ወለጋ፡ መንግሥት አስካሁን ምንም ባላለበት ጥቃት በርካቶች መሞታቸው እና መፈናቀላቸው ተነገረ

ፌደራል እና የክልሉ መንግሥት ዝምታን በመረጡበት ጥቃት በምዕራብ ኦሮሚያ ምሥራቅ ወለጋ ዞን ብሔር ተኮር በሆኑ ጥቃቶች ሰላማዊ ሰዎች ሰለባ መሆናቸው መቀጠሉ እየተነገረ ነው።

በተለይ በምሥራቅ ወለጋ ዞን ውስጥ በሚገኙት ጊዳ አያና እና ኪራሙ ወረዳዎች ባለፉት ሦስት ቀናት ተባብሰው በቀጠሉት ጥቃቶች በርካቶች ሲገደሉ በመቶ ሺዎች መፈናቀላቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አሁን ቀጥሎ እየተካሄደ ስላለው ብሔር ተኮር ግጭት የክልሉም ይሁን የፌደራሉ መንግሥት አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ጥቃቶቹ እየተፈጸሙ ያሉት የት ነው?

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች በአካባቢያቸው እየተካሄደ ያለውን ሁኔታ ‘ጦርነት’ ብለው ይገልጹታል።

እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ቡድን በስፋት የሚንቀሳቀስባቸው የምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች መረጋጋት እርቋቸው ቢቆዩም፣ ባለፉት ጥቂት ቀናት ግድያ እና መፈናቀል የተበራከተበት ግን በምሥራቅ ወለጋ በሚገኙት ሁለት ወረዳዎች ውስጥ ነው።

ምሥራቅ ወለጋ ካሏት 18 ወረዳዎች መካከል ጊዳ አያና እና ኪራሙ ወረዳዎች ባለፉት ሦስት ቀናት ከፍተኛ ግጭቶችን አስተናግደዋል።

ለጥቃቶቹ ተጠያቂ የሚሆነው ማነው?

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች “ጦርነት የከፈቱብን የኦሮሚያ ልዩ ኃይል እና ‘ሸኔ’ ተቀናጅተው ነው” ይላሉ።

አካባቢውን እያስተዳደሩ ያሉት ባለሥልጣናት ደግሞ የኦሮሞን ተወላጅ እየለዩ እየገደሉ ያሉት ‘ጽንፈኛ’ የአማራ ብሔርተኞች ናቸው ይላሉ።

በጊዳ አያና ወረዳ የጉትን ከተማ ነዋሪ የሆነው የአማራ ተወላጅ ከቅዳሜ ኅዳር 24/2015 ዓ.ም. ንጋት ጀምሮ “ጦርነት” ቀጥሎ እየተካሄ መሆኑን ይናገራል።

“በርካታ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል አርብ ከተማዋን አቋርጦ አልፎ ጫካ ገብቶ አደረ። በነጋታው ፓትሮል መኪና ላይ በተገጠመ ዲሽቃ ቤቶችን እየመታ ሰዎችን መግደል ጀመረ” ይላል።

በጉትን በአሁኑ ወቅት ያለው አብዛኛው የአማራ ተወላጅ ነው የሚለው ይህ ነዋሪ፣ በዚህ አካባቢ ይኖር የነበረ የኦሮሞ ተወላጅ ቀዬውን ጥሎ ከተሰደደ ቀናቶች ተቆጥረዋል ይላል።

“ስጋት አለብን ብለው ከጉትን ከወጡ ሁለት ሳምንት አልፏቸዋል። ለምን ወጡ ብለን ማዘጋጃን ጠይቀን ነበር። ‘ፍርሃት ስላለባቸው፤ ለቤተሰቦቻቸው ሲሉ ነው’ አሉን” በማለት ይናገራል።

ሌላኛው የአካባቢው ነዋሪ ባለፉት ቀናት በነበረው ጥቃት የተገደሉ ሰዎችን ትክክለኛ ቁጥር በትክክል መናገር ባልችልም ሕይወታቸውን ያጡት ግን ከ60 አያንሱም ይላል።

“በገብርኤል ቤተክርስቲያና 18 ሰዎችን ቀብረናል። ሙስሊሞች ጋር ደግሞ 32 ቀብረናል። 16 የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ከወደቁበት ይነሱ ተብሎ በሸራ እየተጠቀለሉ ነው” ብሏል።

የተፈናቀሉት ደግሞ 200 ሺህ በላይ እንደሚሆን ይናገራል። ይህ አሃዝ ከዚህ ቀደም በነበሩ ግጭቶች ከሌሎች ቦታዎች ተፈናቅለው ጉትን ላይ ከትመው የነበሩ ሰዎችን እንደሚጨምር ነዋሪው ይገልጻል።

በአሁኑ ወቅት ጉትን ከተማ የአገር መከላከያ ገብቶ ቢገኝም፣ ሰዎች አከባቢው ጥለው እየወጡ እንደሆነ ይገልጻል።

ቃሉን ለቢቢሲ የሰጠ የጉትን ነዋሪ ጥቃት የተፈጸመው “የኦሮሚያ ልዩ ኃይል እና ሸኔ እየተናበቡ ነው” በማለት፣ መንግሥት ያስታጠቃቸው የአማራ ተወላጅ የሆኑ የሚሊሻ አባላት “ጥምር ጦሩን” ውጊያ ገጥመው እንደነበረ የሚገልጸው ነዋሪው፤ “ከሞቱ መካከል ጸጉራቸው ያደገ እና መታወቂያቸው የሸኔ መሆኑን የሚያሳይ ይገኙበታል” ይላል።

ኦሮሞን የሚገድሉት “ጽንፈኞች ናቸው”

በኪራሙ ወረዳ ለተፈጸመው ጥቃት የአማራ ጽንፈኛ ኃይሎች የኦሮሞ ተወላጆችን እየለዩ እየገደሉ እንደሆነ የገለጸው ደግሞ የጊዳ አያና ወረዳ ኮሚኒኬሽን ነው።

የጊዳ አያና ወረዳ ኮሚኒኬሽን ኅዳር 24 የአማራ ጽንፈኞች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጦርነት ከፍቶ የወረዳዋ ነዋሪ ሙሉ በሙሉ ተፈናቅሏል ብሏል።

እንደ የወረዳው ኮሚኒኬሽን ከሆነ በኪራሙ ወረዳ 19 ቀበሌዎች ውስጥ ይኖር የነበረ የኦሮሞ ተወላጅ ከዚህ ቀደም በአካባቢው ‘ታይቶ በማይታቅ’ ጥቃት ሙሉ በሙሉ ተፈናቅሏል።

ሌላ የኦሮሞ ተወላጅ የሆነ የኪራሙ ወረዳ ነዋሪ እንደሚሉት ባለፉት ቀናት ግጭት እንደ አዲስ ያገረሸው ባሳለፍነው ሐሙስ ኅዳር 22/2015 ዓ.ም የአማራ ኃይሎች ጥቃት ከከፈቱ በኋላ ነው ይላል።

ነዋሪው እንደሚሉት ሐሙስ ዕለት የአማራ ኃይሎች በኦሮሚያ ልዩ ኃይል ላይ ጥቃት ከከፈቱ በኋላ አርብ ኅዳር 23 ቀጥሎ በተካሄደው ግጭት በርካታ ንጹሃን የኦሮሞ ተወላጆች ሰለባ ሆነዋል ብለዋል።

ምን ተባለ?

ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰላማዊ ሰው ሕይወቱን እያጣ እና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ መፈናቀላቸው እየተገለጸ የክልሉም ሆነ የፌደራሉ መንግሥት በጉዳዩ ላይ እስካሁን አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ቢቢሲ ከሚመለከታቸው የክልል እና የፌደራል መንግሥት ባለሥልጣናት መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

በምዕራብ ኦሮሚያ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ብሔር ተኮር ጥቃቶች መድረሳቸውን ተከትሎ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ ፖለቲካ ፓርቲዎች እና ፖለቲከኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) የፌደራሉም ሆነ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ለጉዳዩ በቂ ትኩረት ባለመስጠቱ ግድያ ማስቆም እና የዜጎችን የሰብዓዊ መብት ማስከበር አልቻሉም ብሏል።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በበኩሉ ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ የፌደራል መንግሥት በኦሮሚያ ክልል በየወለጋ አካባቢዎች በአማራ ተወላጆች ላይ እየተፈፀመ ያለውን ጭፍጨፋ በአፋጣኝ ያስቁም ሲል ጠይቋል።

ፓርቲው በመግለጫው የኦሮሚያ ክልል መንግሥት በሰላማዊ የአማራ ተወላጆች ላይ እየተፈፀመ ያለውን ግድያ፣ እንግልት እና ንብረት ዝርፊያ ለማስቆም “ፍላጎት እና አቅም እንደሌለው በተደጋጋሚ ጊዜ ታይቷል” ከማለቱም በላይ፣ “የክልሉ መዋቅርም የጭፍጨፋው ተሳታፊና ሽፋን ሰጭ ሆኗል” ሲል ከሷል።

ፖለቲከኛው ጃዋር መሐመድ በበኩሉ ግጭቱ ከወለጋ ዞኖች ባሻገር ምሥራቅ እና ሰሜን ሸዋ እየተካሄደ መሆኑን እና በግጭቱ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት፣ የፋኖ ሚሊሻ እና የአማራ ልዩ ኃይል ከመሳተፉም በላይ “ግጭቱ ውስብስብ እና በማኅበረሰቦች መካከል አየሆነ በፍጥነት መጥቷል” ብሏል።

መንግሥት ሸኔ የሚለው እና በሽብር ቡድንነት የፈረጀው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በሚንቀሳቀስባቸው የምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች፣ ባለፉት ዓመታት ግጭቶች እና ጥቃቶች በሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ በተለያዩ ጊዜያት ሲፈጸም ቆይቷል።

በአሁኑ ወቅት በአካባቢው እየተስፋፋ ካለው ጥቃት ጋር በተያያዘ ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በተጨማሪ ከአጎራባች የአማራ ክልል አካባቢዎች ይገባሉ የተባሉ ታጣቂዎችም ተሳታፊ እንደሆኑ ይነገራል።