ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ምዕራባውያን ለዩክሬን ያስታጠቁት እጅግ ዘመናዊ ከባድ የጦር መሳሪያዎች
አንድ ዓመት ሊሞላው የተቃረበው የሩሲያ ወረራ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከ30 በላይ አገራት የወታደራዊ ቁሳቁሶች ድጋፍን ለዩክሬን ሰጥተዋል።
በቅርቡም ጀርመን እና ዩናይትድ ስቴትስ የዩክሬን ባለሥልጣናት በጉጉት እየጠበቋቸው ያሉትን ዘመናዊ ታንኮች ለመስጠት ቃል ገብተዋል።
ሁለቱም አገራት በዚህ ዘመን የጦር መሳሪያ አቅርቦት ውስጥ እጅግ የረቀቁ እና በውጊያ ላይ ከፍተኛ ውጤት ያስገኛሉ የተባሉትን ታንኮች ለመስጠት የሚያስችላቸውን ውሳኔያቸውን ለማሳወቅ የወራት ፈጅቶባቸዋል።
ከዚህም በኋላም ታንኮቹን ወደ ዩክሬን ልኮ ውጊያ ላይ ለማሰማራት ወራትን እንደሚፈልግ የጦር ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ቢሆንም ግን አሁን ጀርመን 14 ሊዮፓርድ 2 እንዲሁም አሜሪካ ደግሞ 32 ኤብራምስ ኤ1 የተባሉትን ታንኮች ለዩክሬን ለማስታጠቅ ቃል ገብተዋል።
ዩናይትድ ኪንግደምም ከሁሉም ቀድማ ለዩክሬን ቻሌንጀር 2 የተባሉትን 14 ታንኮች ለመስጠት ቃል መግባቷ ይታወቃል።
በተጨማሪም ጀርመን ከዚህ በፊት ሊዮፓርድ 2 የተባሉትን ታንኮች አስታጥቃቸው የነበሩ አገራት፣ ለዩክሬን አሳልፈው መስጠት ከፈለጉ ፈቅዳላቸዋለች።
ታንኮች
የዩክሬን ፕሬዝዳንት አገራቸውን ለመከላከል እና የተያዙባቸውን ግዛች ለማስለቀቅ ምዕራባውያን ታንኮችን እንዲያስታጥቋቸው በተደጋጋሚ ሲጠይቁ ቆይተዋል።
ሊዮፓርድ 2 የተባለው ጀርመን ሰራሽ ዘመናዊ ታንክ፣ በርካታ የአውሮፓ አገራት ሠራዊቶች የታጠቋቸው ሲሆኑ፣ ከሌሎች የምዕራባውያን ታንኮች በተለየ ቀላል ጥገና የሚፈልጉ እና ዝቅተኛ ነዳጅ የሚጠቀሙ ናቸው።
ነገር ግን የጦርነቱን መቀስቀስ ተከትሎ ምዕራባውያን ለዩክሬን ዘመናዊዎቹን ታንኮች ከመስጠት ይልቅ ሶቪየት ሰራሽ ታንኮችን እንዲታጣቁ ነበር የፈለጉት። ምክንያቱም ዩክሬን የምትጠቀመው እነዚህን አይነት ታንኮች በመሆኑ ለማንቀሳቀስ እና ለጥገና በቂ አባላት በሠራዊቷ ውስጥ አሉ በማለታቸው ነው።
የኔቶ አባል አገራት የሚጠቀሙባቸውን ታንኮች ለመስጠት የሚያስፈልጉ የአቅርቦት እና የሰለጠነ የሰው ኃይል የሌላት ዩክሬን ታንኮቹን በአስፈላጊው ሁኔታ ለመጠቀም ትቸገራለች ብለው በመስጋታቸው አስካሁን ሳያስታጥቋት ቆይተዋል።
ነገር ግን ዩክሬን የኔቶ አገራት የሚጠቀሙባቸውን ከባድ የጦር መሳሪያዎችን ለመታጣቅ ዝግጁ መሆኗን ባለሥልጣናቷ ይናገራሉ።
ከሁሉ ቀድማ ዩናይትድ ኪንግደም 14 ቻሌንጀር 2 የተባሉትን ታንኮች ለዩክሬን እንደምትሰጥ አስታውቃለች። እነዚህ ታንኮች የብሪታኒያ ጦር የታጠቃቸው ዘመናዊ ከባድ የጦር መሳሪያዎች ናቸው።
ዩክሬን ከተፈጸመባት ወረራ በፊት በሶቪየት ኅብረት ዘመን የተሰሩትን ቲ-72 ታንኮችን ታጥቃ የነበረ ሲሆን፣ ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላም የቀድሞ የሶቪየት አጋሮች ከነበሩት ከፖላንድ፣ ከቼክ ሪፐብሊክ እና ከሌሎች አገራት 200 የሚደርሱ ቲ-72 ታንኮችን በድጋፍ አግኝታለች።
አሜሪካንም ለዩክሬን 31 ኤብራምስ የተባሉ ዘመናዊ ታንኮችን እንደምትሰጥ አስታውቃለች። አገራቸው ታንኮቹን ለዩክሬን ለማስታጠቅ መወሰኗን ባስታወቁበት ጊዜ ፕሬዝዳንት ባይደን ታንኮቹ “በዓለም ላይ ካሉ ሁሉ ያላቁ” በማለት ገለጸዋቸዋል።
ጨምረውም የዩክሬን ወታደሮች ታንኮቹን ለመጠቀም እንዲችሉ በአስቸኳይ ሥልጠና መስጠት እንደሚጀምሩ ቢያሳውቁም፣ ነገር ግን ታንኮቹ መቼ ወደ ዩክሬን ጦር ግንባሮች እንደሚደርሱ ግልጽ አይደለም።
የውጊያ ተሽከርካሪዎች
ወታደራዊ ባለሙያዎች እንደሚሉት አንድ ሠራዊት በጦር ሜዳዎች ላይ ለሚያስመዘግበው ስኬት የሚያሰልፋቸው መጠነ ሰፊ ትጥቆች በተቀናጀ ሁኔታ ከአስፈላጊ አቅርቦቶች ጋር መገኘታቸው ወሳኝ ነው።
ስትራይከር የተባለው ብረት ለበስ ተሽከርካሪ ለዩክሬን ከተሰጡ በርካታ ወሳኝ የጦር ሜዳ ተሽከርካሪዎች መካከል አንዱ ነው።
አሜሪካ ከዚህ በፊት ከሰጠቻቸው በተጨማሪ 90 ስትራይከር ብረት ለበስ የጦር ሜዳ ተሽከርካሪዎችን በቅርቡ እንደምትልክ አረጋግጣለች።
ከዚህ ባሻገርም ሌሎች በቅርቡ በአሜሪካ ለዩክሬን ጦር ከተሰጡ የጦር ተሽከርካሪዎች በተጨማሪ 59 ብራድሊ የእግረኛ ወታደሮች የውጊያ መኪኖች ይገኙበታል።
እነዚህ ተሽከርካሪዎች ኢራቅ ውስጥ የአሜሪካ ወታደሮች በስፋት ሲጠቀሙበት ነበር።
ብራድሊ የውጊያ ተሽከርካሪዎች ከሩሲያውያኑ አቻቸው ጋር ሲነጻጸሩ ከባድ እና በተሻለ ሁኔታ ብረት ለበሶች ናቸው።
ይህ ተሽከርካሪ ባለሰንሰለት መድፍ እና ፀረ ታንክ ሚሳኤሎችን የታጠቀ ሲሆን፤ በእግረኞች፣ በቀላል እና በከባድ ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎ ላይ ለሚፈጸም ጥቃት ውጤታማ ነው።
የአየር መከላከያ
ባለፈው ታኅሣሥ ወር አሜሪካ ለዩክሬን የአየር መከላከያ አገልግሎት የሚውለውን ፓትሪዮት የተባለው የሚሳኤል ሥርዓትን መላኳን ያሳወቀች ሲሆን፣ በተከታይነትም ጀርመን እና ኔዘርላንድስም በቅርቡ ተመሳሳይ ድጋፍ አድርገዋል።
ይህ በጣም ዘመናዊ የሆነው የአየር መከላከያ ሥርዓት እንደሚታጠቀው የሚሳኤል አይነት አስከ 100 ኪሎ ሜትሮች ርቅተ ድረስ የመሸፈን አቅም አለው።
መሳሪያውን ለመጠቀም የተለየ ሥልጠና ለዩክሬናውያን መስጠት የሚያስፈልግ ሲሆን፣ ይህም ጀርመን ውስጥ በሚገኘው የአሜሪካ ሠራዊት ጦር ሰፈር ውስጥ ተሰጥቷል።
ነገር ግን መሳሪያውን አገልግሎት ላይ ለማዋል ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቅ ነው። አንድ ፓትሪዮት ሚሳኤል አስከ 3 ሚሊዮን ዶላር ዋጋን ይፈልጋል።
ከጦርነቱ መጀመር አንስቶ ዩክሬን የሶቪየት ዘመን ስሪት የሆኑትን ኤስ-300 ከምድር ወደ አየር የሚተኮሱ የአየር መከላከያ ሥርዓቶችን ከሩሲያ የሚፈጸምባትን ጥቃት ለመከላከል ስትጠቀም ቆይታለች።
ባለፈው ዓመት የካቲት ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ዩክሬን 250 የሚሆኑ ኤስ-300 የአየር መከላከያዎች ታጥቃ ነበር።
ይህንን የአየር መከላከያ መሳሪያ የሚያስፈልገውን ተተኳሾች እና መለዋወጫዎች ተመሳሳይ መሳሪያ ካላቸው ከሌሎች የቀድሞ ሶቪየት አገራት ለማሟላት ተሞክሯል። የተወሰኑትንም ከስሎቫኪያ አግኝታለች።
አሜሪካ በተጨማሪም ‘ናሳማ’ የተባለውን ከምድር ወደ አየር የሚተኮስ የአየር መከላከያ ሥርዓት የመጀመሪያውን ድጋፍ ባለፈው ኅዳር ሰጥታለች።
እንዲሁም ዩናይትድ ኪንግደም ዝቅ ብለው የሚበሩ አውሮፕላኖችን በቅርብ ርቀት መትቶ ለመጣል እንደሚያስችሉ የሚነገርላቸውን በርካታ ስታርስትሪክ የሚባሉትን የአየር መከላከያ ሥርዓቶች ለዩክሬን አበርክታለች።
ጀርመን በበኩሏ አስከ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ድረስ የቀረቡ የሚሳኤል ጥቃቶችን መትቶ የሚጥለውን አይአርአይኤስ-ቲ የተባሉትን የአየር መከላከያ ሥርዓትን ለዩክሬን አስታጥቃለች።
የረጅም ርቀት ሮኬቶች
አሜሪካ ዩክሬንን ካስታጠቀቻቸው የጦር መሳሪያዎች መካከል ረጅም ርቀት መጓዝ የሚችሉ ኤም142 ሂማርስ የተባሉት የሮኬት ማስወንጨፊያዎች ይገኙበታል። በርካታ የአውሮፓ አገራትም ተመሳሳይ ሮኬቶችን ሰጥተዋል።
እነዚህ ሂማርስ የተባሉት ሮኬት ማስወንጨፊያዎች ባለፈው ኅዳር ወር በደቡባዊ ግንባሮች በተለይ ደግሞ በኼርሶን በኩል በተደረጉ ውጊያዎች የዩክሬን ኃይሎች የሩሲያን ሠራዊት ወደ ኋላ እንዲያፈገፍግ ለማድረግ ወሳኝ ነበሩ ተብሎ ይታመናል።
የሂማርስ እና የሌሎች መሳሪያዎች የርቀት ስኬታማነት በዋናነት የሚወሰነው በሚቀርብላቸው የተተኳሽ አይነት ነው። ነገር ግን ረጅም ርቀት ሊጓዙ የሚችሉ ተተኳሾች በምዕራባውያኑ ለዩክሬን እንዳልቀረበላት ይታመናል።
ተገቢው ተተኳሽ ለዩክሬን የሚቀርብላት ከሆነ ሩሲያ ካላት ስመርች ተብሎ ከሚጠራው ተመሳሳይ መሳሪያ ጋር ሲወዳደር አስከ 80 ኪሎ ሜትር ሊጓዝ ስለሚችል የበለጠ አቅም ይኖረዋል።
በተጨማሪም ይህ ሂማርስ የተባለው የሮኬት ማስወንጨፊያ ሥርዓት ኢላማውን በመምታት በኩል ከሩሲያ አቻው አንጻር ስኬታማ ነው ይባልለታል።
ሆዊትዘር
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ከከፈተች በኋላ ወታደሮቿ ከዋና ከተማዋ ኪዬቭ ሲያፈገፍጉ፣ ከባድ ውጊያ ይደረግበት በነበረው ምሥራቃዊ የዩክሬን ክፍል ውጊያው ማዕከል በነበረበት ጊዜ መድፍ በጣም አስፈላጊ ነበረ።
ይህንንም ፍላጎት ለማሟላት አውስትራሊያ፣ ካናዳ እና አሜሪካንን ጨምሮ ሌሎች አገራት ኤም777 ሆዊትዘር የተባሉትን ዘመናዊ መድፎች እና ተተኳሾቻቸውን ለዩክሬን አስታጥቀዋል።
ይህ ኤም777 የተባለው ዘመናዊ መድፍ ከሚመታው ርቀት አንጻር የሩሲያ ሠራዊት ከታጣቀው ጋር ሲነጻጻር የላቀ እንደሆነ ይታመናል።
ፀረ ታንክ
በአንድ ምት ብቻ ታንኮችን እንዲያወድሙ ተደርገው የተሰሩት ኤንላው የተባሉት ፀረ ታንክ መሳሪያዎች በከፍተኛ ቁጥር ለዩክሬን ጦር ከምዕራባውያኑ ተሰጥቷል።
ይህንን ፀረ ታንክ መሳሪያን ለመጠቀም የተወሰነ ሥልጠና ብቻ የሚያስፈልግ ሲሆን፣ በቅርብም ሆነ በርቀት የሚንቀሳቀስን ኢላማ በተሳካ ሁኔታ የማውደም አቅም አለው።
ሩሲያ ወረራዋን ጀምራ ወደ ዋና ከተማ ኪዬቭ ስትገሰግስ እነዚህ መሳሪያዎች የወታደሮቹን እንቅስቃሴ በመግታት በኩል በጣም ጠቃሚ ሚና እንደነበራቸው ይነገራል።
ድሮኖች
ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ውስጥ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው። ድሮኖች ለቅኝት፣ ኢላማዎችን ለማጥቃት እንዲሁም ከባድ ቁሶችን በማንቀሳቀስ በኩል አገልግሎት እየሰጡ ነው።
ከወራት በፊት ቱርክ ባይራክታር ቲቢ2 የተባሉ ወታደራዊ ድሮኖችን ለዩክሬን በሽያጭ አቅርባለች። በተጨማሪም የድሮኖቹ አምራች ዩክሬንን ለመደገፍ በተሰበሰበ መዋጮ አማካይነት ድሮኖችን ሰጥቷል።
ባይራክታር ቲቢ2 አሜሪካ ከምትሰራቸው ድሮኖች አንጻር ርካሽ ሲሆን፣ በጦርነት ውስጥ ለቀጥታ ጥቃት ወይም ከሌሎች የጦር መሳሪያ ሥርዓቶች ጋር በመቀናጀት ጥቃቶችን ለማካሄድ ያግዛል።
ወታደራዊ ተንታኞች እንደሚሉት ባይራክታር ቲቢ2 ኢላማዎችን በመምታት በኩል በከፍተኛ ደረጃ ውጤታማ ነው።
በ25,000 ጫማ ከፍታ ላይ መብረር የሚችለው ይህ ድሮን ዝቅ በማለት በጨረር በሚመሩ ቦምቦች ኢላማዎችን ማውደም ይችላል።