ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አዲዳዕሮ፡ በትግራይ የተፈጸሙ የአየር ጥቃቶች ሰላማዊ ነዋሪዎችን መትተዋል?
በትግራይ ክልል አዲ ዳዕሮ በደረሰ የአየር ጥቃት ንጹሃን ነዋሪዎች እንደሞቱ ሪፖርቶች ወጥተዋል። ቢቢሲ ፋክት ቼክ በአዲ ዳዕሮ የደረሰውን ነገር ተመልክቶታል።
“ከልጆቼ ጋር ቴሌቪዥን እየተመለከትን በነበረበት ወቅት ከየት መጣ ሳይባል የአየር ጥቃት ደረሰብን፤ እዛውም ቤታችን በላያችን ላይ ፈራረሰብን” ይህንን የተናገሩት በትግራይ መስከረም አጋማሽ ላይ አዲ ዳዕሮ በምትባል ከተማ ላይ ከተፈጸመ የአየር ጥቃት የተረፉ ግለሰብ ናቸው።
በዚህ የአየር ጥቃት ስምንት ሰዎች መሞታቸው እንዲሁም በርካቶች ቆስለዋል ተብሏል።
አዲ ዳዕሮ በወቅቱ ክልልሉን በሚያስተዳድረው በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ስር ነበረች። ከተማዋ በትግራይ ኃይሎችና በኢትዮጵያ መከላከያ ኃይልና በአጋሩ የኤርትራ ሰራዊት መካከል በሚደረገው ውጊያ ለግንባሩ ቅርብ ነበረች።
ስለተፈጸመው የአየር ጥቃት እርስ በርስ የሚጋጩ መረጃዎች የወጡ ሲሆን ስፍራው ለጋዜጠኞች ተደራሽ አለመሆኑም አዳጋች አድርጎታል።
አንዳንድ ማስረጃዎች በቪዲዮዎች የወጡ ሲሆን ቢቢሲም እነዚህን ተንቀሳቃሽ ምስሎችና የአካባቢውን የሳተላይት ምስሎች በመጠቀም ምን እንደተፈጠረ ለማወቅ ሞክረናል።
ስለተፈጸመው ጥቃት ምን ተባለ?
መስከረም 17፣ 2015 ዓ.ም የኤርትራ አየር ኃይል በአዲ ዳዕሮ የመኖሪያ ስፍራ ላይ የአየር ጥቃት መፈጸሙን ህወሃት አስታወቀ።
የህወሃትባለስልጣናት እንዳሉት “በቦምብ ድብደባ በርካታ ሰላማዊ ዜጎች ተገድለዋል፤ በርካቶች ቆስለዋል እንዲሁም የመኖሪያ ቤቶች አመድ ሆነዋል”
የትግራይ ከፍተኛ አመራር የሆኑት ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረህይወት የኤርትራ ሚግ 29 ጄት ጥቃት አድርሷል ሲሉ ከሰዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት መስከረም 17፣ 2015 ዓ.ም በአዲዳዕሮ የአየር ኃይሉ ጥቃት ፈጽሟል ቢልም ከህወሃት ጋር ግንኙነት ያላቸውን ወታደራዊ ኢላማዎች መምታቱን ገልጿል።
የኢትዮጵያ መንግሥት አካል የሆነው ወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያ ገፅ በትዊተር አካውንቱ የትግራይ ኃይሎች በጥቃቱ ሰላማዊ ሰዎች ኢላማ ተደርገዋል ማለታቸው “ቀደም ብሎ የተቀነባበረ ውሸት” ነው ሲልም ከሷቸዋል።
"የኢትዮጵያ ብሄራዊ መከላከያ ሰራዊት እርምጃ ከመውሰዱ በፊት ወታደራዊ ቁሳቁሶች ከሰላማዊ ሰዎች መገለላቸውን ያረጋግጣሉ" ሲል በትዊተር ላይ ባወጣው መግለጫ አክሏል።
ስለ ጥቃቱ ምን ማስረጃ አለ?
ጥቃቱን የሚያሳይ ቪዲዮ የወጣ ሲሆን የተወሰነውም ክፍል በትግራይ የቴሌቪዥን ጣቢያ አባላት ኦንላይን ላይ ተጭኗል።
አንደኛው ቪዲዮ መስከረም 17፣ 2015 ዓ.ም በአካባቢው የአየር ጥቃት የተመታበትን የሚያሳይ ቪዲዮ ይታያል እና ይህም ከአዲ ዳዕሮ እንደሆነ ለቢቢሲ ተነግሮታል።
ነገር ግን መጀመሪያ የቀረጸውን ሰው ማግኘት ባለመቻላችን አካባቢውን ማረጋገጥ አልቻልንም።
በማግስቱ መስከረም 18፣ 2015 ዓ.ም በትግራይ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሰቪል የለበሱ ሰዎች በተደረማመሱ ህንጸዎችና ፍርስራሾች ውስጥ በህይወት የተረፉ ሰዎችን ሲፈልጉ የሚያሳይ ቪዲዮም ታይቷል።
በቪዲዮው ላይ እንደተመለከትነው ሴቶች እና ህፃናት የሚታዩ ሲሆን ከፍርስራሹም ውስጥ አንዲት ሴት ተቆፍራ ስትወጣም ያሳያል።
ማንነታቸውን ያልለየናቸው ሁለት ሲቪል የለበሱ ሰዎች ሽጉጥ ይዘውም ይታያሉ።
በአንዳንድ የኢትዮጵያ ክፍሎች ህዝብ በአደባባይ መሳሪያ ይዞ ማየት የተለመደ ሲሆን ይህ አካባቢ በወቅቱ በህወሓት ቁጥጥር ስር እንደነበረም እናውቃለን።
በቪዲዮው ላይ ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው ነዋሪዎች በኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል መገኘት አስመልክቶ የምትከበረውን የመስቀል ኃይማኖታዊ በዓል እያከበሩ እንደነበረና ጸጥታ የሰፈነበትም ዕለት እንደነበር ይገልጻሉ።
"ይህ ይፈጸማል ብለን አላሰብንም ነበር፣ እዚህ ምንም አይነት ወታደራዊ እንቅስቃሴ የለም፣ ይሄ የድሆች ሰፈር ነው" ስትል አንዲት ሴት ለትግራይ ቲቪ ተናግራለች።
በቪዲዮው ላይ ስፍራው አዲዳዕሮ መሆኑን ለማረጋገጥ የረዳንን ፍንጮች አግኘተናል።
አንደኛው ቪዲዮ በጉግል ካርታዎች ላይ እንደሚታየው ከከተማዋ በስተምዕራብ ካለው ኮረብታ ጋር አንድ የሆነ ኮረብታ ያሳያል።
የሚቀርጸው ግለሰብ ካሜራውን ሲያስጠጋው በስፍራው ያለ የመስጊድ ህንጻ ለሰኮንዶች ይታያል። በጉግል ካርታዎች ላይ ከሚታየው በአዲ ዳዕሮ ምስሎች ላይ ከሚታየው የመስጊዱ ህንፃ ጋር አንድ ነው።
መስጊዱ ጥቃት ከደረሰበት አካባቢ በስተሰሜን የሚገኝ ሲሆን በጉግል ኧርዝ ላይ በአረንጓዴው ጉልላት ሊለይ ይችላል።
ቢቢሲ ጥቃቱ ከደረሰበት በፊት እና በኋላ የአካባቢውን የሳተላይት ምስሎች መርምሯል።
በምስሉ ላይ በከተማዋ ባለ የመኖሪያ ሰፈር ባሉ ጎዳናዎች ህንጻዎች የሚታዩ ሲሆን መስከረም 21፣ 2015 ዓ.ም ጀምሮ ያሉ ምስሎች በአንድ አካባቢ ላይ ጉዳት መድረሱ በግልጽ ይታያል።
ከዚያ በፊት በተወሰዱ ፎቶዎች ላይ ይህ ጉዳት አይታይም። ነገር ግን ይህ ጉዳት ምን እንደሆነ እርግጠኛ ለመሆን ከመስከረም 21 በኋላ የተወሰደው ምስል ጥራት ግልጽ አይደለም።
የኢትዮጵያ መንግሥት ምላሹ ምንድን ነው?
በወቅቱ አዲ ዳዕሮ አካባቢ ወታደራዊ ኢላማ የነበረው ምን እንደሆነ የኢትዮጵያ ባለስልጣናትን ብንጠይቅም ምላሽ አላገኘንም።
ጥቅምት 17 የኢትዮጵያ መንግሥት ባወጣው መግለጫ ሠራዊቱ “የሰላማዊ ሰዎች ጉዳትን ለመቀነስ በከተሞች አካባቢ ውጊያ ላለማድረግ ጥረት ያደርጋል” ያለ ሲሆን “ህወሓት ሰላማዊ ሰዎችን እና ሲቪል ተቋማትን እንደ መሸሸጊያ የመጠቀም ልምድ አለው ሲል” ከሷል ።
አክሎም እስካሁን “በሰላማዊ ሰዎች እና በሰብዓዊ ድርጅት ሠራተኞች ላይ ደርሶ ሊሆን በሚችለው ጉዳት የተሰማውን ሐዘን ገልጾ ክስተቱ ያጋጠመበትን ሁኔታ ምርመራ አደርጋለሁ” ብሏል።
በትግራይ ውስጥ ተደጋጋሚ የአየር ጥቃቶች እየተፈጸሙ ሲሆን ነገር ግን በክልሉ ውስጥ የኮሚዩኒኬሽን አገልግሎቶች ተቋርጦ በመቀጠሉ ዝርዝሮችን ለመረዳት ፈታኝ ያደርገዋል።
ዓለም አቀፉ የነፍስ አድን ኮሚቴ ከአዲ ዳዕሮ በስተደቡብ በምትገኘው ሽረ ከተማ ላይጥቅምት 4፣ 2015 ዓ.ም በተፈጸመ የአየር ጥቃት የድርጅቱ ሰራተኛ መገደሉን ተናግሯል።
በሌሎች አካባቢዎችም ላይ በደረሱ ጥቃቶች ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው ሪፖርቶች የወጡ ሲሆን እነዚህን ለማረጋገጥ አስቸጋሪ ነው።
የአውሮፓ ህብረት “ነዋሪዎች በሚበዙባቸው ቦታዎች ላይ ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) በተደጋጋሚ መጠቀም ሰላማዊ ሰዎችን ለከፋ አደጋ እያጋለጠ ነው” ብሏል።