ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዱባይ ማራቶን በኢትዮጵያውያን አትሌቶች የበላይነት ተጠናቀቀ
ትናንት ሌሊት በተከናወነው የዱባይ ማራቶን በሁለቱም ጾታ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በበላይነት አጠናቀዋል።
በወንዶች አትሌት ኦሊቃ አዱኛ ቢቂላ ሲያሸንፍ በሴቶች ደግሞ ወርቅነሽ ደገፋ የመጀመሪያ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
አትሌት ኦሊቃ ውድድሩን በአንደኝነት ለማጠናቀቅ 02፡06፡15 የፈጀበት ሲሆን፤ ሌሎች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከሦስተኛ እስከ 10 ያለውን ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል።
ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ኬኒያዊው ኤሪክ ኪፕታኑ ነው።
በሴቶች በተካሄደው ውድድር አትሌት ወርቅነሽ ደገፋ 02፡19፡37 በመግባት በአንደኝነት ስትጨርስ፤ ሌሎች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከሁለተኛ እስከ ዘጠነኛ ያለውን ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል።
አትሌት ጉተኒ ሾኔ ሁለተኛ ስትሆን አትሌት በዳቱ ሂርጳ ደግሞ ሦስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
አትሌት ወርቅነሽ ትናንት ከውድድሩ በፊት ለቢቢሲ ለዚህ ውድድር ከፍተኛ ዝግጅት ማድረጓን ተናግራለች። አትሌት ወርቅነሽ "የዱባይ አቀማመጥ ለኔ በጣም ምቹ ነው አሸንፋሁ" ብላ ነበር።
አትሌት ወርቅነሽ ደገፋ የ2017ቱን የዱባይ ማራቶን ማሸነፏ ይታወሳል።
ሁለተኛ ደረጃን የያዘችው አትሌት ጉተኒ ሾሜ 02፡20፡11 የገባች ሲሆን አትሌት በዳቱ ደግሞ 02፡21፡54 በሆነ ሰዓት አጠናቃለች።
የዱባይ ማራቶን መዘጋጀት ከጀመረ ወዲህ ኢትዮጵያውያን ሴት አትሌቶች 15 ጊዜ በወንዶች ደግሞ 14 ጊዜ አሸንፈዋል።