ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኤርትራ ሠራዊት ከትግራይ ከተሞች እየወጣ መሆኑን ነዋሪዎች ተናገሩ
ከኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት ጎን ሆኖ የትግራይ ኃይሎችን ሲወጋ የነበረው የኤርትራ ሠራዊት ከቆየባቸው ተለያዩ ትግራይ አካባቢዎች እየወጣ መሆኑን ነዋሪዎች ተናግሩ።
ቢቢሲ በሽረ ከተማ የሚገኙ ነዋሪዎችን አናግሮ መረዳት እንደቻለው ለወራት በከተማዋ የቆዩት የኤርትራ ሠራዊት አባላት እየወጡ ናቸው።
ሮይተርስ የዜና ወኪልም ሦስት ነዋሪዎች ነግረውኛል ብሎ እንደዘገበው ከሆነ የኤርትራ ሠራዊት ከሽረ እንዳሥላሴ እና አክሱም ከተሞች ወጥተዋል።
የኤርትራ ወታደሮችን የጫኑ በርካታ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች ከአክሱም ከተማ አቅጣጫ በመምጣት ወደ ሽራሮ ሲያልፉ መመልከታቸውን የሽረ ከተማ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ነዋሪዎቹ የኤርትራ ወታደሮች እንቅስቃሴ መኖሩን ይመልከቱ እንጂ ወታደሮቹ ትግራይን ለቅቀው እየወጡ ስለመሆናቸው እርግጠኛ መሆን አይቻልም ብለዋል።
እንደ ነዋሪዎች ገለጻ ከሆነ በሽረ ከተማ ዙሪያ ያነበሩ የኤርትራ ጦር አባላት ከዚህ ቀደም ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሱ ስለሚመላለሱ ይህ የአሁኑ እንቅስቃሴም ሠራዊቱ የትግራይ ክልልን ለቆ የመውጣት ስለመሆኑ ማወቅ እንደማይቻል ተናግረዋል።
በሽረ እና በአክሱም ከተማ ያሉ የእርዳታ ድርጅት ሠራተኞችም በተመሳሳይ በበርካታ የጭነት ተሽከርካሪዎች የተሳፈሩ የኤርትራ ወታደሮች ዛሬ ሐሙስ ታኅሣሥ 21/2019 ዓ.ም. ወደ ሽራሮ ከተማ አቅጣጫ ሲጓዙ መመልከታቸውን ለሮይተርስ የዜና ወኪል ገልጸዋል።
አንድ የእርዳታ ድርጅት ሠራተኛ ጨምሮም ወታደሮቹ በእጃቸው እያውለበለቡ ሲሰናበቱ እንደነበር ገልጿል።
የፌደራሉ መንግሥት እና ህወሓት ከሁለት ወራት ገደማ በፊት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ግጭቱን በዘላቂን ለማቆም በደረሱት ስምምነት የውጭ ኃይሎች ከትግራይ እንዲወጡ መስማማታቸው ይታወሳል።
ሮይተርስ የኤርትራ ሠራዊት ከትግራይ እየወጣ ስለመሆኑ ለአገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር ጥያቄ ቢያቀርብም፤ ሚኒስትሩ የማነ ገ/መስቀል የሠራዊቱን እንቅስቃሴ በተመለከተ ማረጋገጫም ሆነ ማስተባበያ መስጠት እንደማይፈልጉ ተናግረዋል።
ከኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ ከህወሓት በኩልም የኤርትራ ሠራዊት እንቅስቃሴን በተመለከተ አስካሁን የተባለ ነገር የለም።
ለሁለት ዓመታት በተካሄደው የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት ተሳትፎ ያደረገው የኤርትራ ሠራዊት በካባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና የመሠረተ ልማቶች ላይ ውድመት በማድረስ ሲከሰስ ቆይቷል።
ጦሩ እስካሁን በኢትዮጵያው ጦርነት ስለመሳተፉ ምንም ያለው ነገር ባይኖርም ምዕራባውያን የኤርትራ ጦር ከትግራይ እንዲወጣ በአሥመራ እና በአዲስ አበባ ላይ ጫና ሲያሳድሩ ቆይተዋል።
አሜሪካም በጦሩ እና በጦሩ ከፍተኛ አመራሮች ላይ ማዕቀብ መጣሏ ይታወሳል።
የፌደራል መንግሥቱ እና ህወሓት ከስምምነት መድረሳቸውን ተከትሎ የኤርትራ ሠራዊት ከትግራይ የመውጣት ጉዳይ ለስምምነቱ እንቅፋት ይሆናል ተብሎ በአንዳንዶች ተሰግቶ ነበር።
ነዋሪዎች እንዳሉት አሁን እየታየ ያለው የኤርትራ ሠራዊት እንቅስቃሴ መጀመር ለሰላም ስምምነቱ ተፈጻሚነት ወሳኝ እርምጃ መሆኑ ይታመናል።
ነዋሪዎች ምን ተመለከቱ ?
በአክሱም፣ በሽረ እና ከኤርትራ ጋር በሚዋሰኑ አካባቢዎች የኤርትራ ሠራዊት አባላት እየወጡ መሆናቸውን የሚናገሩ ነዋሪዎች እንዳሉ ሁሉ፣ አሁንም በእነዚህ ስፍራዎች ወታደሮቹ እንዳሉ የሚገልጹም አሉ።
“ሐሙስ ዕለት የኤርትራ ሠራዊት እየወጣ እንደሆነ የነገሩን ሰዎች ነበሩ” የሚሉት የሽረ ነዋሪ በከተማ ውስጥ የሚታይ የተለየ እንቅስቃሴ እንደሌለ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ዛሬ ጠዋት (አርብ) የኤርትራ ታርጋ ያለው መኪና ባይኔ አይቻለሁ። አፍሪካ ሆቴል ላይ ሆኜ ወደታች ሲወርዱ አይቻቸዋለሁ። የሚቆዩ ይሁኑ የሚወጡ የማውቀው ነገር የለም። መኪኖቹ የተሸፈኑ ስለሆኑ ምን እንደጫኑ ለማወቅ ይከብዳል። ከላያቸው የተወሰኑ የተጫኑ ወታደሮች ግን ነበሩ” ሲሉ ወታደሮች የጫኑ ተሽከርካሪዎችን ማየታቸውን ገልጸዋል።
ቢቢሲ ያናገራቸው በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ሰዎች የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ ክልል እየወጡ መሆናቸውን እርግጠኛ ባይሆኑም በመኪኖች ላይ ሆነው ሲሄዱ ማየታቸውን ጠቅሰዋል።
“ተጭነው ሲወጡ አይተን ነበር። ነገር ግን አሁንም በከተማዋ የማያቸው የኤርትራ ሠራዊት አባላት አሉ። ትናንት (ሐሙስ) አጋጣሚ አክሱም ነበርኩ እዚያም የሚንቀሳቀሱ ወታደሮችን አይቻለሁ” ሲሉ ስማቸው እንዲጠቅስ ያልፈለጉ ሌላ የሽረ ነዋሪ ገልጸዋል።
ጨምረውም “ከፊት እና ከኋላ መከላከያ አጅቧቸው አይቻለው። ክላሸ ብቻ ይዘው ነበር። ሌላ የከባድ መሳሪያ እንቅስቃሴ አላየሁም። ወደ ሽረ እንዳስላሴ ከተመለስኩ በኋላ ደግሞ በከተማዋ የሚንቀሳቀሱ የኤትራ ሠራዊት አሉ። በብዛት ወደ ሸራሮ መውጫ አካባቢ ይታያሉ። ወደዚህ ወደ ሽረ የሚመጡም አሉ” ብለዋል።
የሰላም ስምምነት
ይህን ለሁለት ዓመታት የዘለቀ የርስ በርስ ጦርነት ለማስቆም የአፍሪካ ኅብረት በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል ሽምግልና ሲያካሂድ ቆይቶ የተሰካለት ባለው ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም. ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ላይ ነበር።
ሁለቱወገኖች ፕሪቶሪያ ላይ በደረሱት ስምምነት በዋናነት ዘላቂ የግጭት ማቆም ስምምነት የፈረሙ ሲሆን በዚህም ሰብዓዊ እርዳታያለገድብ እንዲቀርብ፣ የተቋረጡ መሠረታዊ አግልገሎቶች መልሰው እንዲጀመሩ እና የህወሓት ተዋጊዎች ትጥቅ እንዲፈቱ ወስነው ነበር።
በስምምነቱየፌደራሉ መንግሥት ሠራዊት በትግራይ ውስጥ የሚገኙ ተቋማትን በሚቆጣጠርበት ጊዜ የህወሓት ወታደሮች ትጥቅ በመፍታት ወደ ኅብረተሰቡ እንዲመለሱ የሚደረግ ሲሆን በተመሳሳይ ጊዜም የኤርትራን ሠራዊት ጨምሮ ከፌደራሉ ሠራዊት የሆኑ ኃይሎች ከክልሉ እንደሚወጡ ተገልጿል።
የህወሓትእና የፌደራል መንግሥቱ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ አመራሮች ከፕሪቶሪያ በማስከተል ለሁለት ጊዜ ኬንያ ናይሮቢ ውስጥ ተገናኝተው በስምምነቱ አተገባበር ላይ ተወያይተው ከስምምነት ደርሰዋል።
ከፐሪቶሪያውስምምነት በኋላ በሁለቱ ኃይሎች መካከል ሲካሄድ የነበረው ጦርነት የቆመ ሲሆን፣ የህወሓት አመራሮች ግን በክልሉ ውስጥ ያሉ የኤርትራ ወታደሮች በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት እያደረሱ መሆናቸውን በተደጋጋሚ ሲከሱ ቆይተዋል።
ባለፉትሳምንታት የሰብአዊ እርዳታ እየቀረበ፣ የተቋረጡ መሠረታዊ አገልግሎቶች ወደ ሥራ እየተመለሱ ሲሆን፣ የፌደራል ፖሊስ ከሐሙስ ጀምሮ ወደ መቀለ በመግባት የፌደራል መንግሥቱን ተቋማት መቆጣጠር ጀምሯል።
እየተጠበቀያለው የፌደራል መንግሥቱ የመከላከያ ሠራዊት ወደ መቀለ መግባት እና የህወሓት ተዋጊዎች ከባድ የጦር መሳሪያዎችን ማስረከብ መጀመር ነው።
አሁንእየተነገረ እንዳለው የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ አካባቢዎች መውጣታቸው እውን ከሆነ የሁለቱ ወገኖች ስምምነት ያለ እንቅፋት ተግባራዊ ሆኖ ትግራይ ወደ መደበኛው እንቅስቃሴ ሙሉ ለሙሉ ትመለሳለች።