ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሰሜን ምዕራብ ትግራይ በአዲ ዳዕሮ የአየር ጥቃት መፈጸሙን መንግሥት አስታወቀ
በትግራይ ክልል አዲ ዳዕሮ በተባለ ስፍራ የአየር ጥቃት እንደደረሰ የትግራይ ኃይሎች ከገለጹ በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት ጥቃቱ መፈጸሙን አረጋገጠ።
የወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያ ገጽ የተባለው የመንግሥት የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ ላይ እንደተገለጸው የኢትዮጵያ አየር ኃይል “ሰሞኑን በተመረጡ ዒላማዎች ላይ እርምጃ ወስዷል” ሲል አረጋግጧል።
የትግራይ ኃይሎች ግን ማክሰኞ፣ መስከረም 17/2015 ዓ.ም. አዲ ዳዕሮ በምትባለው በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ውስጥ በምትገኘው ከተማ ላይ የአየር ጥቃቱን ኤርትራ ፈጽማለች ሲሉ ከሰው ነበር።
መንግሥት የአየር ጥቃቱ የተፈጸመበተን ትክክለኛ ቀን ባይገልጽም፣ “ከሰሞኑ በትግራይ ክልል ዓዲ ዳዕሮ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ወታደራዊ ቁሳቁሶች እና ተተኳሾች ያሉበትን ቦታ ዒላማ አድርጎ እርምጃ ወስዷል” ሲል አስፍሯል።
የትግራይ አመራሮች ከጥቂት ቀናት በፊት ጥቃቱ መፈጸሙን በመግለጽ ኢላማ የተደረገው ሰላማዊ ሰዎች የሚገኙበት ስፍራ ነው ሲሉ ክስ አሰምተዋል።
መንግሥት እንደሚለው ሠራዊቱ በሚወስደው እርምጃ “በሲቪሎች ላይ ጉዳት ሳያደርስ በከፍተኛ ጥንቃቄ የወታደራዊ ዒላማዎችን ነጥሎ እየመታ ይገኛል” ብሏል።
ማክሰኞ ዕለት በኤርትራ ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው አዲ ዳዕሮ ከተማ ላይ በተፈጸመው የአየር ጥቃት ቢያንስ ስድስት ሰዎች መሞታቸውን አንድ የረድዔት ሠራተኛ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ከጥቃቱ በኋላ የክልሉ ቴሌቪዥን ጣቢያ በጥቃቱ የተጎዱ ናቸው የተባሉ ሰዎች እና የፈራረሱ ቤቶችን አሳይቷል።
የመረጃ ማጣሪያ ገጹ እንዳለው ህወሓት “ወታደራዊ አቅሙን እና አመራሮቹን በዕምነት ቦታዎች፣ በጤና ተቋማት፣ በትምህርት ቤቶች እና በሌሎች ማኅበራዊ አግልግሎት መስጫ ቦታዎች እና ሲቪሎች በሚኖሩባቸው ቦታዎች እየደበቀ ነው” ሲል ከሷል።
ጋብ ብሎ የነበረው ጦርነት መልሶ ከተቀሰቀሰ በኋላ የፌደራል መንግሥቱ፣ የህወሓት “ወታደራዊ አቅሞችን በተመረጠ ሁኔታና በከፍተኛ ጥንቃቄ ዒላማ በማድረግ” ጥቃት እየፈጸመ መሆኑን ገልጿል።
ነሐሴ ወር ላይ ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ የኢትዮጵያ ሠራዊት በሰው አልባ አውሮፕላኖች በዋና ከተማዋ መቀለ እና በሌሎች ስፍራዎች ላይ የአየር ጥቃት መፈጸሙ ተዘግቧል።
በጥቃቱ የተጎዱ ነዋሪዎች በአምቡላንስ ወደ ሆስፒታል ሲወሰዱ ማየታቸውንም የእርዳታ ሠራተኛው ለቢቢሲ አክለው ተናግረዋል።
የትግራይ ባለሥልጣናት የአየር ጥቃቱ ማክሰኞ ዕለት “በተደጋጋሚ” መፈፀሙንና በዚህም የመኖሪያ ቤቶች ወድመዋል ብለዋል።
የአየር ጥቃቱ የተፈጸመባት አዲ ዳዕሮ በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ውስጥ ለኤርትራ አዋሳኝ በሆነ ስፍራ የምትገን ናት።
ድጋሚ ጦርነቱ ካጋረሸ በኋላ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በምትዋሰንባቸው የድንበር አካባቢዎች ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች እንደታዩ ተነግሯል።
ቢቢሲ ማክሳር ከተባለ ተቋም ያገኛቸው የሳተላይት ምስሎችም በኢትዮጵያና ኤርትራ ድንበር አካባቢ ሽራሮ ከተማ ወታደሮችና የጦር መሳሪያ መከማቸታቸውን የሚያሳዩ ምስሎች አግኝቷል።
የመጀመሪያዎቹ የሳተላይት ምስሎች የተነሱት መስከረም 16/2015 ዓ.ም. በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ውስጥ በምትገኘው ሽራሮ ከተማ ነው። ከተማዋ ቀደም ሲል በትግራይ ኃይሎች እጅ ነበረች።
ባለፉት ሳምንታት ከሳተላይት የተነሱት ምስሎች ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር በሚያዋስናት ድንበር ላይ የጦር ሠራዊት ክምችት እና መሳሪያዎች የተጠመዱባቸውን ቦታዎች አሳይተዋል።
ለሁለት ዓመት ሊሞላው የተቃረበው ጦርነት ለአምስት ወራት ጋብ ብሎ ከቆየ በኋላ ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ መልሶ ማገርሸቱ ይታወቃል።
በባለፉት ሳምንታት በተለያዩ አካባቢዎች ከባድ ውጊያዎች እንደተካሄዱ ቢነገርም ዝርዝር መረጃ ለማግኘት አዳጋች ሆኗል።