የኢንዶኔዥያዋ ሴት አስክሬን በዘንዶ ሆድ ውስጥ ተገኘ

በኢንዶኔዥያ ጃምቢ ግዛት የአንዲት ሴት አስክሬን ገድሎ በዋጣት ዘንዶ ሆድ ውስጥ ተገኘ።

በ50ዎቹ ዕድሜዋ ላይ የምትገኘው ጃህራህ እሁድ ወደምትሰራበት የጎማ እርሻ ስፍራ አቅንታ ነበር።

በዚያው ቀን ምሽት ከስራ ባለመመለሷ ጠፍታለች ተብሎ የፈላጊ ቡድን እንዲሰማራ ተደርጓል።

ከአንድ ቀን በኋላም የመንደሩ ነዋሪዎች ሆዱ በከፍተኛ ሁኔታ የተነፋ ዘንዶም ተመለከቱ።

የተጠራጠሩት ነዋሪዎች ዘንዶውን ገድለው ሲከፍቱት የግለሰቧን አስከሬን ሳይቆራረጥ አግኝተውታል።

“ግለሰቧ በዘንዶው ሆድ ውስጥ ተገኝታለች” ሲሉ የቤታራ ጃምቢ ፖሊስ ኃላፊ ኤኬፒ ኤስ ሃሬፋ ለኃገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።

ግለሰቧ በዘንዶው ሆድ ውስጥ ብትገኝም አካሏ ምንም እንዳልተነካ ገልጸዋል።

የግለሰቧ ባለቤት ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ አንዳንድ ልብሶችዋን እና መሳሪያዎቿን በምትሰራበት ጎማ እርሻ ውስጥ ማግኘቱን ተከትሎ ፍለጋ እንዲሰማራ መደረጉን ፖሊስ አስታውቋል።

ቢያንስ አምስት ሜትር (16 ጫማ) ርዝማኔ ያለው ዘንዶ ሰኞ በሚያጠራጥር መልኩ መታየቱን ተከትሎም ነው የመንደሩ ነዋሪዎች ይዘው የገደሉት።

“የዘንዶውን ሆድ ከከፈቱት በኋላ በውስጡ ጃህራህን አገኟት” ሲሉ የፖሊስ ኃላፊው ለሲኤኤን ኢንዶኔዥያ ተናግረዋል።

ምንም እንኳን እንደዚህ አይነት ክስተቶች የተለመዱ ባይሆኑም በኢንዶኔዥያ አንድ ሰው በዘንዶ ተገድሎ ሲበላ ይህች ግለሰብ የመጀመሪያዋ አይደለችም።

በአውሮፓውያኑ 2017 እና 2018 በሃገሪቱ ውስጥ ሁለት ተመሳሳይ ሞቶች ተመዝግበዋል።

ዘንዶዎች ምግባቸውን ሳያኝኩ ሙሉ በሙሉ ይውጡታል። መንጋጋቸው በጣም ተጣጣፊ በሆኑ ጅማቶች የተገናኘ በመሆኑ ትልልቅ እንስሳትን መዋጥ ያስችላቸዋል።

አንድ ባለሙያ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ዘንዶዎች በተለምዶ አይጦችን እና ሌሎች እንስሳትን ይመገባሉ ፣ ነገር ግን አካላቸው እያደገ ሲመጣ አይጦችና ሌሎች አናሳ እንስሳት አይበቋቸውም።