ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኢንዶኔዢያ ተራራ ላይ እሳተ ገሞራ ፈንድቶ አስራ አንድ ተራራ ወጪዎች ሞቱ
ኢንዶኔዢያ ውስጥ በሚገኘው ማራፒ ተራራ ላይ እሳተ ገሞራ መፈንዳቱን ተከትሎ አስራ አንድ ተራራ ወጪዎች ሞተው መገኘታቸውን የነፍስ አድን ሠራተኞች ገለጹ።
ሌሎች 12 ተራራ ወጪዎች የጠፉ ሲሆን፣ ሌላ አነስተኛ እሳተ ገሞራ ከፈነዳ በኋላም የፍለጋ ሥራው ተቋርጧል።
የአካባቢው የነፍስ አድን ቡድን ቃል አቀባይ ጆዲ ሃርያዋን፣ ሌላ እሳተ ገሞራ በፈነዳበት ወቅት ፍለጋ መቀጠሉ አደገኛ ነው ብለዋል።
እሑድ ዕለት የመጀመሪያው እሳተ ገሞራ ሲፈነዳ 75 ተራራ ወጪዎች በአካባቢው ነበሩ። አብዛኞቹ በሰላም ከአካባቢው መውጣት ችለዋል።
ተራራው ወደ ላይ ሦስት ኪሎ ሜትር የወጣ አመድ ተፍቶ ሰማዩን እና በአካባቢው ያሉ መንደሮችን በአመድ ሸፍኗል።
ማራፒ በኢንዶኔዢያ ንቁ እሳተ ገሞራዎች ከሚገኙበት 127 አካባቢዎች አንደኛው ሲሆን፣ በተራራ ወጪዎች ዘንድም ይታወቃል።
ከጥር እስከ የካቲት ባሉት ጊዜያት የእሳተ ገሞራ ብናኝ ስለሚወጣ አካባቢው ለጎብኚዎች እንደገና የተከፈተው ባለፈው ሰኔ ወር ላይ ነበር።
በማራፒ ተራራ ላይ አስከፊው እሳተ ገሞራ የተከሰተው እንደ አውሮፓውያኑ በ1979 ሲሆን በአደጋው 60 ሰዎች ሞተዋል።
ዛሬ ሰኞ በሥፍራው እየተካሄደ የነበረው ፍለጋ ከመታገዱ በፊት የሦስት ሰዎችን ሕይወት መታደግ ተችሏል።
የፓዳንግ የፍለጋ እና የነፍስ አድን ድርጅት ኃላፊ አብዱል ማሊክ እንዳሉት ግለሰቦቹ የተዳከሙ ሲሆን፣ ቃጠሎም ደርሶባቸዋል።
አርባ ዘጠኙ ተራራ ወጪዎች ደግሞ ቀደም ብሎ ከአካባቢው እንዲወጡ የተደረጉ ቢሆንም፣ በርካቶቹ ቃጠሎ አጋጥሟቸዋል።
ባለሥልጣናት የተራራ ወጪዎቹን ማንነት ወዲያውኑ አልገለጹም።
ፍንዳታውን የሚያሳዩ ቪዲዮዎች ሰማዩ፣ መኪናዎች እና መንገዶች በአመዱ ተሸፍነው አሳይተዋል።
የነፍስ አድን ሠራተኞችም የሞቱትን እና የተጎዱትን ተሸክመው ከተራራው ሲያወርዱ እና ወደ አምቡላንስ ሲወስዱ ታይተዋል።
የምዕራብ ሱማትራ የአደጋ መከላከል ኤጀንሲ ኃላፊ ሩዲ ሪናልዲ “የተወሰኑት ቃጠሎው ያጋጠማቸው ከፍተኛ ሙቀት በመሆኑ ነው” በማለት ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን ተናግረዋል።
ከተራራ ወጪዎቹ መካከል አንዷ የሆነችው ዛፊራህ ዛህሪም ከእሳተ ገሞራው አካባቢ ሆና በለቀቀችው ቪዲዮ የእናቷን እርዳታ ተማጽናለች።
ኢፌ በሚል ቅጽል ስም የምትታወቀው የ19 ዓመቷ ተማሪ፣ በቪዲዮው ላይ ፊቷ ተቃጥሎ፣ ፀጉሯ አመድ ለብሶ እና ድንጋጤ ወርሷት ታይታለች።
ከ18 የትምህርት ቤት ጓደኞቿ ጋር ሆና ወደ ተራራው ጉዞ ያደረገችው ወጣቷ፣ አሁን ላይ የሕክምና ክትትል እየተደረገላት ነው።
እናቷ ራኒ ራድላኒ ልጃቸው በብዙ ስቃይ ውስጥ እንዳለፈች ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
“ሥነ ልቦናዋ ተጎድቷል፤ ምክንያቱም የደረሰባትን ቃጠሎ አይታዋለች። በዚህ ላይ ሌሊቱን ሙሉ ህመሙን መቋቋም ነበረባት” ብለዋል።
ሌላኛዋ ተራራ ወጪም በነፍስ አድን ሠራተኞች ተደግፋ እያቃሰተች “ፈጣሪ ትልቅ ነው” ማለቷን የዜና ወኪሉ ዘግቧል።
ማራፒ ተራራ ከኢንዶኔዢያ 18 ሺህ ደሴቶች ውስጥ በትልቅነቱ ሦስተኛ ደረጃ ላይ በሚገኘው ሱማትራ ደሴት ውስጥ ይገኛል።
ተራራው ከባሕር ወለል በላይ 2 ሺህ 891 ሜትር ከፍታ አለው ።