ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከሙድሪክ ዝውውር ከተገኘው ገንዘብ ክለቡ ለዩክሬን ሠራዊት 22 ሚሊዮን ዩሮ ሊሰጥ ነው
ዩክሬናዊው ሚካይሎ ሙድሪክ ወደ ቼልሲ መዛወሩን ተከትሎ የሻክታር ዶኔስክ ፕሬዝዳንት የሆኑት ሪናት አክሜልቶቭ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ዩክሬንን ለመደገፍ 22 ሚሊዮን ዩሮ እንደሚለግሱ አስታወቁ።
ሙድሪክ ከሻክታር ወደ ቼልሲ ከተዛወረ በኋላ ነው ክለቡ ለዩክሬን ልገሳ እንደሚያደርግ ያስታወቀው።
ሙድሪክ ወደ ቼልሲ የተዛወረው በ89 ሚሊዮን ዩሮ ሲሆን፣ ይህም በዩክሬን እግር ኳስ ታሪክ ከፍተኛው ክፍያ ነው።
ገንዘቡ በማሪዮፖል ግዛት ለሚገኙ የዩክሬን ወታሮች እና ቤተሰቦቻቸው ድጋፍ ለሚያደርግ ፕሮጀክት እንደሚሰጥ ተገልጿል።
“ሥልጡኑ ዓለም ዩክሬንን በመደገፉ አመሰግናለሁ። ስለ ዩክሬን እግር ኳስ ማውራት የቻልነው በዩክሬን ወታደሮች፣ በዩክሬን ሕዝብ እና በሥልጡኑ ዓለም ድጋፍ አማካይነት ነው” ብለዋል የክለቡ ፕሬዝዳንት።
ሙድሪክ ክለቡን ለቆ ወደ ቼልሲ መሄዱ ድብልቅ ስሜት እንደፈጠረባቸውም ተናግረዋል።
“ሕልሜ የአውሮፓን ዋንጫዎች ማንሳት መሆኑን ደብቄ አላውቅም። እንደ ሙድሪክ ያሉ ተጫዋቾችን ወደ ክለባችን በመጋበዝ የአውሮፓን ዋንጫዎች እናነሳለን። አሁን ሩሲያ በከፈተችብን ወረራ ምክንያት ይህን ማድረግ አንችልም” ብለዋል።
ከሙድሪክ ዝውውር የተገኘው ገንዘብ በማሪዮፖል ግዛት ለሕክምና፣ ለሥነ ልቦና ድጋፍ እና ሌሎችም የበጎ አድራጎት አገልግሎቶች እንደሚውል ተናግረዋል።
በዩክሬን ዶንባስ አሬና ክለባቸው ከቼልሲ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ እንደሚያደርግ ሻክታር ዶኔስክ ፕሬዝዳንት የሆኑት ሪናት አክሜልቶቭ ገልጸዋል።
የ22 ዓመቱ ሙድሪክ እንዴት ከቼልሲ ጋር እንደተፈራረመ “አለማወቃቸውን” የቼልሲ ኃላፊ ግራሀም ፖተር ተናግረዋል። “እንዴት እንደመጣ ባለውቅም እኛ ጋ በመምጣቱ ደስተኞች ነን” ብለዋል።
ተጫዋቹ ስምምነቱ የስምንት ዓመት ተኩል ነው። ቼልሲን ከመቀላቀሉ በፊት አርሰናል ሊገባ እንደሚችል ተገምቶ ነበር።
“ትኩረቴ ጨዋታው ላይ ነው። ድንቅ ተጫዋች ነው። ወጣት ነው። ፕሪሚየር ሊግን እስኪላመድ ትንሽ ጊዜ ሊፈልግ ይችላል” ብለዋል ግራሀም ፖተር።
ተጫዋቹ በዚህ ወር ለቸልሲ በመፈረም አምስተኛው ነው።
ጃዎ ፌሊክስ ከአትሌቲኮ ማድሪድ በውሰት ሲመጣ፣ ቤኖት ባዲሽሌ፣ ዴቪድ ዳትሮ ፎፋና እና አንድሪ ሳንቶስ ለቼልሲ ፈርመዋል።
ሙድሪክ በዩክሬን በሦስት ክለቦች 47 ጊዜ ተጫውቶ ሁለት ጎል ብቻ ቢያስቆጥርም፣ በቻምፒዮንስ ሊግ ለክለቡ ሦስት ጎል በማስቆጠር መሻሻል አሳይቷል።
በቀጣዩ ቅዳሜ ከሊቨርፑል ጋር ቼልሲ በሚኖረው ግጥሚያ ለመጀመሪያ ጊዜ ይጫወታል ተብሎ ይጠበቃል።