ማንቸስተር እና ሰሜን ለንደን ‘ቀይ’ በሆኑበት ሳምንት አርሰናል እና ዩናይትድ ድል ቀንቷቸዋል

አርሰናል የሰሜን ለንደን ተቀናቃኙ ቶተንሃም ሆትስፐርስን በመርታት በሊጉ ያለውን መሪነት አጠናክሯል።

መድፈኞቹ በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ አናት የተቀመጡ ሲሆን፣ ሁለተኛ ደረጃን ከያዘው ማንቸስተር ሲቲ በስምንት ነጥብ መራቅ ችለዋል።

አርሰናሎች በመጀመሪያው አጋማሽ ባስቆጠሯቸው ሁለት ጎሎች ድል ሲቀዳጁ ባለሜዳው ቶተንሃም ጥርስ አልባ ሆኖ አምሽቷል።

በ14ኛ ደቂቃ ቡካዮ ሳካ ወደ ጎል የሰደዳት ኳስ የቶተንሃሙ በረኛ ኡጎ ሎሪስ ስህተት ታክሎበት ጎል መሆን ችላለች።

የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ 9 ደቂቃዎች እየቀሩት የአርሰናሉ አማካይ ማርቲን ኦዴጋርድ ከበረኛው ሳጥን ውጭ የለጋት ኳስ ድንቅ ጎል ሆናለታለች።

በመጀመሪያው አጋማሽ በጣም ደካማ የነበሩት ቶተንሃሞች በሁለተኛው አጋማሽ አቅማቸውን አጠናክረው ቢመጡም የአርሰናልን በረኛ ሊያልፉ አልቻሉም።

አሮን ራምስዴል ከአንድም ሁለት ሦስት ጎል ሊሆኑ የሚችሉ ሙከራዎችን በማዳን የቡድኑ ባለውለታ ሆኗል።

በሌላ የደርቢ ጨዋታ ማንቸስተር ዩናይትድ ማንቸስተር ሲቲን አስከንድቷል።

ኦልድ ትራፈርድ በተሰኘው የማንቸስተር ዩናይትድ ዕድሜ ጠገብ ስታድዬም የተካሄደው ይህ ጨዋታ በሰሜት መደበላለቅ የታጀበ ነበር።

በመጀመሪያው አጋማሽ ቀያይ ሰይጣኖቹ ጎል ለማስቆጠር በተደጋጋሚ ያደረጉት ሙከራ አልተሳካላቸውም። በተቃራኒው ማንቸስተር ሲቲ የወትሮውን ሆኖ አልተገኘም።

እንደተለመደው ሲቲዎች ኳሱን የተሻለ ቢቆጣጠሩም ወደ ጎል ክልል ሄዶ አደጋ በመፍጠር ግን ዩናይትድ የተሻለ ነበር።

የዚህ ጨዋታው ሁለተኛው አጋማሽ በተለያዩ ስሜቶች እና በአወዛጋቢ ውሳኔዎች የተሞላ ነበር።

ማንቸስተር ሲቲ በሁለተኛው 45 የተሻለ ሲንቀሳቀሱ ቆይተው ተቀይሮ በገባው ግሪሊሽ አማካይነት ቀዳሚነቱን ወሰዱ።

ነገር ግን በዚህ ውጤት ያልተበገሩት ማንቸስተር ዩናይትድ አቻ የምታደርጋቸውን ጎል በብሩኖ ፈርናንዴዝ አማካይነት አስቆጠሩ።

ፈርናንዴዝ ፈንጠዝያውን ሳይጨርስ የመስመር ዳኛው ዳረን ካን ጎሉ ከጨዋታ ውጭ ነው በማለት ሻሩት።

ይህ ያልተዋጠላቸው የማንቸስተር ዩናይትድ ተጨዋቾች የመሃል ዳኛው ስቱዋርት አትዌልን ከበው ያናግሯቸው ጀመር።

የመሃል ዳኛው ከመስመር ዳኛው ጋር ለጥቂት ደቂቃዎች ከመከሩ በኋላ ጎሉ ሕጋዊ ነው ሲሉ አፀደቁ።

ማንቸስተር ዩናይትድ በዚህ ጎል ተነቃቅተው ኖሮ ከደቂቃዎች በኋላ በማርከስ ራሽፈርድ አማካይነት ሁለተኛዋን ጎል አስቆጥረው ፍልሚያው 2 ለ 1 ተገባዷል።

ቢሆንም የፈርናንዴዝ ጎል ከጨዋታው ፍፃሜም በኋላ ማነጋገርና ማከራከሯን ቀጥላለች።

ፈርናንዴዝ ጎሏን ከማስቆጠሩ በፊት ከጨዋታ ውጭ የሆነው ማርከስ ራሽፈርድ ጣልቃ ገብቷል? ወይስ አልገባም? የሚለው ነው አከራካሪ ሆኖ የተገኘው።

የማንቸስተር ደርቢ ውጤትን ተከትሎ ዩናይት ከሲቲ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አንድ ዝቅ አድርጓል።

ኒውካስትል ዩናይትድ በመጨረሻው ደቂቃ በትውልደ ኤርትራዊው አሌክዛንደር ኢሳክ ጎል ፉልሃምን ረትቶ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

በሌሎች ፍልሚያዎች የውጤት አዘቅት ውስጥ የሚገኙት ቼልሲዎች ክሪስታል ፓላስን አንድም ለምንም በመርታት ወደ ድል ተመልሰዋል።

ሌላኛው ውጤት የራቀው ሊቨርፑል ወደ ብራይተን አቅንቶ ሦስት ለባዶ ተረምርሞ ተመልሷል።

ሊቨርፑል ሊጉ ዘጠነኛ፤ ቼልሲ ደግሞ አስረኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።