አሜሪካ ታሪፍን ሙሉ በሙሉ እንድትሰርዝ ቻይና አስጠነቀቀች

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአገራት ላይ እየጣሉት ያለው ተጨማሪ ታሪፍ አገራትን እያነጋገረ ነው። ለፕሬዝዳንቱ የታሪፍ ጭማሪ አጸፋ ከሰጡት አገራት መካከል ቻይና አንዷ ነች።

የቻይና ባለስልጣናት ሰሞኑን ዶናልድ ትራምፕ በአገራቸው ላይ የጣሉትን ተጨማሪ ታሪፍ ተከትሎ አሜሪካ ይህንን ውሳኔዋን ሙሉ በሙሉ እንድትሰርዝ አስጠንቅቀዋል።

ዶናልድ ትራምፕ በአገራት ላይ ሊጥሉት ያቀዱትን ታሪፍ ለ90 ቀናት እንዲዘገይ በዚህ ሳምንት አሳውቀዋል። በአንጻሩ በቻይና ምርቶች ላይ የሚጥሉትን ታሪፍ ደግሞ ወደ 145% ከፍ አድርገዋል።

"አሜሪካ ስህተቷን ለማረም ትልቅ ርምጃ እንድትወስድ ለማስጠንቀቅ እንወዳለን፤ የተሳሳተ አካሄድ የሆነውን የአጸፋ ታሪፍ ጭማሪ በመሰረዝ ትክክለኛውን የጋራ ተጠቃሚነት መንገድ መመለስ ይገባል" ብሏላ የቻይና የንግድ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ።

ባለፈው አርብ ዶናልድ ትራምፕ ቻይና የሚመረቱ የተወሰኑ የኤሌክትሮኒክስ ምርቶችን ከታሪፍ ነጻ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን አሳውቀዋል።

ነገር ግን የአሜሪካው የንግድ ሚኒስትር ሐዋርድ ሉትኒክ ባለፈው እሁድ እንዳሉት እንደዚህ ዓይነቶቹ ውሳኔዎች ለአጭር ጊዜ ብቻ የሚቆዩ ናቸው።

በእነዚህ ምርቶች ላይ በተለየ ሁኔታ የታሪፍ ጭማሪ የሚደረግ ሲሆን፣ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ጭማሪው ይፋ ይደረጋል ብለዋል።

"እነዚህ ምርቶች በአሜሪካ እንዲሠሩ እንፈልጋለን" ሲሉ ሚኒስትሩ ተደምጠዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ደግሞ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ በጻፉት መረጃ በእነዚህ ምርቶች ላይ የሚደረገው የታሪፍ ጭማሪ ቀርቷል መባሉ "ሐሰት" ነው ብለዋል። በአንጻሩ የተለየ የታሪፍ ስርዓት እንደሚበጅላቸው ተናግረዋል።

ትራምፕ አክለውም "ሁሉንም የኤሌክትሮኒክ ምርቶች እና ሰማይኮንዳክተር የአቅርቦት ሰንሰለትን በቀጣይ በሚደረገው የብሔራዊ የጸጥታ ታሪፍ ጥናት ላይ እንመለከታቸዋለን" ብለዋል።

ይህ ንግግራቸውም እንደ ስልክ፣ ኮምፒውተር እና ሌሎች የቴክኖሎጅ ምርት አቅራቢዎች ላይ ስጋትን ፈጥሯል።

የቻይናው ንግድ ሚኒስቴር በኤሌክትሮኒክስ ምርቶች ላይ የተጣለው የታሪፍ ጭማሪ በአሜሪካ የተደረገ "ውስን እርምጃ ነው" ያሉት ሲሆን፣ እርምጃው የሚኖረውን ተጽዕኖም ቤጂንግ እየገመገመች መሆኑን ገልጿል።

ነገር ግን የትራምፕ አስተዳደር በእነዚህ ምርቶች ላይም ቢሆን በቀጣይ ታሪፍ ለመጨመር ማቀዱ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የንግድ ጦርነት የበለጠ ያጋግለዋል ተብሎ ይታሰባል።

በሚያዚያ ወር መጀመሪያ ዶናልድ ትራምፕ ከቻይና በሚገቡ ምርቶች ላይ የ54% የታሪፍ ጭማሪ አድርገው ነበር። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ይህ የታሪፍ ጭማሪ ወደ 145% አድጓል።

ቻይናም የአሜሪካን እርምጃ በመከተል በአሜሪካ ምርቶች ላይ የ34 በመቶ ታሪፍ ጭማሪ አድርጋ ነበር። አሜሪካ ጭማሪ ስታደርግ ቻይናም በአሜሪካ ላይ የምትጥለውን የታሪፍ ጭማሪ ወደ 84% ያሳደገች ሲሆን አሁን ላይ 125% አድርሳዋለች።

በቅርቡ የተደረገውን ጭማሪ ተከትሎ የተጀመረውን የንግድ ጦርነት አሜሪካ የምትቀጥልበት ከሆነ ቻይና እስከመጨረሻው ለመፋለም መዘጋጀቷንም አስታውቃለች።

የታሪፍ ጭማሪ በማይደረግባቸው ምርቶች ላይ ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮ ተጨማሪ ማብራሪያዎችን እንደሚሰጡ ዶናልድ ትራምፕ ተናግረዋል።

ዋይት ሐውስ አሜሪካ የታሪፍ ጭማሪ የምታደርገው ከአገራት ጋር በመደራደር የተሻለ የንግድ ስርዓት ለመዘርጋት በማሰብ መሆኑን ገልጿል።

ዶናልድ ትራምፕ በዓለም ላይ ያለውን 'የተዛባ' ያሉትን የንግድ ስርዓት ማስተካከል፣ ተጨማሪ የሥራ ዕድል መፍጠር እና ፋብሪካዎችን ወደ አሜሪካ መመለስ ላይ ያተኮሩ ሥራዎችን እንደሚተገብሩ አስተውቀዋል።

ነገር ግን ይህ ጣልቃ ገብነት በስቶክ ማርኬት ላይ ከፍተኛ ግሽበት ያስከተለ ሲሆን፣ የዓለም ንግድን በመቀነስ በሥራ እና በግለሰቦች ኢኮኖሚ ላይ መቀዛቀዝን ያስከትላል የሚል ስጋትንም ፈጥሯል።