ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በርካታ የአውሮፓ አገራት ለዩክሬን ተጨማሪ ከባድ መሳሪያዎችን ሊያስታጥቁ ነው
በዩክሬን እና በሩሲያ መካከል የሚካሄደው ጦርነት መልሶ እየተባባሰ ባለበት በአሁኑ ወቅት የፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪን ጥሪ ተከትሎ ተጨማሪ አገራት ምላሽ እየሰጡ ነው።
ሐሙስ ዕለት ኢስቶኒያ ውስጥ በሚገኝ አንድ የጦር ሰፈር ውስጥ ስብሰባ ካደረጉ በኋላ በርካታ የአውሮፓ አገራት ተጨማሪ ወታደራዊ ድጋፍ ለዩክሬን ለመስጠት አዲስ ቃል ገብተዋል።
ዩክሬን የሩሲያ ሠራዊትን ለመመከት ለምታደርገው ጥረት ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ሌላ ዙር 600 ብሪምስቶን የተባሉ ሚሳኤሎችን ትሰጣለች ተብሏል።
ዛሬ አርብ ደግሞ 50 አገራት የሚሳተፉበት እና ለዩክሬን የሚቀርበውን ወታደራዊ ድጋፍ ለማቀናጀት የሚያግዝ ስብሰባ ከመካሄዱ በፊት ነው አውሮፓውያኑ በየበኩላቸው ቃል የገቡት።
የ11 አገራት ተወካዮች በተሳተፉበት የሐሙሱ ስብሰባ ላይ ዩክሬን የተያዙባትን ግዛቶች ለማስለቀቅ እና ተጨማሪ የሩሲያ ሠራዊት ግስጋሴን ለመከላከል አዳዲስ የድጋፍ ዕቅዶችን አስታውቀዋል።
በዚህም ዘጠኝ አገራት ማለትም ዩኬ፣ ፖላንድ፣ ላትቪያ፣ ሊቱዋኒያ፣ ዴንማርክ፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ኢስቶኒያ፣ ኔዘርላንድስ እና ስሎቫኪያ ድጋፍ ለመስጠት ቃል ገብተዋል።
ለዩክሬን የሚሰጠው ወታደራዊ ድጋፍን በተመለከተም በወጣው የጋራ መግለጫ ላይ አገራቱ የሚያደርጉት ድጋፍ በዝርዝር ተገልጿል።
- ዩኬ - 600 ብሪምስቶን ሚሳኤሎች
- ዴንማርክ - 19 ፈረንሳይ ሰራሽ ሲዛር የተባለ በእራሱ የሚንቀሳቀስ ሆዊትዘር መድፎች
- ኢስቶኒያ - ሆዊተዝር መድፎች፣ የመድፍ አረሮች፣ ድጋፍ ሰጪ ተሽከርካሪዎች እና ፀረ ታንክ ፈንጂ አስወንጫፊዎች
- ላትቪያ - ስቲንገር የአየር መቃወሚያዎች፣ ሁለት ሄሊኮፕተሮች እና ድሮኖች
- ሊትዋኒያ - አየር መቃወሚያ መድፎች እና ሁለት ሄሊኮፕተሮች
- ፖላንድ - ኤስ-60 አየር መቃወሚያ መድፎች ከ70,000 ተተኳሾች ጋር
- ቼክ ሪፐብሊክ - ከፍተኛ መጠን ያላቸው ጥይቶች እና መድፎች
- ኔዘርላንድ ደግሞ ለዩክሬን የምትሰጠውን ወታደራዊ ድጋፍ ዛሬ አርብ ለማሳወቅ ቃል ገብታለች።
የዩናይትድ ኪንግደም የመከላከያ መሥሪያ ቤት ኃላፊ ቤን ዋላስ እንደተናገሩት፣ ይህ ዓመት ዩክሬንን በማጠናከር በሩሲያ ላይ የበላይነትን አግኝታ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት መብቷ የሆነውን ሉአላዊነቷን የማስከበር ጥረቷ የተሳካ እንዲሆን ማድረግ አለብን ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ በዓለም የምጣኔ ሀብት መድረክ ላይ ለተሰበሰቡ አገራት በቪዲዮ ባስተላለፉት ጥሪ፣ ታንኮችን እና መድፎችን ጨምሮ ሌሎች ከባድ መሳሪያዎችን በፍጥነት እንዲሰጧቸው ጠይቀዋል።
ነገር ግን ምዕራባውያን ዩክሬንን ለመደገፍ ቢሊዮኖች ቢመድቡም፣ ትልቅ ጥያቄ የሆነው ከባባድ ታንኮች መላክ እንዳለባቸው እና ማን እነዚህን መሳሪያዎች እንደሚሰጥ በመወሰኑ ላይ ነው።
ዩክሬን ጀርመን ሰራሽ የሆኑትን ሌፓርድ የተባሉትን ታንኮች እንዲሰጣት እየጠየቀች ሲሆን፣ የጀርመኑ መራሄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝም ታንኮችን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለዩክሬን እንዲያቀርቡ በአገር ውስጥ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ጫና በርትቶባቸዋል።
ፖላንድ እና ፊንላንድም ያሏቸውን ሌፓርድ ታንኮች ለመስጠት ፈቃደኛ ቢሆኑም፣ የአምራቿ አገር የጀርመንን ፈቃደኝነት ማግኘት ይኖርባቸዋል።
የፖላንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ማቱዩዝ ሞራዌኪ፣ ታንኮቹን ለዩክሬን ለመስጠት ካቀረቡት ጥያቄ አንጻር የጀርመን ምላሽ አውንታዊ ሊሆን እንደማይችል ስጋት እንዳላቸው ተናግረዋል።
ዩኬ የሠራዊቷን 14 ቻሌንጀር 2 የተባሉ ከባድ ታንኮችን ለዩክሬን ለመስጠት ፈቃደኛ በመሆን የመጀመሪያዋ አገር ሆናለች።
ለዩክሬን መከላከያ ድጋፍ ለመስጠት የሚመክር አሜሪካንም የምትገኝበት የአጋሮች ስብሰባ ዛሬ አርብ ጀርመን ውስጥ በሚገኘው የራምስታይን የአየር ኃይል ሰፈር ተጨማሪ ወታደራዊ ድጋፍ ለየክሬን በመስጠት ዙሪያ ይመክራል ተብሏል።