ኬንያ ከአዲሱ አሠራሯ ውጪ ኢትዮጵያውያን ያለክፍያ ወደ አገሯ እንዲገቡ ፈቀደች

የፎቶው ባለመብት, AFP
ኬንያ ወደ ግዛቷ ለሚገቡ ተጓዦች ቪዛ መጠየቋን ካቆመች በኋላ ከጀመረችው አዲስ የጉዞ ፈቃድ ማረጋገጫ ጥያቄ እና ክፍያ ኢትዮጵያውያን ነጻ እንዲሆኑ መወሰኗን በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር አስታወቁ።
አምባሳደር ባጫ ደበሌ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ኢትዮጵያውያን ከአዲሱ አሠራር ነጻ ሆነው ቀደም ሲል እንደነበረው ወደ ኬንያ መግባት እንዲችሉ በመንግሥት የቀረበውን ጥያቄ የኬንያ መንግሥት ተቀብሎታል።
ኬንያ ካለንበት የአውሮፓውያን ዓመት መጀመሪያ አንስቶ የመላው ዓለም ተጓዦች ያለ ቪዛ በበይነ መረብ አማካይነት የጉዞ ፈቃድ ለማግኘት በማመልከት እና ክፍያ በመፈጸም ብቻ ወደ አገሯ እንዲገቡ አዲስ አሠራር መጀመሯ ይታወቃል።
ነገር ግን ለበርካታ ዘመናት ወደ ኬንያ ያለ ቪዛ እና ክፍያ ሲገቡ በነበሩት ኢትዮጵያውያን ላይ ይህ አሠራር ወጪን እና በውስብስብ የጉዞ ሂደት ውስጥ እንዲያልፉ በማድረግ ቅሬታ እና ጥያቄን ሲፈጥር ቆይቷል።
ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ጉዳዩን ከኬንያ ባለሥልጣናት ጋር እንደሚነጋገርበት አሳውቆ የነበረ ሲሆን፣ አሁን የኬንያ መንግሥት ኢትዮጵያውያን ቀደም ሲል እንደነበረው ወደ አገሩ ያለ ምንም ክፍያ እንዲገቡ መፍቀዱን በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ባጫ ደበሌ አስታውቀዋል።
አምባሳደር ባጫ በኤክስ (የቀድሞው ትዊተር) ገጻቸው ላይ የኬንያ መንግሥት ኢትዮጵያውያንን ከአዲሱ የጉዞ ማረጋገጫ የክፍያ ሥርዓት ውጪ እንዲሆኑ የቀረበለትን ጥያቄ በአፋጣኝ ተቀብሎ በመወሰኑ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
አምባሳደሩ አክለውም ወደ ኬንያ የሚጓዙ ኢትዮጵያውያን ቪዛ እና ተያያዥ ክፍያ እንደማያስፈልጋቸው ገልጸው፣ ነገር ግን በበይነ መረብ በኩል የሚሞላውን ፎርም ቀድመው መሙላት እንደሚጠበቅባቸው አሳውቀዋል።
ኬንያ ከየትኛውም የዓለም ክፍል ለሚመጡ ተጓዦች ቪዛን በማስቀረት አዲሱን የማመልከቻ እና የክፍያ ሥርዓት የጀመረችው ጎብኚዎች እንደልብ እንዲንቀሳቀሱ ለማስቻል በሯን ክፍት ለማድረግ በያዘችው ዕቅድ መሠረት ነው።
ነገር ግን ኢትዮጵያውያን ቀድሞውኑም ቪዛም ሆነ ሌላ ማመልከቻ ሳያስፈልጋቸው ወደ ኬንያ በመግባት አስከ ሦስት ወራት የመቆየት ፈቃድ ነበራቸው። የአዲሱን አሠራር መተዋወቅ ተከትሎ ይህ የኢትዮጵያውያን ነጻ እንቅስቃሴ ለተወሰነ ጊዜ ተስተጓጉሎ ነበር።
የኬንያ መንግሥት የጉዞ ማረጋገጫ እና የክፍያ ሥርዓትን ተግባራዊ ካደረገ ከሁለት ወራት ገደማ በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት ጥያቄን ተቀብሎ ኢትዮጵያውያን ያለክፍያ ወደ ኬንያ መግባት የሚችሉበት መንገድ መከፈቱን አምባሳደር ባጫ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ እና ኬንያ ለረጅም ዘመናት ዜጎቻቸው ወደ አንዳቸው ግዛት ሲጓዙ ያለቪዛ ለመግባት የሚያስችል ስምምነት ሰላላቸው የሁለቱ አገር ዜጎች ያለቪዛ እና ክፍያ ያለችግር ሲዘዋወሩ ቆይተዋል።
አዲሱ አሠራር ከተጀመረ በኋላ ኢትዮጵያ አባል ካልሆነችበት የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ አባል አገራት ዜጎች ውጪ ያሉ የአፍሪካ አገራት በሙሉ ኤሌክትሮኒክ የጉዞ ፍቃድ (ኤሌክትሮኒክ ትራቭል ኦተራይዜሽኝ - ኢቲኤ) የሚባለውን እንዲፈጽሙ ይጠበቅባቸዋል።
በዚህ ሂደትም ተጓዦች ከጉዟቸው ሦስት ቀናት ቀድመው ከኬንያ መንግሥት ባለሥልጣናት በበይነ መረብ የሚሞሉት ፎርም ተቀባይነት ማግኘት እና እስከ 30 ዶላር የ ሚደርስ ክፍያ እንዲፈጽሙ ይጠበቅባቸዋል።












