ማራቶንን ከሁለት ሰዓት በታች መሮጥ ይቻላል? ኢትዮጵያውያን ወይስ ኬንያውያን ታሪክ ይሠራሉ?

ኬንያዊው የረዥም ርቀት ሯጭ ኬልቪን ኪፕቱም በቅርቡ በመኪና አደጋ ሕይወቱ አልፏል። አትሌቱ በዘርፉ ለማሳካት ከባድ ነው የተባለውን ዒላማ ዕውን ለማድረግ ዕቅድ ነበረው፤ ከሁለት ሰዓት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ማራቶንን በማጠናቀቅ የመጀመሪያው ሰው መሆን።

ከኪፕቱም ህልፈት በኋላ ግን ይህንን ማን ሊያሳካው ይችላል የሚሉ ብዙ መላምቶች እየተሰጡ ነው። የምሥራቅ አፍሪካ ሯጭ ስለመሆኑ የሚጠራጠሩ ግን ጥቂቶች ናቸው።

በዓለም ዙሪያ በየዓመቱ በርካታ ታዋቂ ማራቶን ውድድሮች ይካሄዳሉ። የቶኪዮ፣ የለንደን፣ የኒው ዮርክ እና የበርሊን ማራቶኖች ተጠቃሽ ናቸው።

የሆላንዷ ሮተርዳም ከተማ እንደ ሌሎቹ በማራቶን ብዙም ባትታወቅም ኬልቪን ኪፕቱም በታኅሣሥ ወር በከተማዋ ማራቶንን ከሁለት ሰዓት በታች ለመሮጥ እንደሚሞክር አውጆ ነበር።

የ24 ዓመቱ ሯጭ ሞት ባይቀድመው ለአስርት ዓመታት የማይቻል ነው ተብሎ የሚታሰበውን በኦፊሴላዊ ውድድር ማራቶንን ከሁለት ሰዓት በታች መግባትን በመጨረሻ ለማሳካት ተዘጋጅቶ ነበር።

ኪፕቱም እአአ ጥቅምት 2023 ሦስተኛውን ማራቶኑን (42 ኪሜ) ቺካጎ ላይ የሮጠው ሁለት ሰዓት ከ35 ሰከንድ ነው። ይህ አዲስ የዓለም ክብረወሰን ብቻ አልነበረም።

ከአንድ ዓመት በፊት የአገሩ ልጅ እና ድርብ የኦሊምፒክ ሻምፒዮን የሆነው ኢሊዩድ ኪፕቾጌ (2፡01፡09) ካስመዘገበው ሪከርድ በ34 ሰከንድ የፈጠነ ነበር።

“ኬልቪን እያደረገ የነበረውን ነገር ከተመለከትነው ከሁለት ሰዓት በታች የሚሮጠው እሱ ነው ብሎ ከማሰብ በቀር ምንም ማድረግ አልቻልም” ሲል ኬንያዊው የሩጫ ተንታኝ እና የቀድሞ ሯጭ ማርቲን ኬይኖ ተናግሯል።

“የኬልቪን ሞት በእርግጠኝነት ያንን ወሳኝ ምዕራፍ ከማሳካት ወደ ኋላ እንድንመለስ አድርጎናል። ‘ከሁለት ሰዓት በታች’ መሮጥ እንደሚቻል ግን ለእያንዳንዱ ሯጭ አሳይቷል።”

እንደ ብዙዎቹ ሁሉ ኬይኖ ብዙዎቹ ለዚህ ስኬት ዕጩ የሚሆኑት ኬንያውያን እና ኢትዮጵያውያን ሯጮች እንደሆኑ ያምናል።

በሌሎች ስፖርቶች እንዳየነው ሁሉ የረዥም ርቀት ሩጫም በሥልጠና፣ በሥነ-ምግብ እና ከፍተኛ ቴክኖሎጂ ያፈራቸው ቀላል ጫማዎችን በመሳሰሉ መሳሪያዎች ላይ መሻሻሎች መታየታቸው ፈጣን ውጤት እንዲመዘገብ ሆኗል።

ለአብነት ያህል የወንዶች የማራቶን የዓለም ክብረ ወሰን ባለፉት 20 ዓመታት ከአራት ደቂቃ በላይ ቀንሷል። በሴቶች ውድድርም ተመሳሳይ መሻሻል ታይቷል።

እአአ በ2015 በአሜሪካ የስፖርት ሳይንቲስቶች የተደረገ ጥናት እንደሚያሳው እአአ በ2003 ብሪታኒያዊቷ ፓውላ ራድክሊፍ ማራቶንን በሁለት ሰዓት ከ15 ደቂቃ ከ25 ሰከንድ በሆነ ጊዜ በመግባት በሴቶች መስክ በተመሳሳይ “የማይቻል” የተባለው ደረጃ ላይ ተደርሷል።

የስምጥ ሸለቆ ሯጮች

በሚገርም መልኩ የአንድ አካባቢ አትሌቶች በረዥም ርቀት ሩጫ የበላይ ሆነዋል። ባለፉት አራት የኦሊምፒክ ውድድሮች ኢትዮጵያውያን እና ኬንያውያን አትሌቶች በ800 ሜትር እና ከዚያ በላይ በሆነ ውድድር በርካታውን የወርቅ ሜዳሊያ አግኝተዋል።

በወንዶች ማራቶን ከምን ጊዜውም 20 ፈጣን ሰዓቶች ውስጥ 18ቱ በሁለቱ አገራት ሯጮች የተመዘገቡ ናቸው። በሴቶች ማራቶን ከ20 ፈጣን ሯጮች 17ቱ ከሁለቱ አገራት የተውጣጡ ናቸው። ኢትዮጵያዊቷ ትዕግስት አሰፋ (2፡11፡53) የሴቶቹን ክብረ ወሰን ሰብራለች።

የዚህ የበላይነት ምክንያት ብዙ አከራካሪ ቢሆኑም ለአሸናፊዎቹ ወሳኝ የሆነው ነገር ከስምጥ ሸለቆ የምሥራቅ አፍሪካ ተራራማ አካባቢ ጋር የተያያዘ ይመስላል። ታዋቂዎቹ የኬንያ እና የኢትዮጵያ ሯጮች የወጡት ከዚያ ነው።

ሳይንሳዊ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከባሕር ጠለል በላይ በሆኑ ከተሞች እና መንደሮች ውስጥ የሚኖሩ ሯጮች [በተለይም እዚያው የተወለዱት] የኦክስጂን መጠን ዝቅተኛ በሆነባቸው ከፍታማ ቦታዎች ላይ አዘውትረው በመሠልጠን ጠንካራ ልብ እና ሳንባዎችን ያዳብራሉ።

ይህ ግን ለስኬቱ ዋስትና አይሆንም። እንደ ኔፓል እና ቦሊቪያ ያሉ በከፍታማ ቦታዎች የሚኖሩ ሰዎች ተመሳሳይ ተጽዕኖ ሲፈጥሩ አልታየም። ኢትዮጵያውያን እና ኬንያውያንን የሚለያቸው የሚመስለው ሩጫ በዕለት ተዕለት ኑሯቸው ውስጥ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የቆየ መሆኑ ነው።

የበርካታ የዓለም ሻምፒዮን እና የኦሊምፒክ አሸናፊው እንዲሁም የሁለት ጊዜ የማራቶን የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤቱ ኃይሌ ገብረሥላሴ ትምህርት ቤቱ ከቤታቸው 10 ኪሎ ሜትር ይርቃል። ትምህርት ቤት ለመመላለስ ትራንስፖርት አይገኝም ነበር።

መሮጥ አስፈላጊ ሆነና ኃይሌ የሚታወቅበትን አሯሯጥን አዳበረ። በግራ እጁ ደብተር እና መጽሐፍቱን ደረቱ ላይ አስደግፎ የሚሮጥበት መንገድ እስከ ዓለም ውድድር ድረስ ተከትሎታል።

አሁን ራሱን ከውድድር ያራቀው አትሌቱ በ2022 (እአአ) ከታይምስ ኦፍ ኢንዲያ ጋዜጣ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ “ሌላ አማራጭ ስላልነበረ ትምህርት ቤት ሮጬ እሄድ ነበር። ወላጆቼን በእርሻ ሥራ ለመርዳት ደግሞ ወደ ቤት በሩጫ መመለስ ነበረብኝ” ብሏል።

ከፍተኛ ገንዘብ የሚያስገኘው ማራቶን

ዘመናዊ የከተማ አኗኗር የብዙዎችን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ለውጧል። ነገር ግን ብዙዎች አሁንም ይሮጣሉ። በኬንያ ለብዙ ዓመታት የኖረው እና የሠራው የቀድሞ ታዋቂው ስፔናዊ ሯጭ ማርክ ሮግ በልጆቹ ትምህርት ቤት ስላሉ እናቶች ምን እንደተሰማው ያስታውሳል።

“ከዚያ ወዲህ እኔ እዚያ ሯጭ ነኝ አልልም ነበር። ከእኔ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ምርጥ ሰዓት” ያላቸው እንዳሉ እየቀለደ ተናግሯል።

ከናይሮቢ በስተሰሜን 260 ኪሜ ርቀት ላይ በምትገኘው ኢቴን ከተማ የተስፈኛ ሯጮችን ዕድገት ይከታተላል። ከተማዋ ከባሕር ጠለል በላይ 2400 ሜትር ላይ ትገኛለች። የቀድሞ እና የአሁን ታዋቂ አትሌቶችን ያወጣችው ኢቴን “የሻምፒዮኖች መፍለቂያ” በመባል ትታወቃለች።

ታሪኩ ወጣት ሯጮችን በማነሳሳት በገንዘብ ማግኛነም አድርገውታል። “ኬንያውያን በአትሌቲክስ ኑሯቸውን የመምራት ዕድል እንዳለ ያውቃሉ። በዙሪያቸው ብዙ አርአያዎችን በማግኘታቸውም ይነሳሳሉ።”

ለታዋቂ የማራቶን ውድድር ለአሸናፊዎች እስከ 150 ሺህ ዶላር ሽልማት ይሰጣል። ስም ያላቸው ሯጮች ደግሞ በመሳተፋቸው ብቻም ክፍያ ያገኛሉ። ለአዳዲስ ክብረ ወሰኖች፣ ለፈጣን ሰዓቶች እና የግል ስፖንሰርሺፕ ስምምነቶች ታዋቂ ሯጮች ብዙ ጊዜ ጉርሻዎችን ያገኛሉ።

ኬልቪን ኪፕቱም ባደረጋቸው ሦስት የማራቶን ውድድሮች ብቻ ግማሽ ሚሊዮን ዶላር ከሽልማት እና ከጉርሻ ገቢ እንዳገኘ ይታመናል ሲሉ የኬንያ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ያልተመዘገበው የኪፕቾጌ ሰዓት

እአአ በ2019 ኤሊዩድ ኪፕቾጌ በቪየና በተዘጋጀ ልዩ ውድድር ማራቶንን በ1፡59፡40 መሮጥ ችሏል።

ይሁን እንጂ የስፖርቱ የበላይ አካል በሆነው የዓለም አትሌቲክስ እውቅና አልተሰጠውም።

ኮከብ ሯጮች በፍጥነት እንዲሮጡ ለመርዳት አሯሯጮች መኖራቸው የተለመደ ቢሆንም፣ ኪፕቾጌ በቪየና 35 አሯሯጭ ነበሩት። ከነፋስ ለመከላከል በሚያመች መልኩ በ‘V’ ቅርጽ ቀድመውት ሲሮጡ ነበር።

ከአሯሯጮቹ ፊት ደግሞ በርካታ መኪኖች ነበሩ። አንደኛው መኪና በምን ፍጥነት መሮጥ እንዳለባቸው የሚያሳይ ሌዘር ብርሃን ሲያሳያቸው ነበር።

በተለመዱት ውድድሮች የሚገኙ ቋሚ ቦታዎችን ከመጠቀም ይልቅ ኪፕቾጌ በብስክሌት አብረውት በመሄድ የሚጠጣ የሚያቀብሉት ሰዎችም ነበሩት።

እንግሊዛዊው የስፖርት ሳይንቲስት ፕሮፌሰር አንድሪው ጆንስ የኤክሰተር ዩኒቨርሲቲ ምሁር ሲሆኑ፣ ለቢቢሲ እንደተናገሩት “ውጤቱ ኦፊሴላዊ ባለመሆኑ ግድ የለኝም። በስፖርቱ ላይ የተሳተፉ በሙሉ ከሁለት ሰዓት በታች መሮጥ ይቻል እንደሆነ ለማወቅ ፈልገው ነበር። ይህንንም አሳክተነዋል” ብለዋል።

“በቁጥጥር እና ድጋፍ በነበረው ሩጫ ላይ እንኳን ኪፕቾጌ ውጤታማ ለመሆን የላቀ አሯሯጥ ማሳየት ነበረበት።”

ማራቶን ሯጮች ሰውነት ላይ ምን ያስከትላል?

ኬልቪን ኪፕቱም ባለፈው ዓመት በቺካጎ ክበረ ወሰኑን ሲሰብር፣ አንዱን ኪሎ ሜትር በአማካይ ሁለት ደቂቃ ከ52 ሰከንድ በሆነ ፍጥነት ሮጧል። የዓለም አትሌቲክስ (2019) የቅርብ ጊዜ መረጃ እንደሚያሳየው አማተር የሆነ ወንድ የማራቶን ሯጭ አማካይ ፍጥነቱ በኪሎ ሜትር ስድስት ደቂቃ ከ43 ሰከንድ ነው።

ሯጭ ቢሆንም ይህ በአካል ላይ ከባድ ጉዳት ሳያመጣ አይቀርም ሲሉ ፕሮፌሰር ጆንስ ያብራራሉ። “በከፍተኛ ጥንካሬ የሚሮጥ ረዥም ርቀት ነው። ምንም ዓይነት የሩጫ ደረጃ ላይ ያለ ሯጭ ቢሆንም ሰውነት ይቀጣል። እንዲሁም የአዕምሮ ጫና አለው።”

በማራቶን ወቅት በአማካይ አንድ ሯጭ በአከርካሪ አጥንት መጨናነቅ ምክንያት ወደ 1.25 ሴንቲ ሜትር ቁመት ይቀንሳል። በኋላ ላይ ግን ወደ መደበኛው ቁመት ይመለሳል።

በተጨማሪም በጊዜያዊነት እስከ 5 ኪሎ ግራም መቀነስ ሊያስከትል ይችላል። የሯጮች ጥፍር መድማት፣ ጥቁር መሆን አልፎ ተርፎም ጥፍር መነቀል ማጋጠሙ የተለመደ ነው።

“ግን ሰዎችን አናስፈራራ። በተገቢው ሥልጠና ሰውነት ከእነዚያ ተግዳሮቶች ጋር ይለማመዳል” ይላሉ ፕሮፌሰር ጆንስ።

ከከባዱ ሥልጠና ጋር በሳምንት ቢያንስ 160 ኪሎ ሜትር መሮጥን ስለሚጠይቅ በጡንቻዎች፣ በአጥንት እና በመገጣጠሚያ ላይ ጉዳት ያስከትላል። በዚህ ምክንያትም ነው ታዋቂ ሯጮች በዓመት ሁለት ማራቶን ብቻ ይሳተፋሉ ይላሉ።

ኤሊዩድ ኪፕቾጌ እአአ በ2013 በጀመረው የማራቶን ሕይወቱ 18 ውድድሮችን ብቻ ነው የተሳተፈው።

በዚህ ዓመት ለሦስተኛ ጊዜ የኦሊምፒክ ወርቅ ለማግኘት በሚያደርገው ሙከራ በሐምሌ ላይ ለሚጀመረው የ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ ልምምዱን ከመጀመሩ በፊት በቶኪዮ ማራቶን ለመሳተፍ አቅዷል።

‘ኪፕቾጌን መርሳት አይገባም’

ኪፕቾጌ ከሁለት ሰዓት በታች ማራቶንን ለማጠናቀቅ ቀዳሚው ዕጩ ነው። ከሁለት ሰዓት ከሁለት ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ርቀቱን ከሮጡ ሦስት ሰዎች በሕይወት ካሉት አንዱ ነው። ሌሎቹ ኢትዮጵያውያኑ ቀነኒሳ በቀለ እና ሲሳይ ለማ ሲሆኑ፣ ሁለቱም አሁንም እየተወዳደሩ ይገኛሉ።

ኪፕቱም ሞት ቀድሞታል። የኪፕቾጌ ትልቁ ፈተና ደግሞ በቅርቡ 40 ዓመት ሊሞላው መቃረቡ ነው።

ነገር ግን “ኪፕቾጌን መርሳት አይገባም” በማለት ፕሮፌሰር ጆንሰን አስጠንቅቀዋል።

ሌሎች ባለሙያዎችም ደግሞ “ከስምጥ ሸለቆ አስገራሚ ሯጭ” ሊመጣ እንደሚችል ይገልጻሉ።

“ልክ ኪፕቱም ‘ሳይታሰብ እንደመጣው ሁሉ’ ሌላ ሯጭ ከስምጥ ሸለቆ ሊወጣ ይችላል። ምክንያቱም እስካሁን ያልሰማናቸው ብዙ ጎበዝ ሯጮች እዚያ አሉ” ይላል ማርቲን ኪይኖ።

ተሰጥኦ ወደ ስኬት የሚያመራው የተመቻቸ ሁኔታ ሲኖር ነው። አየሩ በጣም ሞቃታማ ወይም እርጥበታማ ሊሆን አይገባም። መወዳደሪያ ቦታው በተቻለ መጠን ዳገት ቁልቁለት ሊኖረው አይገባም።

የበርሊን ማራቶን ካለፉት 10 የወንዶች የዓለም ክብረ ወሰኖች መካከል ስምንቱ የተሰበረበት ነው። በቅርበት መከታተል ሊኖርብን የሚገባን ሌሎች ውድድሮች ደግሞ ለንደን፣ ቺካጎ እና ሮተርዳም ናቸው።

ማርክ ሮግ “በቅርቡ እንደሚሳካ ምንም ዋስትና የለም። ኬልቪን ኪፕቱም እንዳደረገው ሁሉ የሰው ልጅ አሁንም ለማስደነቅ ምንም አያንሰውም” ብሏል።