እናት እና አባቱን የገደለው ታዳጊ ትራምፕን የመግደል ዕቅድ እንደነበረው ኤፍቢአይ አስታወቀ

በዊስኮንሲን ግዛት እናት እና አባቱን የገደለው የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ የአሜሪካው ፕሬዝደንት ትራምፕን የመግደል ዕቅድ እንደነበረው ኤፍቢአይ አስታወቀ።

የ17 ዓመቱ ኒኪታ ካሳፕ የ35 ዓመቷ እናቱ ታቲያና ካሳፕ እና የ51 ዓመት የእንጀራ አባቱ ዶናልድ ሜየርን በመግደል ክስ ቀርቦበታል።

እናት እና አባት በአውሮፓውያኑ የካቲት 28 ነው በመኖሪያ ቤታቸው ተገድለው የተገኙት።

አዲስ የወጣ ዘገባ እንደሚጠቁመው ታዳጊው ይጠቀምበት የነበረው ስልክ የናዚ አቀንቃኝ ከሆኑ ቡድኖች ጋር ግንኙነት ያለው መረጃ ይዟል።

ቡድኑ ኦርደር ኦፍ ናይን ኤንጅልስ የሚባል ሲሆን ለኤዶልፍ ሂትለር አድናቆት በመቸር ይታወቃል።

መርማሪዎች፤ ታዳጊው ፀረ-ሴማዊ የሆነ ፅሑፍ እና መንግሥትን ለመጣል በሚል ትራምፕን ለመግደል ያሴረበት ዕቅድ ማግኘታቸውን የፍርድ ቤት መዛግብት አሳይተዋል።

ተጠርጣሪው ሆነ ብሎ ነብስ በማጥፋት ወንጀል በአንደኛ ደረጃ ግድያ የተከሰሰ ሲሆን ሬሳ መደበቅ እና ማንነት መስረቅን ጨምሮ ሌሎች ሰባት ክሶችም ቀርበውበታል።

ታዳጊው ለሁለት ሳምንታት ትምህርት ቤት አለመምጣቱን ተከትሎ ፖሊስ ወደ ቤተሰቦቹ መኖሪያ ቤት ባቀናበት ወቅት ነው እናት እና አባት ተገድለው ያገኛቸው።

የእንጀራ አባቱ ሜየር ጭንቅላታቸው ላይ በጥይት ተመትተው እናቱ ደግሞ በርካታ ጊዜ በጥይት ተደብድበው የካቲት 11 መገደላቸውን የምርመራ ውጤቱ ያሳያል።

የሁለቱ ግለሰቦች ሬሳ በተገኘበት ቀን ታዳጊው ካንሳስ ግዛት የእንጀራ አባቱን ቮክስቫገን መኪና እየነዳ ሳለ በፖሊስ እንዲቆም መደረጉ ተሰምቷል።

መኪናው ውስጥ የእንጀራ አባቱ ሽጉጥ፣ የጥንዶቹ ንብረት የሆኑ አራት ክሬዲት ካርዶች፣ በርካታ ጌጣጌጦች እንዲሁም መፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ 14 ሺህ ዶላር መገኘቱን ምርመራው ጠቁሟል።

መርማሪዎች እንደሚሉት ታዳጊው የነጭ የበላይነትን የሚያንፀባርቁ ፅሑፎችን የያዘ ሲሆን ፖለቲካዊ አብዮት ለመቀስቀስ ትራምፕን የመግደል ዕቅድ እንዳለውም ገልጿል።

ተጠርጣሪው እናቱን እና የእንጀራ አባቱን የገደለው "ያሰበውን ለማሳካት የገንዘብ አቅም እንዲኖረው ሳይሆን አይቀርም" ይላል የመርማሪዎች ሪፖርት።

የፍርድ ቤት መዛግብት እንደሚያሳዩት ታዳጊው እናት እና አባቱን ለመግደል ሩሲያ ከሚገኙ ሰዎች ጋር ሲያሴር ነበር።

ባለሥልጣናት እንዳሉት ተጠርጣሪው ጥቃት ለማድረስ ለድሮን እና ለፈንጂ መግዣ የከፈለ ሲሆን ከጥቃቱ በኋላ ወደ ዩክሬን ለመጥፋት ዕቅድ ነበረው።

"ከሌሎች ሰዎች ጋር እንዴት ፕሬዝደንቱን እንደሚገድል እና መንግሥት እንደሚጥል ሲወያይ ነበር" ሲሉ መርማሪዎች ፅፈዋል።

ተጠርጣሪው በአውሮፓውያኑ ሚያዚያ 9 የፍርድ ቤት ቀጠሮ ያለው ሲሆን እስካሁን ወንጀሉን መፈፀሙን አላመነም።

ታዳጊው የአንድ ሚሊዮን ዶላር ዋስ ተጠርቶበታል።