ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በፌደራል ፖሊስ በተተኮሰባቸው ጥይት የተገደሉት የሶማሌ ክልል ምክር ቤት አባል ስርዓተ ቀብር ተፈጸመ
በትናንትናው ዕለት ጥቅምት 15፣ 2015 ዓ.ም በፌደራል ፖሊስ አባል በተተኮሰ ጥይት ተመተው ሕይወታቸው ያለፈው የሶማሌ ምክር ቤት አባል በዛሬው ዕለት ጥቅምት 16፣ 2015 ዓ.ም ስርዓተ ቀብራቸው ተፈጸመ።
በዛሬው ዕለት ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ የተቀበሩት የምክር ቤት አባሏ ጁዋሪያ መሐመድ ኢብራሂም የተገደሉት ጅግጅጋ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ነበር።
ከፍተኛ የክልሉ ባለሥልጣኖች እና የአገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰውም በሥርዓተ ቀብሩ ላይ ተገኝቷል።
የቢቢሲ ሶማሌ ዘጋቢ የምክር ቤት አባሏን ግድያ የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ዛሬ ከሰዓት መካሄዱን ገልጿል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች አስክሬኗ ያረፈበት ቤቷ አካባቢ ለተቃውሞ የወጡ ሲሆን ለግድያዋ ተጠያቂ የሆነው ሰው አፋጣኝ እርምጃ እንዲወሰድበት ተቃዋሚዎቹ ጠይቀዋል።
አንዳንድ ተቃዋሚዎች ድንጋይ በመርወር ተቃውሟቸውን የገለጹ ሲሆን ከፓሊስም ጋር ግብግብ ውስጥ የገቡም አልታጡም።
ፖሊስ አስለቃሽ ጭስ ተኩሶ ተቃዋሚዎቹን የበተነ ሲሆን የተጎዳ ሰው እንደሌለ የቢቢሲ ሶማሌ ዘጋቢ ያስረዳል።
የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ሙስጠፌ ኡመር በምክር ቤት አባሏ ሞት የተሰማቸውን ሐዘን ለቤተሰቦቿና ለክልሉ ባጠቃላይ ከገለጹ በኋላ አስተዳደራቸው “ገዳዩ እስከ ሞት ቅጣት ድረስ እንዲቀጣ እንደሚያደርግ ገልጸው ሕዝብ እንዲረጋጋ” ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ጠይቀዋል።
በአሁኑ ወቅት በጅግጅጋ ከተማ ጸጥታ ቢሰፍንም ውጥረት እንደነገሰና ነዋሪዎች በግድያው እጅግ መቆጣታቸውም ተገልጿል ።
በዛሬው ዕለት በነበረው ግርግር የተወሰኑ ወጣት አክቲቭስቶች ታስረው እንደነበር የገለጸው የቢቢሲ ሶማሌ ዘጋቢ ከነዚህም መካከል የቀድሞ ወጣቶች ስፖርት ቢሮ ምክትል የነበሩት አቶ ኢብራሂም አብዱልቃድር ይገኙበታል።
በተጨማሪም ዑሳም ሱሉፕ የተባሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልም ለተወሰነ ሰአት ታስረው መለቀቃቸውን የቢቢሲ ሶማሌ ዘጋቢያችን ገልጿል።
የፌደራል ፖሊስ አባሉ ከከፈተው የተኩስ እሩምታ በኋላ በሌሎች የፌደራል ፖሊስ አባላት፣ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል እና በአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት በቁጥጥር ሥር የዋለ ሲሆን በዛሬው ዕለትም ፍርድ ቤት ቀርቧል።
በዛሬው ችሎትም የፌደራል ፖሊስ አባሉ ጁዋርያ ኢብራሂም ላይ እንደተኮሰባቸው ማመኑም ዘጋቢያችን ገልጿል።
የቢቢሲ ሶማሌ ዘጋቢ በጅግጅጋ አውሮፕላን ማረፊያ እህታቸውን ሊቀበሉ ከመጡት ጁዋሪያ ጋር እህታቸውን ፎቶ ሲያነሱ "እኔንም ፎቶ ውስጥ አስገብተሽኛል" በሚል ውዝግብ ተነስቶ እንደነበር መስማቱን ገልጿል።
ፖሊሱ ከአውሮፕላን ማረፊያው አስተዳዳሪ ጋር ተጣልቶ እንደነበርና በቁጣም ተሞልቶም እንደነበር ዘጋቢያችን አስረድቷል።
የተነሳውንም ውዝግብ ተከትሎ ተኩስ መክፈቱን የገለጸው የቢቢሲ ሶማሌ ዘጋቢ ከጁዋሪያ በተጫማሪ እህታቸውን ሊቀበሉ የመጡ ሌላ የምክር ቤት አባልም እንደተጎዱ ገልጿል።
ከዚህም በተጨማሪ የ ጁዋሪያ እህት እንዲሁ ጉዳት እንደደረሰባትም ዘጋቢያችን ገልጿል።