ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኤርትራ ሠራዊት ከትግራይ ከተሞች እየወጣ ነው? ነዋሪዎች ምን ይላሉ?
የትግራይ ኃይሎች ትጥቅ እንዲፈቱ እና የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት ከህወሓት መሪዎች ጋር ሰላም እንዲፈጥር ዘላቂ የሆነ የተኩስ አቁም ስምምነት ከተፈረመ ሁለት ወራት ተቆጥረዋል።
ይህንን ተከትሎም ለሁለት ዓመት በዘለቀው ጦርነት በትግራይ ክልል ተቋርጠው የነበሩ መሠረታዊዎቹ የስልክ፣ የኢንተርኔት፣ የአየር ትራንስፖርት እና የባንክ አገልግሎቶች በበርካታ አካባቢዎች ወደነበሩበት እየተመለሱ ነው።
“ሕዝቡ ሰላሙ ሲመጣ ሙሉ በሙሉ ተቀብሎታል። አሁን ከሰላም በቀር ምንም መስማት አይፈልግም። ከሰላም በቀር የሚያውቀው ነገር የለም” ሲሉ አንድ የሽሬ እንዳሥላሴ ነዋሪ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በኅዳር ወር 2015 በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ዘላቂ የሆነ የተኩስ አቁም ስምምነት መደረሱን ተከትሎ ሚሊዮኖችን አፈናቅሎ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ሕይወት ቀጥፏል የተባለው ጦርነት ቆሟል።
ከአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት ውጪ የሆኑ የአጎራባች ክልሎች እና የውጭ ኃይሎች ከክልሉ መውጣት እንዳለባቸው በስምምነቱ ላይ ተጠቅሷል።
ከእነዚህም መካከል ከጦርነቱ ጅማሬ አንስቶ ከፌደራል መንግሥቱ የመከላከያ ሠራዊት ጎን በመሆን ከህወሓት ኃይሎች ጋር ሲዋጋ የነበረው የኤርትራ ሠራዊት ከዚህ ጦርነት ጋር ስሙ በስፋት ሲነሳ ቆይቷል።
እስካሁን የኤርትራ ሠራዊት መውጣትን በተመለከተ በየትኛውም ወገን በይፋ የተባለ ነገር ባይኖርም፣ ባለፈው ሳምንት (ታኅሣሥ 22/2015 ዓ. ም.) አንዳንድ ነዋሪዎች የኤርትራ ወታደሮች ከሽረ እንዳሥላሴ እና ከአክሱም ከተሞች ለቀው እየወጡ ስለመሆናቸው ተናግረው ነበር።
በዚህም የኤርትራ ወታደሮችን የጫኑ በርካታ የጭነት ተሽከርካሪዎች ከአክሱም አቅጣጫ በመምጣት በሽራሮ በኩል ሲያልፉ መታየታቸው ተነግሯል።
ይህንን በተመለከተ ከኤርትራ መንግሥት፣ ከኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ ከህወሓት ባለሥልጣናት የሚያረጋግጥም ሆነ የሚያስተባብል መግለጫ አልተሰጠም።
ይሁን እንጂ አሁንም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የኤርትራ ወታደሮች በሰሜን ምዕራብ እና በማዕከላዊ የትግራይ ዞኖች ውስጥ እንደሚገኙ የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች እና የእርዳታ ሠራተኞች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አብሮ መገበያየት እና አገልግሎት መጠቀም
የሰሜን ምዕራብ ትግራይ ዞን ዋና ከተማ የሆነችው ሽሬ እንዳሥላሴ በፌደራል ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ከሚገኙት የትግራይ ከተሞች አንዷ ናት።
ከተማዋ በኮማንድ ፖስት ሥር ስትሆን ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት በኋላ በከተማዋ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ አይፈቀድም።
ባለፈው ሳምንት የኤርትራ ወታደሮች ሲንቀሳቀሱ ሲታዩ፣ ሠራዊቱ ሙሉ በሙሉ ለቆ እየወጣ እንደሆነ እርግጠኛ እንዳልነበረ የሚያስታውስ አንድ ስሙ እንዲገለጽ ያልፈለገ የከተማዋ ነዋሪ የኤርትራ ወታደሮች አሁንም ከተማዋ ውስጥ እንዳሉ ይናገራል።
“የወታደራዊ ልብሳቸውን እና ትጥቃቸውን ይዘው እናገኛቸዋለን። አንዳንዶች ቤተሰቦቻቸውን አግኝተው ያናግራሉ፤ ምግብ ቤት ውስጥ ከነዋሪው ጋር ተቀላቅለው በልተው ይሄዳሉ። በገበያ ስፍራም የሚፈልጉትን በመግዛት ይገበያያሉ” ይላል።
በአሁኑ ወቅት በከተማዋ ያለውን የፀጥታ ሁኔታ እንዲጠብቁ የተመደቡ የፌደራል ፖሊስ አባላት መሰማራታቸውንም የከተማዋ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ትግራይ ውስጥ ተቀስቅሶ ወደ አጎራባች ክልሎች የዘለቀውን ጦርነት ለማስቆም ሲያደራድሩ የነበሩት የአፍሪካ ኅብረት አሸማጋዮች እና የስምምነቱን አፈጻጸም ይከታተላሉ የተባሉት የአፍሪካ እና የአውሮፓ አገራት አምባሳደሮች ታኅሣሥ 21/2015 ዓ.ም. መቀለ ከገቡ ከአንድ ቀን በኋላ “የኤርትራ ሠራዊት ከትግራይ ከተሞች እየወጣ ነው” የሚል መረጃ ተሰምቷል።
ይህንን ልዩ እንቅስቃሴ ተከትሎ ሠራዊቱ ወደ አዲያቦ ወይም ከሽረ በስተምሥራቅ አቅጣጫ ሲወጣ እና ጥቂት ታንኮችም በከተማዋ ሲያልፉ መታየታቸውን ቢቢሲ ያነጋገራቸው የዐይን እማኞች ይገልጻሉ።
ይሁን እንጂ አሁንም የፌደራል እና የኤርትራ ሠራዊት አባላት በአካባቢዎቹ ውስጥ እንዳሉ ለአንድ የሰብአዊ ዕርዳታ ድርጅት የሚሠራ የሽረ ከተማዋ ነዋሪ ተናግሯል።
“ከከተማዋ ወጣ ብላ ከምትገኘው አዲ ሓኖ ጀምሮ እስከ ሸራሮ ድረስ የኤርትራ ወታደሮች አሉ። በዞኑ ከተሞች እና የወረዳ አስተዳደሮች ውስጥ ደግሞ የፌዴራል ፖሊስ አባላት አሉ። ነገር ግን ከከተሞች ውጭ የኤርትራ ሠራዊት አባላት አሉ” ይላል አስተያየት ሰጪው።
የሠራዊቱ እንቅስቃሴ እንዳለ የሚናገረው ይህ ነዋሪ “ወደ ምሥራቅ ሽረ የሚወጣ የኤርትራ ሠራዊት አለ። የሚወጣ መስሎ ይታያል፤ ወደ የት እንደሚሄድ ግን አይታወቅም። ሽረ ውስጥም ገበያ ውስጥ ሲገበያዩ ይታያሉ” ሲል የተመለከተውን እንቅስቃሴ ይገልፃል።
በተጨማሪም ወታደሮቹ ከነሙሉ ትጥቃቸው በምግብ ቤቶች፣ በካፌ እና በሌሎች የሕዝብ ቦታዎች ከሲቪሉ ጋር ተቀላቅለው ሲመገቡ፣ ሻይ ሲጠጡ እና ሲዝናኑ እንደሚታዩ ያነጋገርናቸው ሌሎች ነዋሪዎች አረጋግጠዋል።
ሌላ ነዋሪ ደግሞ በበኩሉ “እኔ እንደሚመስለኝ ቦታ እየቀየሩ እንጂ ጨርሶ አልወጡም። ለምሳሌ አዲያቦ የነበሩት ወደ አንድሪያ ይሄዳሉ፣ ሽረ የቆዩት ወደ ሸራሮ ይሄዳሉ . . .” ይላል።
“የደኅንነት ስጋት አለብን”
ተሰማ በሚል ስም መጠራትን የመረጠ የአክሱም ነዋሪ በበኩሉ በከተማው ዙሪያ በርካታ የኤርትራ ሠራዊት አባላት መታየታቸውን ገልጿል።
ቀደም ሲል ከተማዋን ለቀው ወጥተው እንደነበር የሚገልጸው ተሰማ ከቅርብ ቀናት ወዲህ ወደ ከተማዋ መመለሳቸውን ተናግሯል።
"እንዳ እየሱስ ተብሎ በሚጠራው የአክሱም አየር ማረፊያ አካባቢ (ከከተማው 6 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ) በብዛት ተሰብስበው ይገኛሉ። እስከ አድዋ መግቢያ ድረስ እንዳሉ ሰምቻለሁ። ከተማው ውስጥ ደግሞ ዕቃ ሲገዙ ይውላሉ” ይላል።
ከሁለት ቀናት በፊት ለሥራ ከሽረ ወደ አክሱም የተጓዘ ሌላ ግለሰብም በቅርብ ቀናት አክሱም ውስጥ የኤርትራ ሠራዊት አባላትን ማየቱን ተናግሯል።
“ከሽረ እስከ አክሱም በሚወስደው መንገድ ላይ የፌደራል እና የኤርትራ ኃይሎች አሉ። ነገር ግን አክሱም ውስጥ በአብዛኛው የኤርትራ ወታደሮች ናቸው ያሉት። በአድዋ ዙሪያም በርካታ ሠራዊት አለ” ይላል።
አክሱም ውስጥ ከምሽቱ 12 ሰዓት በኋላ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እንደማይፈቀድ እና የፌደራል ፖሊስ ዩኒፎርም የለበሱ የፀጥታ ኃይሎች ከተማዋን እንደሚጠብቁ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“የኤርትራ ጦር አባላት በአድዋ አሁንም ስላሉ ብዙ ማውራት አልችልም” በማለት የኤርትራ ሠራዊት ባለበት ሁኔታ አሁንም ሙሉ በሙሉ ደኅንነት እንደማይሰማቸው የከተማዋ ነዋሪ ገልጿል።
የኤርትራ ሠራዊት በጦርነቱ ውስጥ መሳተፍን በተመለከተ በርካታ አገራት ሲቃወሙት የቆዩ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል አሜሪካ በዚሁ ሳቢያ በኤርትራ ጦር እና የደኅንነት ባለሥልጣናት ላይ እንዲሁም በኤርትራ ገዢ ፓርቲ የንግድ ተቋማት ላይ ማዕቀብ መጣሏ ይታወሳል።
ለሁለት ዓመታት በዘለቀው ጦርነት ውስጥ የተሳተፈው የኤርትራ ሠራዊት ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በመፈጸም እና መሠረተ ልማቶችን በማውደም ይከሰሳል። የኤርትራ መንግሥት ግን ክሶቹን አይቀበላቸውም።
የትራንስፖርት አገልግሎት ከሠራዊቱ
በነዳጅ እጥረት እና በፀጥታ ችግር ምክንያት በክልሉ እና ከክልሉ ውጪ የትራንስፖርት አገልግሎቶች ተቋርጦ የቆየ ሲሆን፣ ከሁለት ቀናት በፊት ከሽረ ወደ አንዳንድ የዞኑ ከተሞች እንዲሁም ወደ አክሱም የተወሰነ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት መጀመሩ እየተነገረ ነው።
ነገር ግን ጦርነቱ ከቆሙ በኋላ በነበሩት ሁለት ወራት ውስጥ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ሰላማዊ ሰዎችን እና ንብረት በማጓጓዝ ሲሳተፉ ታይተዋል ሲሉ ቢሲሲ ያነጋገራቸው የሽረ እንዳሥላሴ ነዋሪዎች ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ጦር እና ከጎኑ የተሰለፉ የአማራ ኃይሎች የጭነት መኪናዎች እንዲሁም አውቶቡሶች ሰላማዊ ዜጎችን ከሽረ ወደ አድዋ፣ አክሱም እና ሸራሮ በማጓጓዝ ላይ ይሳተፉ እንደነበር የሚገልጹት ነዋሪዎች፣ አሁን ደግሞ የኤርትራ ሠራዊትም ተመሳሳይ አገለግሎት እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
የፌዴራል መንግሥቱ እና የኤርትራ ወታደሮች በጥቅምት 04/2015 ዓ. ም. ሽረን ከተቆጣጠሩ በኋላ አስከ ከጥቅምት መጨረሻ ጀምሮ እስከ ቅርብ ቀናት ድረስ በስፍራው እንደቆየ የሚናገረው ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ የእርዳታ ድርጅት ሠራተኛ የትራንስፖርት አገልግሎቱ መቆየቱን ይናገራል።
“መጀመሪያ ላይ የፌደራል ጦር መኪኖች ወደቀያቸው መመለስ ለሚፈልጉ ተፈናቃዮች ወደ ሸራሮ፣ አዲ ሃገራይ፣ አዲ ነብሪ ኢድ እና የታችኛው አዲያቦ ነፃ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ጀምሮ የማይካድ ነው። ነገር ግን በዚህ መሀል ግን ወደ ንግድ ተቀየረ።”
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የሽረ፣ አክሱም እና አድዋ ነዋሪዎች በትራንስፖርት፣ በምግብ ቤቶች እና በገበያ ስፍራዎች አሁንም ድረስ የኤርትራ ሠራዊት አባላትን እንደሚያዩ እና አብረው አገልግሎቶችን እንደሚጠቀሙ ነዋሪዎች ይናገራሉ።
በአካባቢዎቹ በመቆየታቸው ወታደሮቹ የኤርትራ ስለመሆናቸው እንደሚያውቁ እንዲሁም በተሽከርካሪዎቻቸው የሠሌዳ ቁጥር እና በሚለብሱት የወታደር ልብስ ከኢትዮጵያ ሠራዊት እና የፌደራል ፖሊስ በቀላሉ ለመለየት እንደሚቻል ይናገራሉ።
*ቢቢሲ በስልክ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ለደኅንነታቸውን ስለሚሰጉ ስማቸው እንዲገለጽ አልፈለጉም