ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከጋዛ ህዝብ ውስጥ አንድ ሶስተኛ ገደማው ለቀናት ምግብ እንደማይመገብ የተባበሩት መንግሥታት አስታወቀ
በጋዛ ሰርጥ ከሚገኙ ሶስት ሰዎች አንዱ ምግብ ሳይመገብ ለቀናት እንደሚቆይ የተባበሩት መንግስታት የምግብ እርዳታ ፕሮግራም አስጠነቀቀ።
የዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) ባወጣው መግለጫ፤ "የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እየጨመረ በመምጣቱ 90 ሺህ ሴቶች እና ህፃናት አስቸኳይ ህክምና ያስፈልጋቸዋል" ብሏል።
በዚህ ሳምንት በጋዛ ያለውን ርሃብ በተመለከተ የሚወጡ ማስጠንቀቂያዎች ተጠናክረዋል።
በሀማስ የሚመራው የፍልስጤም ግዛት የጤና ሚኒስቴር፤ አርብ ዕለት ዘጠኝ ተጨማሪ ሰዎች በምግብ እጥረት ምክንያት መሞታቸውን ያስታወቀ ሲሆን ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በርሃብ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 122 ደርሷል።
ወደ ጋዛ የሚገቡትን የእርዳታ አቅርቦቶች በሙሉ የምትቆጣጠረው እስራኤል፤ ወደ ግዛቱ የሚገቡ እርዳታዎች ላይ ምንም ዓይነት ገደብ እንደሌለ በመግለጽ፤ ለየትኛውም የምግብ እጥረት ሀማስን ተጠያቂ ታደርጋለች።
አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ዩናይትድ ኪንግደም የፓርላማ አባላት መንግስት ለፍልስጤም ሀገርነት እውቅና እንዲሰጥ የሚጠይቀውን ደብዳቤ መፈረማቸው ተከትሎ፤ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኬር ስታርመር ዩናይትድ ኪንግደም በአየር እርዳታ ወደ ጋዛ መጣልን በተመለከተ ሚና እንደምትጫወት አርብ ዕለት ጠቁመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ይህንን የገለጹት፤ በመጪዎቹ ቀናት የእርዳታ አውሮፕላኖች ወደ ጋዛ በመብረር እርዳታ እንዲጥሉ ሊፈቀድ እንደሚችል አንድ የእስራኤል የደህንነት ባለስልጣን ከተናገሩ በኋላ ነው።
ይሁን እንጂ ይህ አካሄድ፤ በበቂ ሁኔታ እርዳታዎች ወደ ጋዛ ለማድረስ የማያስችል መንገድ እንዳልሆነ የእርዳታ ድርጅቶች ከዚህ ቀደም አስጠንቅቀዋል።
ስታርመር፤ "እስራኤል ሀገራት በአየር የሚጣል እርዳታ ወደ ጋዛ እንዲደርስ የፈቀደችው እጅግ ዘግይታ ነው። ነገር ግን በዚህ መንገድ እርዳታ ለማድረስ የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን" ሲሉ ዘ ሚረር በተሰኘው የሀገሪቱ ጋዜጣ ላይ ፅፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በተጨማሪም ዩናይትድ ኪንግደም የህክምና እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሕፃናት ህክምና ለመስጠት የምታደርገውን "ጥረት በአስቸኳይ እያፋጠነች" መሆኑን ተናግረዋል።
የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን፤ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ዮርዳኖስ በአየር የሚጣሉ እርዳታዎችን በቅርቡ እንደሚያደርሱ ቢዘግቡም፤ አንድ የዮርዳኖስ ከፍተኛ ባለስልጣን ሠራዊቱ ይህን ለማድረግ ገና ከእስራኤል ፈቃድ አለማግኘቱን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፤ እርምጃውን "ለልግመት ማደናገሪያ" ሲል የእስራኤል መንግስት ተግራባዊ ስራ እያከናወነ አለመሆኑን ለመሸፈን የሚደረግ ማደናገሪያ እንደሆነ ገልጿል።
ይህ እርምጃው የተገለጸው ጋዛ ውስጥ ያለውን ሰብአዊ ሁኔታ በተመለከተ የሚነሳው ዓለም አቀፍ ስጋት እያደገ መምጣቱን ተከትሎ ነው።
አርብ ዕለት ጀርመን፣ ፈረንሳይ እና ዩናይትድ ኪንግደም፤ እስራኤል ወደ ግዛቱ የሚደረስው "የእርዳታ ፍሰት ላይ ያሉትን ገደቦች በአስቸኳይ እንድታስወግድ" ጠይቀዋል።
ሀገራቱ በጋራ ባወጡት መግለጫ፤ "በጋዛ እየታየ ያለውን የሰብአዊ አደጋ" እና ጦርነቱ ራሱ በአስቸኳይ እንዲቆም ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን እስራኤል "በዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ህግ የተጣለባትን ግዴታ መወጣት" እንዳለባትም አሳስበዋል።
"ለሲቪል ሕዝብ አስፈላጊ የሆነ የሰብዓዊ እርዳታ መከልከል ተቀባይነት የለውም" ሲሉም በመግለጫቸው ወቅሰዋል።
የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፤ "በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ውስጥ በብዙዎች ዘንድ የምናየው ግድየለሽነት እና እርምጃ አለመውሰድ፤ የርህራሄ ማጣት፣ የእውነት እጥረት፣ ሰብአዊነት እጥረት ደረጃ ለማብራራት" እንኳ እንደማይችሉ ተናግረዋል።
ዋና ፀሀፊው በአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ በአሜሪካ እና በእስራኤል የሚደገፈው የጋዛ ሂውማኒተሪያን ፋውንዴሽን (GHF)፤ በተባበሩት መንግስታት የሚመራውን የእርዳታ አቅርቦት ስርዓት በመተካት ማሰራጨት ከጀመረበት ከግንቦት 20/2017 ዓ.ም. አንስቶ ከ1,000 በላይ ፍልስጤማውያን ምግብ ለማግኘት ሲሞክሩ መገደላቸውን ገልጸዋል።