደምነት ቱርክ ትጠቀሳለች።

ግንባታ እና ግብርናን ጨምሮ ወደ 2.5 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ኢንቨስትመንት እንዳላት ሪፖርቶች ይጠቁማሉ።

ቱርክ ቀይ ባሕር ላይ ያላትን ፍላጎት ለማስጠበቅ ዋነኛ አጋር አድርጋ ከወሰደቻቸው አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ናት።

የኢትዮጵያ እና ቱርክ የሁለትዮሽ ትስስር ወታደራዊ ግንኙነትንም ያማከለ ነው።

እስራኤል ከኢትዮጵያ ጋር ያላት የዓመታት ቁርኝት ፖለቲካ እና ቀጣናዊ ደኅንነትን መሠረት ያደረገ ነው።

በየመን፣ በአረብ ባሕረ ገብ መሬት እንዲሁም በጂቡቲ እና ኤርትራ መካከል ያለው የባብ ኤል-መንዳብ ወሽመጥ ለኢትዮጵያ ቅርብ ነው። በዚህም ምክንያት እስራኤል ከኢትዮጵያ ጋር የቅርብ ወዳጅነት መሥርታለች።

በቀጣናው እንደ አል-ሻባብ ያሉ ታጣቂ ቡድኖችን መዋጋትም እስራኤል እና ኢትዮጵያን ያስተሳስራቸዋል።

የእስራኤል ተቋማት በኢትዮጵያ የኢነርጂ እና ማዕድን ዘርፍ ኢንቨስት ያደርጋሉ። አገራቱ በውጭ ንግድም ጠንካራ የምጣኔ ሃብት ትስስር አዳብረዋል።

በእስራኤል ወደ 180 ሺህ የሚጠጉ ቤተ እስራኤላውያን እንደሚኖሩ እና ወደዚያው ለማቅናት የሚጠባበቁ እንዳሉ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ።

________

ማስታወሻ፡ ይህ ዘገባ የተዘጋጀው አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ የከፈቱት ጦርነት ከመጀመሩ ቀደም ብሎ ነው።