“ድንገት ስለሄድን ቤተሰቦቼን ሳላገኝ ነው የተመለስኩት” - አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ

ባለፈው ዓመት በተካሄደው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያውያን ሴት አትሌቶች ታላቅ ድል ያስመዘገቡበት ውድድር ነበረ።

በዚህ ውድድር ላይ በ10,000 ሜትር ለተሰንበት ግደይ የወርቅ ሜዳሊያ፣ ጎይተቶም ገብረሥላሴ በማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ፣ ጉዳፍ ፀጋይ በ5,000 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ አስገኝተዋል።

ይህ ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድር ታሪክ ከፍተኛውን የሜዳሊያ ብዛት ባስመዘገበችበት ውድድር ላይ የተሳተፉት የትግራይ ተወላጅ አትሌቶች ከውጤታቸው ጎን ለጎን አነጋጋሪ የሆነ አንድ ጉዳይ ነበር።

እነዚህ ከትግራይ የመጡ አትሌቶች ባለፉት ሁለት ዓመታት በተካሄደው ጦርነት ምክንያት ከቤተሰቦቻቸው ተለያይተው ከባድ ፈተና ውስጥ ቆይተዋል።

አብዛኛዎቹም ከገበሬ ቤተሰብ የመጡ እና ወላጆቻቸው ከፍተኛ ጦርነት በሚካሄድበት እና የስልክ ግንኙነት በሌለበት አካባቢ ስለሚኖሩ ቤተሰቦቻቸውን ለማግኘት ተቸግረው ነበር።

በዚህም ምክንያት በኦሪገን ባስመዘገቡትን የዓለም ሻምፒዮና የድል ስሜታቸውን በእንባ ሲገልጹ ተስተውለዋል።

ለምሳሌ የሴቶችን የማራቶን አዲስ ክብረወሰን ያስመዘገችው እና የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘችው አትሌት ጎይተቶም ገብረሥላሴ በወቅቱ ስለ ድሉ በቢቢሲ ስፖርት ተጠይቃ “ሰላም ሆኖ ወላጆቼ እንደ እኔ እንዲደሰቱ ምኞቴ ነው” በማለት እንባ እንደቀደማት ይታወሳል።

ከውድድሩ በኋላም አትሌቶቹ አዲስ አበባ ሲገቡ ደማቅ አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ የኢትዮጵያ መንግሥት እና የህወሓት መሪዎች የትግራይ አትሌቶች ከወላጆቻቸው ጋር የሚገናኙበትን መንገድ እንዲከፍቱ ጠይቃ ነበር።

ባለፈው ጥቅምት ማብቂያ ላይ የፌደራል መንግሥቱ እና የህወሓት መሪዎች ለሁለት ዓመታት የዘለቀውን ደም አፋሳሽ የእርስ በእርስ ጦርነት ለማስቆም የተኩስ አቁም ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ፣ ከአንድ ዓመት ተኩል በከላይ ተቋርጠው የነበሩት የግንኙነት መስመሮች በፍጥነት መመለስ ጀምረዋል።

ይህንንም ተከትሎ በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ኢትዮጵያን ወክለው የተሳተፉት የትግራይ ተወላጅ አትሌቶች እና አሰልጣኞችን ያካተተው የልኡካን ቡድን በዚህ ሳምንት መጀመሪያ መቀሌ ሲገባም ተመሳሳይ ስሜት ታይቷል።

በትግራይ ክልል ሚዲያዎች ከወላጆቿ ጋር ሲገናኙ ከታዩት አትሌቶች መካከል አትሌት ጎይተቶም ገብረሥላሴ “ሰላም ለሁሉም አስፈላጊ ነው። ወላጆቼ ያገኘሁት ሰላም ስለሆነ ነው። ይህ ለእኔ ሰላም ነው” ስትል ተናግራለች።

የሦስት የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት አትሌት ለተሰንበት ግደይ በበኩሏ፣ ላለፉት ሁለት ዓመታት ከቤተሰቦቿ ጋር መለያየቷ በጣም ከባድ እንደነበር ተናግራለች።

“የሰላም ስምምነቱ ቤተሰቦቻችንን እንድናይ፣ ሥራችንን እንድንሰራ፣ ጦርነቱን እንዲያቆም አስችሏል። በስፖርት ውስጥም ያለውን ሰላም እንሰብካለን፤ ሰላም ካለ ሁሉም ነገር ስለሚኖር እንድታግዙን፣ ባንኮችን እና መንገዶችን እንዲከፈቱ መልዕክቴን አስተላልፋለሁ” ብላለች።

አትሌቶቹ ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ ወደ አዲስ አበባ ቢመለሱም አንዳንዶቹ በጊዜ ውስንነት፣ በትራንስፖርት ችግር እና በስልክ ኔትዎርክ ችግር ምክንያት ቤተሰቦቻቸውን ማግኘት አልቻሉም።

በ2022 የዓለም ሻምፒዮና ሁለት ሜዳሊያዎችን ያስገኘችው ብቸኛዋ ኢትዮጵያዊ አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ አንዷ ናት።

“ቤተሰቦቼ እንደማይመጡ አውቅ ነበር”

አትሌት ጉዳፍ ለቢቢሲ በሰጠችው ቃለ መጠይቅ በመቀለ የነበራቸው ቆይታ አጭር በመሆኑ ቤተሰብ ለማግኘት አስቸጋሪ ጊዜ እንደነበር ተናግሯለች።

በዋናነት ቤተሰቦቿ ከከተማ ርቆ ገጠር ደቡብ ትግራይ ውስጥ አድዋ እና ቦራ እንደሚኖሩ እንዲሁም ወደ መቀለ መምጣት እንዳልቻሉ ተናግራለች።

“ድንገት ነው የሄድነው፤ ስለዚህ ሦስት ሰዓት ብቻ ቆይተን ተመለስን። ኔትዎርክ ደግሞ ስለማይሰራ ስልክ መደወል አልቻልኩም። ከአድዋ ወደ መቀለ ያለው መንገድም ተዘግቷል፤ ወደ ቦራም የስልክ ኔትዎርክ አይሰራም። በዚህ ምክንያት ቤተሰቤ ጋር አልተገናኘሁም። ነገር ግን አብሮ አደጎቼን ማግኘቴ እንዲሁም ክልሉ አይቶ መመለስ የሚፈጥረው ስሜት አለ፤ ደስተኛ ነኝ” ትላለች።

ጉዳፍ በ2022 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሴቶች 5000 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ፣ በ1500 ሜትር የብር ሜዳሊያ አሸንፋለች።

ከዚያ በፊት ጉዳፍ በ2021 የቶኪዮ ኦሊምፒክ በ5,000 ሜትር ሜዳሊያ አግኝታለች። በዚህ ውድድር ያገኘችው ሜዳሊያ የነሐስ ቢሆንም በኦሪገን የወርቅ ሜዳሊያ ለማሸነፍ ችላለች።

“ወደ ትግራይን ደርሶ መመለስ ትልቅ ነገር ስለሆነ ነው የሄድኩት፤ የትውልድ ቦታዬ አይቼ መመለስ ቤተሰብን እንደማየት ነው የምቆጥረው። ትናንት የደገፈንን ሕዝብ አይቶ መመለስ በጣም ደስ ይላል። ነገር ግን ቤተሰቦቼ ከሁኔታው አንጻር እንደማይመጡ አውቅ ነበር” ስትል ተናግራለች።

የቀድሞ የረጅም ርቀት ሯጭ አሰልጣኝ ህሉፍ ይህደጎ በበኩሉ፣ ከአትሌቲክስ ቡድኑ ጋር ወደ መቀሌ ቢሄድም ቤተሰቡን ሳያገኝ ተመልሷል።

“ጉዟችን በድንገት የመጣ ነበር፤ እኛ ግን ሕዝቦቻችንን ናፍቅን ስለነበረ እነሱን ለማየት በጉጉት ሄድን። ሕዝቡ እንደ ቤተሰባችን ስለምናስበው እንጂ ከቅርብ ቤተሰባችን ጋር እንኳን አልተገናኘንም። የእኔ ቤተሰቦች አድዋ ነው ያሉት፤ በአድዋ አካባቢ ደግሞ የኤርትራ ወታደሮች ስላሉ ሊመጡ አይችሉም” ብሏል።

አሰልጣኝ ህሉፍ የአትሌት ጉዳፍ ፀጋይ አሰልጣኝ እና ባለቤት ነው። በተጨማሪም የአትሌት ለምለም ኃይሉ፣ ፍሬወይኒ ኃይሉ፣ ብርቄ ሓየሎም እና ሌሎች በርካታ የትግራይ አትሌቶች አሰልጣኝ ነው።

በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት የዘለቀው የእርስ በርስ ጦርነት በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት፣ ለንብረት ውድመት እና ከሁለት ሚሊዮን በላይ ዜጎች መፈናቀል ምክንያት ሆኗል።

ስሜቶች የተቀላቀሉበት የስኬት ዓመታት

አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ በማዕከላዊ ትግራይ ክልል ቦራ ከተማ ነው የተወለደችው።

ስፖርት በትምህርት ቤት መጀመሯን የምትናገረው ጉዳፍ በ2013 (እአአ) መጨረሻ በኔዘርላንድስ የበተሳተፈችበት መጀመሪያዋ ውድድር አንደኛ ሆና በማጠናቀቅ ሪከርድ መስበሯ ትናገራለች።

በ2021 በፈረንሳይ በ1,500 ሜትር የቤት ውስጥ ውድድር አዲስ ክብረ ወሰን ማስመዝገብ ችላለች።

ጉዳፍ ያለፉት ሁለት ዓመታት በጦርነት ምክንያት ፈታኝ ጊዜ ብታሳልፍም ትልቅ ስኬቶች ማስመዝገቧን ትናገራለች።

“ስናሸንፍ ለቤተሰቦቻችን ደውለው እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት በማይችሉበት ሁኔታ ውስጥ ነበርን። ነገር ግን በሥራችን ላይ ትኩረት አድርገን፣ ባለቤቴም እየረዳኝ ስኬትን ማስመዝገብ ችለናል” በማለት ባለፉት ሁለት ዓመታት ደስተኛ የሆነችባቸውን ስኬቶች ማስመዝገቧን ገልጻለች።

“2021 (እአአ) ለእኔ ጥሩ ዓመት ነበር፤ በዚህ ዓመት ክብረ ወሰን ሰብሬአለሁ። በ3,000 ሜትር በዓለም ሁለተኛ ፈጣን ሰዓት አስመዝግቢያለሁ። 2022 ደግሞ በቤት ውስጥ ውድድር በዓለም 2ኛ ፈጣን ሰዓት ሩጫለሁ። በ5000 እና 1500 ሁለት ወርቅ ያመጣሁበት እና ምርጥ ኢትዮጵያዊ አትሌት ሆኜ የተመረጥኩባቸው ዓመታት ነበሩ።”

አትሌት ጉዳፍ በ5,000 ሜትር ውድድር በቀጥታ ወደ ዓለም ሻምፒዮና በማለፏ በዚህ ውድድር ፈጣን ሰዓት ለመሮጥ እንደምትዘጋጅ ገልጻለች።

በአስቸጋሪ ነገር ግን ከፍተኛ ድል ባስመዘገበችባቸው ባለፉት ሁለት ዓመታት ከሌሎች አትሌቶች ጋር የነበራት መደጋፈፍ ወሳኝ ነበረ። “በአትሌቲክስ ውስጥ በጣም አስፈላጊው ነገር እርስ በርስ መደጋገፍ ነው” ትላለች ጉዳፍ።