ረሃብ ሰውነታችን ላይ ምን ጉዳት ያደርሳል?

የመንግሥታቱ ድርጅት የምግብ እርዳታ ፕሮግራም በጋዛ ሰርጥ ውስጥ ከሚገኙ ሦስት ሰዎች መካከል አንዱ ለቀናት ሳይበላ እንደሚቆይ አስታውቋል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ረሃብ የሚባል ነገር የለም ቢሉም የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ግን በጋዛ "እውነተኛ ረሃብ" አለ ሲሉ ተናግረዋል።

ባለፉት ሁለት ቀናት ውስጥ፣ በጋዛ ረሃብ የለም የምትለው እስራኤል፣ እርዳታ ወደ ክልሉ እንዲገባ "በአካባቢው ስልታዊ ፋታ" ማድረጓን አስታውቃለች።

ነገር ግን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ ኃላፊ ቶም ፍሌቸር ረሃቡ የሚያደርሰውን አደጋ ለማስቆም "ከፍተኛ መጠን ያለው ምግብ" ያስፈልጋል ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የፍልስጤም የስደተኞች ኤጀንሲ እንዳለው በጋዛ ከተማ ከአምስት ሕጻናት አንዱ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ያለበት ሲሆን ይህም በየቀኑ እየጨመረ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በበኩሉ በምግብ እጦት ምክንያት በተከሰተ ከባድ ድካም ውስጥ ያሉ ሰዎች ወደ ሆስፒታል መምጣታቸውን እና ሌሎችም በጎዳናዎች ላይ እየወደቁ መሆናቸውን ገልጿል።

የተባበሩት መንግሥታት እስካሁን በግዛቱ ውስጥ የከፋ የምግብ እጥረት መከሰቱን ማወጅ ባይችልም፣ አይፒሲ አሳሳቢ የረሃብ አደጋ ይከሰታል ሲል አስጠንቅቋል።

አስከፊ ረሃብ ምንድን ነው? መቼ ነው የሚታወጀው?

የተቀናጀ የምግብ ዋስትና ደረጃ ምደባ (IPC) አንድ ሕዝብ በቂ ተመጣጣኝ፣አልሚ ምግብ ለማግኘት ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነበት ለመግለጽ የሚያገለግል ዓለም አቀፍ ደረጃ ነው።

ደረጃ 5 ወይንም ከፍተኛው ደረጃ የሚባለው አስከፊ ረሃብ የሚከተሉትን መመዘኛዎች የሚያሟላ ይሆናል።

  • 20 በመቶ የሚሆኑት ቤቶች ለከፋ የምግብ እጦት ተዳርገዋል
  • ቢያንስ 30 በመቶ የሚሆኑት ሕጻናት በከፍተኛ የምግብ እጥረት እየተሰቃዩ ነው
  • ከ10,000 ሰዎች ቢያንስ ሁለት ጎልማሶች ወይም አራት ሕፃናት በቀጥታ በረሃብ ወይም በተመጣጠነ ምግብ እጥረት እና በበሽታ ጋር በተያያዘ ምክንያት ይሞታሉ

ግንቦት 12 ላይ የታተመው የአይፒሲ ሪፖርት በጋዛ መላው ሕዝብ ደረጃ 3 እና ከዚያ በላይ ሲል በገለፀው ቀውስ ውስጥ እየኖረ ነው።

በግንቦት እና መስከረም 2025 መካከል ወደ 469,500 የሚጠጉ ሰዎች አስከፊ የምግብ ዋስትና እጦት (አይፒሲ ደረጃ 5) ሊገጥማቸው እንደሚችል ተንብይዋል።

እነዚህ ሁኔታዎች አንዴ ከተከሰቱ፣ የከፋ ረሃብ መከሰቱ የሚታወጀው በተባበሩት መንግሥታት፣አንዳንድ ጊዜ ከአንድ አገር መንግሥት ጋር በጥምረት በመሆን፣ አብዛኛውን ጊዜ ከሌሎች ዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች ወይም የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅቶች ጋር በመሆን ነው።

ረሃብ በሰውነት ላይ ምን ያስከትላል?

ረሃብ የሚከሰተው ለረጅም ጊዜ በቆየ የምግብ እጥረት ምክንያት ሲሆን ይህም ማለት ሰውነት ለዋና ዋና ተግባሮቹ የሚያገለግለው በቂ ካሎሪዎችን አያገኝም ማለት ነው።

አብዛኛውን ጊዜ ሰውነት ምግብን ወደ ግሉኮስ ይሰባብራል። ነገር ግን ምግብ በማያገኝበት ጊዜ ሰውነት በጉበት እና በጡንቻዎች ውስጥ ያለውን ግላይኮጅንን በመሰባበር ወደ ደም ውስጥ ግሉኮስ እንዲለቀቅ ያደርጋል።

እነዚያ የግሉኮስ ምንጮች ሲሟጠጡ፣ ሰውነቱ በቂ ኃይል ለማምረት ወደ የተከማቸ ስብ እና በመጨረሻም ወደ ጡንቻዎች ፊቱን ያዞራል።

ረሃብ ሳንባዎች፣ሆድ እና የመራቢያ አካላት እንዲቀንሱ እና አንጎልን ሊጎዳ ይችላል።

ይህም ቅዠት፣ድብርት እና ጭንቀት ያስከትላል።

አንዳንድ ሰዎች በረሃብ የሚሞቱ ሲሆኑ፣የከፋ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ያጋጠማቸው ሰዎች ብዙውን ጊዜ በሽታ የመከላከል አቅማቸው ስለሚጎዳ እንደ የመተንፈሻ አካላት ወይም የምግብ መፍጫ ስርዓቶች ላይ በሚከሰቱ ኢንፌክሽኖች ምክንያት ይሞታሉ።

ረሃብ ሰዎችንም በተለያየ መንገድ ይጎዳል።

በዩናይትድ ኪንግደም በግላስጎው ዩኒቨርሲቲ በተመጣጠነ ምግብ ላይ ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ሻርሎት ራይት "በድንገት በከፋ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ብቻ አይጠቁም፤ እነዚህ ልጆች ቀደም ሲል ኩፍኝ፣ የሳንባ ምች፣ተቅማጥ ወይም ተመሳሳይ የሆነ ሕመም ሊኖርባቸው ይችላል" ብለዋል።

"ቀደም ሲል ጤነኛ የነበሩ አሁን ግን መራብ የጀመሩ ልጆች አሁንም ምግብ ከተገኘ ለመመገብ እና ለመፍጨት የሚያስችል ጉልበት ይኖራቸዋል።ሌሎች ግን በቀላሉ ይጎዳሉ።"

የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሕጻናትን እና ልጆችን እንዴት ይጎዳል?

በልጅነት ጊዜ በምግብ እጥረት መጠቃት ከአካል እና ከዕድሜ ጋር የማይመጣጠን የአእምሮ እድገት እንዲኖር እና መቀንጨር ያስከትላል።

የዓለም ጤና ድርጅት መቀንጨርን ሕፃናት በተመጣጠነ ምግብ እጥረት እና ተደጋጋሚ ኢንፌክሽን ሲያጋጥማቸው የሚከሰት ነው ሲል ገልጿል።

ብዙውን ጊዜ እነዚህ ልጆች ቁመታቸው ለእድሜያቸው ከሚጠበቀው በታች ይሆናል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፋውንዴሽን በተመጣጠነ ምግብ እጥረት የሚሰቃዩ እናቶች የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ያለባቸውን ልጆች የመውለድ እድላቸው ከፍተኛ ነው ይላል።

ዩኒሴፍ በእርግዝና ወቅት የተመጣጠነ ምግብ እጥረት የደም ማነስ፣ ከፍተኛ የደም ግፊት (pre-eclampsia)፣ የደም መፍሰስ እና በእናቶች ላይ ሞት፣ እንዲሁም የሞተ ልጅ እንዲወለድ፣ ዝቅተኛ ክብደት እንዲኖራቸው እና የሕጻናት የእድገት መዘግየትን ያስከትላል።

የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ያለባቸው እናቶች ልጆቻቸውን ለመመገብ በቂ የሆነ ወተት ለማምረት ሊቸገሩ ይችላሉ።

የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ያለባቸውን ሕጻናት በማከም ላይ ያተኮረው ድንበር የለሽ የሐኪሞች ማሕበር አባል የሆኑት ዶክተር ኑራዲን አሊባባ ችግሩ እድሜ ልክ ሊዘልቅ እንደሚችል ያስረዳሉ።

"የተገታ እድገት ሊቀለበስ የማይችል ነው፣ ይህም ማለት የተመጣጠነ ምግብ እጦቱ አልፎ እንኳ ችግሩ ይቀጥላል፤ ይህም ለከፍተኛ ተጋላጭነት ይዳርጋቸዋል።ትምህርት ቤት እስኪገቡ ድረስ ልናስተውለው ለማንችለው ቋሚ ለሆነ የመማር ጉዳት ያጋልጣቸዋል።

"[የተመጣጠነ ምግብ እጥረት] በሽታን የመከላከል አቅምን በማዳከም ለበሽታዎች በጣም ተጋላጭ ያደርጋቸዋል።

"ብዙ ሰዎች ሙሉ በሙሉ ያልተረዱት አንድ አስፈላጊ ነገር በልጃገረዶች ላይ በትክክል መሃንነት ሊያስከትል የሚችል የተመጣጠነ ምግብ እጥረት አለ። እና እነዚህ ሴቶች ከፀነሱ ዝቅተኛ ክብደት ያላቸው ሕፃናትን የመውለድ እድላቸው ከፍተኛ ነው።"

ለከፋ የአጥንት መሳሳት (Osteoporosis) የመጋለጥ እድላቸውም ሰፊ ነው።

"እድሜያቸው እየጨመረ ሲሄድ አጥንቶቻቸው በቀላሉ ስለሚሰበር የሰውነት ክብደታቸውን በበቂ ሁኔታ መሸከም አይችሉም፤ስለዚህ ትንሽ ክስተት እንኳን ወደ ስብራት ሊመራ ይችላል" ብለዋል ዶክተር አሊባባ።

የምግብ እጥረትን እንዴት ማከም ይቻላል?

ፕሮፌሰር ራይት "ለዚህ ቀውስ ምላሽ ለመስጠት ሁለት መሠረታዊ መንገዶች ያስፈልጋሉ፤ እነዚህም ወደ ጋዛ የሚገቡ ተጨማሪ ምግቦች እና በጣም ውድ የሆኑ የሕክምና ምግቦችን ማቅረብ ናቸው" ብለዋል ።

"ምግብ በአስቸኳይ ለሕጻናት እና እናቶቻቸው መቅረብ አለበት።"

"ጡት ማጥባት ለጨቅላ ሕጻናት በጣም አስተማማኝ እና ንፅህናው የተጠበቀ ምግብ ነው፤ ነገር ግን ሕጻኑን እንድትመግብ እናቲቱን መመገብ አለብን፤እና ትክክለኛው ፈተና ከወንዶች ይልቅ በትክክል እናቶች እርዳታው እንደደረሳቸው ማረጋገጥ ነው።

"ዋናው መልዕክት ሕጻናት እና እናቶች ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል፤ ደግሞ ብዙም አያስፈልጋቸውም።"

በሕክምና ሙያ የሰለጠኑት የቢቢሲ ጋዜጠኛ ስሚማ ሙንዳሳድ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በተለይ በልጆች ላይ የከፋ መሆኑን እና ሕክምናውም ሁልጊዜ ቀላል አለመሆኑን ይናገራሉ።

በከባድ ሁኔታዎች፣ አንድ ሰው መዋጥ በማይችልበት ጊዜ፣ በሆስፒታል ወይም በክሊኒክ ውስጥ የሚሰጥ ልዩ የተመጣጠነ ምግብ አለ በተጨማሪም "ለኢንፌክሽን ወይም ሌሎች ችግሮች ሕክምና ሊያስፈልጋቸው ይችላል" ብለዋል።

"በአንዳንድ ሁኔታዎች አንድን ሰው በፍጥነት ወይም የተሳሳተ ምግብ መመገብ አደገኛ ሊሆን ይችላል።

"መልሱ ታድያ ምግብ ማግኘት ብቻ አይደለም፤ትክክለኛውን ምግብ ማግኘት ነው።ይህንን ለመደገፍ ደግሞ የሚሰራ የጤና አጠባበቅ ስርዓት መኖር አለበት።"