ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ብሔረ ተኮር ጥቃት ወደ ተፈጸመባቸው የወለጋ ዞኖች የፌደራሉ ሠራዊት መሰማራቱ ተገለጸ
ባለፉት ቀናት ብሔር ተኮር ግጭት ወደ ተቀሰቀሰባቸው የወለጋ ዞኖች የአገር መከላከያ ሠራዊት መሰማራቱ ተገለጸ።
ባለፉት ቀናት በምሥራቅ ወለጋ እና ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞኖች በሚገኙ አካባቢዎች በተፈጸሙ ብሔር ተኮር ጥቃቶች በርካታ ሰዎች መገደላቸው እና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ መፈናቀላቸው ሲገለጽ ቆይቷል።
ነዋሪዎች በአካባቢያቸው ለተፈጠረው ግጭት እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እያለ የሚጠራው ቡድን እና የአማራ ታጣቂዎችን ተጠያቂ ይደረጋሉ።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንም በሰሞኑ ግጭት ዋነኛ ተሳታፊዎች መንግሥት ‘ሸኔ’ ብሎ የሚጠራው ቡድን እና የአማራ ታጣቂዎች መሆናቸው ለቢቢሲ አስታውቋል።
“የፌደራል ኃይል አባላት አንገር ጉተን ከተማ ከገቡ በኋላ በአካባቢው የጸጥታ መሻሻል አለ” ሲሉ ግጭት ካጋጠመባቸው አንዷ በሆነችው የምሥራቅ ወለጋ ዞን የጊዳ አያና ወረዳ አንድ ባለሥልጣን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የአገር መከላከያ ሠራዊት ወደ በምሥራቅ ወለጋ ዞን ባለፉት ጥቂት ቀናት የተሰማራ ሲሆን በሆሮ ጉዱሩ ዞን ደግሞ ከአንድ ሳምንት በፊት ተሰማርቷል።
በምዕራብ ኦሮሚያ እየተፈጠረ ስላለው ግድያ፣ መፈናቀል እና ንብረት መወደም ዝምታን የመረጠው የፌደራሉ መንግሥት ጦሩን ወደ ግጭት ቀጠናው ያሰማራው በርካቶች የዜጎች ደኅንነት እንዲረጋገጥ በስፋት እየጠየቁ ባሉበት ወቅት ነው።
ፖለቲከኞች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ማኅበራት መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት እንዲጠብቅ ሲጠይቁ ነበር።
የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በወለጋ ዞኖች በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው ሞት፣ መፈናቀል እና ሰቆቃ በእጅጉ ያሳስበኛል ያለ ሲሆን፣ መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት የማረጋገጥ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ትናንት ማክሰኞ ኅዳር 27/2015 ዓ.ም. ጥሪ አቅርቧል።
ፖለቲከኛው ጃዋር መሐመድ ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ላለው ቀውስ መፍትሄ ናቸው ያላቸውን ምክረ ሃሳቦች የለገሰ ሲሆን፤ መንግሥት ተኩስ በማቆም ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር ንግግር መጀመር አለበት ብሏል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ)፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እና ሌሎችም የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉዳዩን አስመልክተው ባወጧቸው መግለጫዎች፣ ወለጋ ውስጥ በዜጎች ላይ የሚፈጸመው ግድያ እንዳሳሰባቸውና መንግሥት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
የፌደራል መንግሥት ጦር በአካባቢዎች መሰማራቱ ይገለጽ እንጂ ግጭት ሸሽተው ከቀያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች የሰብዓዊ እርዳታ እንደሚያሻቸው እየተገለጸ ይገኛል።
ባለፉት ቀናት በወለጋ ዞኖች በተቀሰቀሱት ግጭቶች በሰው እና በንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት እስካሁን በውል ባይታወቅም፣ የምሥራቅ ወለጋ ዞን ነዋሪዎች ግን ከ60 ያላነሱ ሰዎች በአንድ ጀምበር መገደላቸውን ተናግረዋል።
ሰዎች በማንነታቸው ምክንያት የጥቃቶች ዒላማ መሆናቸውን የገለጸው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በጥቃቶቹ የደረሰውን ጉዳት ለማወቅ ምርመራ ላይ መሆኑን ለቢቢሲ አስታውቋል።